የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት አስመልክቶ ከአብነት መምህራን ጋር ውይይት አካሄደ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት በመምህርነት ሥራ ተመድበው ከሚያገለግሉ የአብነት መምህራን ጋር ረዕቡ የካቲት 9 ቀን 2008 ዓ.ም ለግማሽ ቀን የቆየ የጋራ ምክክርና ውይይት አካሂደዋል፡፡
የውይይቱና ምክክሩ አጀንዳ ከፊታችን የሚጠብቀንን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ዓቢይ ጾም አስመልክቶ የስብሐተ ነግህ አገልግሎት በማይካሄድባቸው ገዳማትና አድባራት የስብሐት ነግህ አገልግሎት እንዲካሄድ፣ እስከ አሁን ድረስ የስብሐተ ነግህ አገልግሎት ሲካሄድባቸው የቆዩት ገዳማትና አድባራት የስብሐት ነግሑ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በተጨማሪ በወርሐ ጾሙ የጾመ ድጓ አገልግሎት እንዲካሄድ፣ በየሳምንቱ ዕሁድ በሁሉም ገዳማትና አድባራት የመወድስ አገልግሎት እንዲፈጸም፣ በየወር በዓላቱ የማኀሌቱ ሥነ ሥርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የመምህራን ዋና ተግባራቸው የማስተማር ሥራ እንደመሆኑ መጠን የመማር ማስተማሩ ሂደትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በአንድ ገዳም ወይም ደብር ቢያንስ 25 ደቀ መዛሙርት የመማር ዕድል እንዲኖራቸውና ሰርከ ህብስትም የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው፣ በሁሉም ገዳማትና አድባራት የአብነት ትምህርት መምህራን እንዲኖሩና ሁሉም የአብነት ትምህርቶች ተተኪ ደቀ መዛሙርት እንዲኖራቸው የሚል ሲሆን በሁሉም አጀንዳዎች ዙሪያ በቂ ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡
በመጨረሻም በውይይት ስምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች የመምህርነት ደረጃ ኑሮት ነገር ግን ወንበር ዘርግቶ ደቀ መዛሙርትን የማያስተምር መምህር ተብሎ መጠራት እንደማይኖርበት የአብነት መምህራን ባልተመደቡባቸው ገዳማትና አድባራት እስከ አሁን እንደሚደረገው በሀገረ ስብከቱ በኩል እየተወዳደሩ እንዲመደቡ የስነ ምግባርና የሃይማኖት ህፀፅ አለባቸው ተብሎ የሚጠረጠሩ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን አስመልክቶ የሃይማኖት ህፀፅንና የሥነ ምግባር ጉድለትን ለይተው ውሳኔ ሊሰጥ ለሚችል አካል የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ የሚችሉ ሌሎችንም መንፈሳዊ ሥራዎች የሚሠሩ ብዛታቸው ከአስር ያላነሱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ከመምህራን መካከል ተመርጠው ከሀገረ ስብከቱ የትምህርት ክፍል ጋር እንዲሠሩ ለማድረግ የምርጫው ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ አስር የቤተክርስቲያን መምህራን ከተመረጡ በኋላ ስብሰባው ተጠናቅቋል፡፡
{flike}{plusone}