የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የውስጥ ቢሮዎች ዕድሳት ተጠናቆ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ ተመረቀ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የውስጥ ቢሮዎች ዕድሳት ተጠናቆ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ ተመረቀ ።
የሀገረ ስብከቱ ዋና መሥሪያ ቤት ቀደም ሲል ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ሊቀ ጳጳስ በሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ለመሥራት አቅደው ባይሳካም በኋላ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት ከብዙ እንቅስቃሴ በኋላ በሰኔ 15/1999 ዓ/ም ቋሚ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ዛሬ ባለበት ቦታ ሕንጻ እንዲሠራ ተፈቅዷል።
ከዚያም በሊቀ ጳጳሱ ትጋት በሁሉም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች ድጋፍና የኔባይነትት በ16,770,984.65 ብር ተሠርቶ ሚያዚያ 2001 ዓ/ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጬጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቡራኬ ተመርቆ ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል።
ከዚያም በብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ በዚህ ዓመት በ2017 ዓ/ም የኮሪደር ልማቱን መነሻ በማድረግ ውጨኛ ክፍልና የጣራ ቅየራ እንደተደረገለት መረጃዎች ያመለክታሉ።
በግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ከመጡ ጀምሮ ሥራዎችን በሦስት ወራት ዕቅድ በመከፋፈል እየሠሩ ይገኛሉ።
ከነዚህ በመጀመሪያ ሦስት ወራት ወስጥ እንዲሠሩ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ያደሩና የሰነበቱ ሥራዎች መካከል በቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተወሰነላቸው የ150 ተፈናቃይ አገልጋዮችን ሥራ መመደብ፣ የሀገረ ስብከቱን ዋና መሥሪያ ቤት ከሊቀ ጳጳስ ቢሮ ጀምሮ ያሉ ቢሮዎች ለሥራ መች እንዲሆኑ ማደስና የአስተዳዳር ችግር የተፈጠረባቸውን አብያተ ክርስቲያናት መፍትሔ ሰጥቶ ማቃናትና የሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ጥናት የሚሉት ይገኙበታል።
ከላይ ከተዘረዘሩት ቅድሚያ ከተሰጣቸው የሦስት ወር ሥራዎች መካከል በዛሬው ዕለት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት የተመረቀው የሀገረ ስብከቱ ቢሮች ዕድሳት አንዱና ዋነኛው ነው።
የቢሮ ዕድሳቱን በአስተዳዳር ጉባኤው በማስወሰን የጀመሩት ብፁዕነታቸው ጥንታዊውና ታሪካዊውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብሎም የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን መልክና ክብርን ታሳቢ ያደረገ የመገልገያ ቢሮ እንዲኖር ለማድረግ እንደሆነም ተገጿል።
በየጊዜው የሚመደቡ ብፁዓን አባቶች በተለይም ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሊቀ ጳጳስ ለጊዜው የሚበጅና የሚመጥን ቢሮ እንደሠሩ የሚታወስ ሲሆን የዕድሳቱ መሠረታዊ ለውጣ ሳይፈጥር ዘመኑንና ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን የክብር ምዕራፍ መሠረት በማድረግ በመጠኑም ቢሆን ለማሻሻልና ለመጠበቅ ተችሏል ተብሏል።
የቢሮዎቹ መታደስ ለዘለዓላማዊ ሕይወት በምናገለግልባት ቤተ ክርስቲያንና ሕያውን አደራ በሰጠን በእግዚአብሔር ፊት በጥንቃቄ እንድናገለግል ምክንያት እንዲሆን እንዲሁም የአገልጋዮችን የአእምሮና አካባቢያዊ መደላድል ለመፍጥር እንደሆነም ተነግሯል።
የዕድሳቱ ሙሉ ወጪ ከቢሮዎች ቀለምና የሊቀ ጳጳሱና ሥራ አስኪያጅ ጠረጴዛና ወንብር ውጭ ሙሉ በሙሉ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ባመጡ በጎ አድራጊ ኦርቶዶክሳዊ እንደተሸፈነ የደረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በአባታዊ ቡራኬ የመረቁት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የተመደቡት ጊዜ ቅርብ ከመሆኑ አካያ የማይጠበቅና የማይገመት ድንቅና ታሪክን ያስቀለጠለ እንዲሁም ዘመኑን የዋጀ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም የሥራ ቦታን ምቹ ማድረድግ ይልቁንም ንጹሐ ባሕርይ አምላክ በሚመለክባት ቤተ ክርስቲያን ለሚሠራ ሥራ ንጹሕ ቦታና አካባቢ ማዘጋጀቱ ለውጤታማ ሥራ ከማብቃቱ በላይ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ ለሀገረ ስብከቱ የመደባቸው ሊቀ ጳጳስና በብፁዕነታቸው ተመርጠው የሾሙት ዋና ሥራ አስኪያጅ የተጣለባቸውን ከፍተኛ አደራ እንደሚወጡና በበለጠ ትውልዳዊና ቤተ ክርስቲያናዊ ሥራ እንደሚገለጡ ማሳያ ነው ለዚህም ተስፋቸው የጸና ነው ብለዋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና ብፁዕ የብዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ጨምሮ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የመንበረ ፓትርያርክና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሐላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ኮሆነት ዋና ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ተገኝተዋል።