የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነድ ርክክብ ተካሄደ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የተቋማዊ ለውጥ አመራር ሲያጠና የቆየው የባለሞያ ቡድን የካቲት 6 ቀን 2006 ዓ.ም የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነዱን ለሀገረ ስብከቱ በይፋ አስረክቧል፡፡
የካቲት 6 ቀን 2006 ዓ.ም ረፋድ ላይ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተካህደው የርክክብ እና ምስጋና መርሐ ግብር፣ 13 አባላት ያሉት የባለሞያ ቡድኑ ከ800 በላይ አጠቃላይ ገጾች ያሏቸውን 12 ሰነዶች በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳትና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለኾኑት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አስረክቧል፡፡
ከረፋዱ 4፡00 – 8፡00 በዘልቀው በዚኹ የርክክብና የምስጋና መርሐ ግብር፣ የሀ/ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ የዋና ክፍል ሓላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል::
በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያና በረዳት ሊቀ ጳጳሱ የቅርብ ክትትል የሀ/ስብከቱን የመዋቅር አደረጃጀትና አሠራር ጥናት ያከናወነው የባለሞያ ቡድኑ በዛሬው ዕለት ለሀ/ስብከቱ በይፋ ያስረከበው ሰነድ÷ በሀገረ ስብከቱ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ ሓላፊዎች፣ በ169 ገዳማትና አድባራት የአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ የካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የሰንበት ት/ቤቶችና የምእመናን ተወካዮች ውይይት የተደረገበትና ከውይይቱ በተሰበሰቡ ግብዓቶች የዳበረና የተስተካከለ ነው፡፡
ከውይይት መድረኩ የተገኘውን የተሳታፊዎች ትችትና አስተያየት በከፍተኛ ጥንቃቄ መለየቱንና ማደራጀቱን የገለጸው የባለሞያ ቡድኑ፣ በተለይም÷ ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያለውን የአደረጃጀት መዋቅር፣ የአገልግሎት መደቦችን የሥራ ዝርዝር መመሪያ፣ የገዳማትና አድባራት የደረጃ መስፈርት መመሪያን፣ የሰው ኃይል ትመናና የተፈላጊ ችሎታ መስፈርት መመሪያን እንዲሁም የፋይናንስ ፖሊሲውንና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያውን መሠረታዊ ማስተካከያ በማድረግ ጭምር ለማደራጀት ሌት ተቀን ሲሠራ መሰንበቱ ተዘግቧል፡፡
በርክክቡ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአጥኚው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ አሠፋ እንደገለጹት “ቡድኑ የልጅነት ድርሻውን ይወጣ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት ስትሰጠው ወደ ዋና ጥናቱ ከመግባቱ በፊት ሥራው የተቃና ይሆን ዘንድ በአባቶች ጸሎት እንዲታሰብ መብዓ አሰባስቦ መላኩ ለጥናት ቡድኑ ብርታት እንዲሁም ሥራ መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጐለታል፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱሳን ጸሎት አልተለየንም” ብለዋል፡፡
በመቀጠልም “ጥናቱን እያጠናን ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ምእመናን ድረስ በማወያየት 96 በመቶ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን በውይይቱ ወቅት እንዲካተቱ የተነሡ ነጥቦች ተካተውና ተሻሽለው ለዚህ ቀን ደርሰናል፡፡
• ለባለሞያ ቡድኑ ይህ ታሪካዊ ዕድል ተሰጥቶን ችግር ፈቺ ጥናት እንድናጠና በመደረጋችን ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡
• የጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ የጥናት ሰነዱ በየደረጃው ካሉ ሓላፊዎች ጀምሮ እስከ አጥቢያ ምእመናን ድረስ ወርዶ ውይይት እንዲደረግበት በወሰነው መሠረት ውይይቱ ተከናውኗል፡፡
• በሀ/ስብከቱ አዳራሽ ለ14 ቀናት በተካሔደው ውይይት÷ የጥናት ሰነዱ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የሀ/ስብከቱ የዋና ክፍል ሓላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሥራ አስኪያጆች፣ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ የካህናት፣ የምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ተወካዮች ሐሳብ የተካተተበትና 96 በመቶ ተቀባይነት ያገኘ በመኾኑ ከአኹን በኋላ የመላው የቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች ሰነድ ነው ብለን እናምናለን፡፡
•ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎችና አገልጋዮች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሓላፊዎች፣ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ ከምንምና ከማንም በላይ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ድረስ በኹሉ ነገር ያልተለዩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ጥናቶቹም፡-
1. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመዋቅር የአደረጃጀት ጥናትና መመሪያ 119 አንቀጽ
2. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአብያተ ክርስቲያናት የደረጃ መስፈርት መመሪያ 23 ገጽ
3. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአገልግሎት መደቦች የሥራ ዝርዝር መመሪያ 120 ገጽ
4. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰው ኃይል ትመናና የተፈላጊ ችሎታ መስፈርት መመሪያ 53 ገጽ
5. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደመወዝ ስኬል ጥናት 99 ገጽ
6. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአገልግሎጋዮች ማስተዳደሪያ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 125 ገጽ
7. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥልጠናና የሰው ሃብት ልማት ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 30 ገጽ
8. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፋይናንስ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 107 አንቀጽ
9. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የግዢ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር መመሪያ 26 ገጽ
10. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የልማት ሥራዎች ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 16 ገጽ
11. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዕቅድና ሪፖርት ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ መመሪያ 31 ገጽ
12. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 57 ገጽ
13. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥልጠና ማእከል፣ ወላጅ አልባ ሕፃናትና የአረጋውያን መርጃ ማእከል ፕሮጀክት ጥናት ሰነድ /የተሠጠ/
ሲሆኑ የዚህ ጥናት ትግበራ ስልትና የእያንዳንዱ መመሪያና ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ብዛት ያላቸው ቅጾች ለትግበራ ስለሚያስፈልጉ ወደፊት ተጠናቀው ይቅርባሉ” በማለት ገልጸው ሰብሳቢው የአጥኚው ቡድን አባላት ለብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጥናት ሰነዱን እንዲያስረክቡ ካደረጉ በኋላ “በዚህ ጥናቱን በሚመለከት ማብራሪያ ለሚጠይቀን አካል ሁሉ ምላሽ ለመስጠትና ለመወያየት ዝግጁ ነን” በማለት ገልጸዋል፡፡
ከአጥኚ ኮሚቴው በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ በላይ መኰንን “እንደገለጹት ለቤተ ክርስቲያን ብላችሁ ጊዜያችሁን ገንዘባችሁን ሁሉን ነገር አውጥታችሁ የሠራችሁትን እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ፡፡
እግዚአብሔር ለሥራ ጊዜ አለው፡፡ ሁሉም ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ነው፡፡ ቅዱስ አባታችንም ጥናቱ ለምን ቆየ? ከምን ደረሰ? እያሉ እየጠየቁ ነው፡፡ የተቃውሞ ጥያቄ የሚያነሱትም ነፃ አስተሳሰብ ነውና ሊመሰገኑ ይገባል” ብለዋል፡፡
ጥናቱን የተረኩበት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ባደረጉት ንግግር “መነሻ የሚሆን ነገር እንድናቀርብ በመጠየቃችን እናንተም ይህን በመሥራታችሁ እግዚአብሔር በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ያድላችሁ፡፡
በእግዚአብሔር የምንጠየቀው የሚጠብቅብንን ሳንሠራ ስንቀር ነው፤ የታዘዛችሁትን አዘጋጅታችሁ አቀርባችኋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተግባራዊ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ ቃለ ዓዋዲው መጀመሪያ ሲረቀቅ ብዙ ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር፤ ግን ተግባራዊ ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ የሚያስፈልገው ሁላችንም ወደ አንድ መጥተን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን ማድረግ ነው” በማለት አባታዊ ምክር ሰጠተዋል፡፡ በርክክቡ መርሐ ግብር ላይ ለተገኙት ተሳታፊዎች የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ የምሳ ግብዣ አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናቶችና መመሪያዎች ዝግጅት ማጠቃለያ ሪፖርት(የባለሞያዎች አጥኚ ቡድን)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአራት ተከፍሎ የነበረውን አደረጃጀት ወደ አንድ እንዲመጣ ያስተላለፈውን ውሳኔ መሰረት አድርጎ በርካታ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶች እንዲዘረጉ ጥናት እንዲካሄድ ወስኗል፡፡ ለዚህ የለውጥ እንቅስቃሴም የመጀመሪያው የብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተደርጎ መሾማቸው ነው፡፡ ከብፁዕነታቸው ሲመት ማግስት ጀምሮ የአሠራር ለውጡ እንቅስቃሴ ቀጥሏል፡፡
ብፁዕነታቸው የተሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ያስችላቸው ዘንድ አምስት አባላት ያሉት የጥናት ኮሚቴ አቋቁመው ለሦስት ወራት ማለትም ከሐምሌ 2005 እስከ መስከረም 2006 የሚያገለግል ከሀገረ ስብከት እስከ ክፍል ከተማ ቤተክህነት ድረስ የሚደርስ አደረጃጀትና ተቋማዊ መዋቅር ተጠንቶና በቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ ኮሚቴ ጸድቆ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
የሙከራ ትግበራውን መሠረት በማድረግ እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የሚደርስ እና ሌሎችም አህጉረ ስብከቶች እንዲሁም ለመላዋ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የሚያገለግል የተቋማዊ መዋቅርና የአሰራር ሰነዶችን እንዲዘጋጅ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተሰጠው መመሪያና ቡራኬ አማካይነት ስራው ሰፊ በመሆኑ ተጨማሪ ባለሙያዎችን በማካተት የኮሚቴውን ቁጥር አስራ ስምንት በማድረግ ሥራው እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ በጥናቱ እስከመጨረሻው የዘለቁት 13 ባለሙያዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ጥናቱ ተጠናቅቆ ተግባራዊ እንዲደረግ ከፍተኛ ጉጉት ያላቸው ብፁዕነታቸው ያላሰለሰ ክትትልና ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ከጥናቱ ጎን ለጎን ከጥናት ኮሚቴ አባላት መካከል የስልጠና ባለሙያዎችን በመጠቀም ለሀገረ ስብከቱ የአገልግሎት ክፍል ኃላፊዎች በለውጥ ሥራ አመራር፣ በገንዘብ አስተዳደር እንዲሁም በኦዲትና ኢንስፔክሽን አሰራር ዙሪያ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
የጥናት ቡድኑ ወደ ዋና የመዋቅርና የአሰራር መመሪያዎች ጥናት ከመግባቱ በፊት ሥራው የተቃና ይሆን ዘንድ በአባቶች ጸሎት እንዲታሰብ መብዓ አሰባስቦ በመላኩ ለጥናት ቡድኑ ብርታት እንዲሁም ለሥራው መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
የአደረጃጀትና የአሠራር መመሪያዎች የጥናቱ ረቂቅ ለጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ቀርቦ አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ በየደረጃው ላሉ ኃላፊዎች እስከ አጥቢያ ምዕመናን ድረስ ውይይት እንዲደረግበት በተወሰነው መሠረት ውይይቱ ተከናውኗል፡፡ በዚህ ውይይት የተካፈሉት የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ክፍል ኃላፊዎች የክፍለ ከተማ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ የካህናት ተወካዮች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች፣ የምእመናን ተወካዮች እና የሰበካ ጉባኤ አባላት በወጣላቸው መርሀ ግብር መሰረት ከየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ 16 ሰዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ ለ14 ቀናት በጥናቱ ላይ ውይይት ተካሂዶ 96 በመቶ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ በተካሄዱ ውይይቶች ላይ የተነሱ ነጥቦች በአግባቡ ተመዝግበው በአጥኝ ቡድኑ እንደገና ተገምግመው በእያንዳንዱ የመዋቅርና የአሰራር መመሪያ ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ በቡድኑ የተሰሩት ሰነዶች ዝርዝርም፡-
1. የአደረጃጀትና የመዋቅር ጥናትና መመሪያ፣
2. የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ደረጃ መስፈርት ጥናትና መመሪያ፣
3. የአገልግሎት መደቦች የሥራ ዝርዝር ሰነድ፣
4. የተፈለጊ ችሎታ መመሪያ እና የሰው ኃይል ትመና ሰነድ፣
5. የደመወዝ ስኬል ጥናት ሰነድ፣
6. የአገልጋዮች ማስተዳደሪያ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ፣
7. የፋይናንስ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ፣
8. የልማት ሥራዎች ፖሊሲና የአፈጸጸም መመሪያ፣
9. የግዢ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ
10. የሥልጠናና የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ፣
11. የዕቅድ ዝግጅት፣ ሪፖርትና ግምገማ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ፣
12. የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ
13. የሥልጠና ማዕከልና የአረጋዊያንና የሕጻናት መርጃ ማዕከል ፕሮጀክት ጥናት ሰነድ፣
በዚህ ሥራ ውስጥ ብዙ ተግዳሮቶች የገጠሙን ቢሆንም በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት ያለፍናቸው ሲሆኑ ሳንጠቅሰው የማናልፈው ግን በሰነዱ ላይ ሳይሆን በአጥኝው አካል ላይ ቅሬታ ያላቸው አካላት ጥያቄ ሲያቀርቡ በሠነዱ ዝግጅት ምንም ግንኙነት የሌለው አካል እንዳዘጋጀው ተደርጎ ሥራውን ውድቅ ለማድረግ የተሄደበት አግባብ ላይ የሥራው ባለቤቶች የሆን እኛን ሳያነጋግሩ ወደ ውሳኔ መኬዱ አግባብ ነው ብለን አናምንም፡፡
ይህ ሰነድ የቤተክርስቲየንን አስተዳደር በሁሉም ዘርፍ በማሻሳል ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በቅዱስ ፓትርያርኩም በአንድ ወቅት እንደተነገረው ለሌሎች አህጉረ ስብከቶች እንደ ነባራዊ ሁኔታቸው እየታየ ለእነርሱ በሚሆን አግባብ እንዲዘጋጅላቸው በቅዱስ ሲኖዶስ አቅጣጫ እንዲሰጥበት እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡
በሥራው ሂደት ላይ የተከሰቱትን ተግዳሮቶችን በአግባቡ መዝኖ እና አይቶ ወደ ተግባር እንዲገባ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካላት በሙሉ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራ እንላለን፡፡
ሰነዱ የካህናት ፣የምእመናንና ሰ/ት/ቤት ወጣቶች ትግበራውን በአግባቡ እንዲያስኬዱት እንጠይቃለን፡፡
ለዚህ የመዋቅርና የመመሪያዎች ጥናት ሰነድ ዝግጅት መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉ ስማቸውን ለጊዜው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስብከቱ ሃላፋችና አገልጋዮች የክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ኃላፊዎች የአጥቢያ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ከምንምና ከማንም በላይ ከጀምሩ እስከ ፍጻሜው ድረስ በሁሉ ነገር ያልተለዩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ታሪካዊ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለጥናት ቡድኑ ይህንን ታሪካዊ ዕድል ተሰጥቶን ችግር ፈቺ ጥናት እንድናጠና በመደረጋችን ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡
በመጨረሻ ይህ ሰነድ መታሰቢያነቱ ለብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ለሰንበት ት/ቤቶችና ለምዕመናን እንዲሆን እንመኛለን፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!
{flike}{plusone}