የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ አመራር አባላት የቦሌ ለሚ አቡነ ተክለሃይማኖትን ቤተ ክርስቲያን ጐበኙ

0087

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እና ጠቅላላ የሥራ አመራር አባላት የቦሌ ለሚ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንን ማክሰኞ ታህሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ጉብኝተዋል፡፡
ሰፈራ ጐሮ እየተባለ ከሚጠራው የከተማ ጠርዝ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኑ እስከተሠራበት ድረስ ከአራት ኪሎ ሜትር ያላነሰ ርቀት ያለው ሲሆን አካባቢው ምእመናን የሌሉበት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያኑ ህልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በማሰብ ሀገረ ስብከቱ አጣሪ ቡድን በመላክ ጉዳዩን በጥልቀት ሲመረምረው ቆይቷል፡፡
በልዑካኑ ሪፖርት መነሻነት ጠቅላላ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ሥራ አመራር ማክሰኞ ታህሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በመነሳትና ከቦታው ድረስ በመሔድ የቤተ ክርስቲያኑን ነባራዊ ሁኔታ እየተዘዋወረ ጐብኝቷል፡፡
የቦሌ ለሚ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ የ50 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ የይዞታ ባለቤት መሆኑም ይነገርለታል፡፡
የሥራ አመራር አባላቱ እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር መሰብሰቢያ አዳራሽ በጉባኤ ተሰይመው ከዋሉ በኋላ የአስተዳደር ጉባኤው እንደተጠናቀቀ በቀጥታ ወደ ቦሌ ለሚ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የጉብኝት ጉዞ በማድረግ እስከ ቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ድረስ በጾም ላይ የቆዩ ሲሆን እማሆይ አያል ፀጋው የተባሉ የቤተ ክርስቲያኑ አቃቢት በሁለት ደረቅ እንጀራዎች ቁጥራቸው አስራ ሦስት ለሚደርሱ የሀገረ ስብከቱ የሥራ አመራር አባላት ግብዣ አድርገዋል፡፡
በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የሀገረ ስብከቱ የሥራ አመራር አባላት ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጀምሮ ከግል ኪሣቸው በማዋጣት ከቦታው ለተገኙት ለአንድ ቄስ፣ ለአንድ ዲያቆንና ለአንዲት መነኩሲት የገንዘብ ርዳታ አድርገውላቸዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ታሪክ እንዲህ ዓይነቱ የሥራ አመራር አባላት ጉብኝት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን አንድ አንድ ምንጮች ይናገራሉ፡፡

0108

በሌላ ዜና በዚሁ ዕለት የሀገረ ስብከቱ የሥራ አመራር አባላት በቀጥታ ወደ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል በማምራት በካቴድራሉ በአዳሪነት መንፈሳዊ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙትን የጋምቤላ ክልልና የደቡብ ሱዳን 21 ወጣቶችን ከማደሪያ ክፍላቸው ድረስ በመሔድ የጉብኝት ተግባር አከናውኗል፡፡ ለሠልጣኞቹም የማበረታቻ ሀሳብ ተሰጥቷል፡፡ በመመገቢያ ክፍላቸውም በመገኘት ሥርዓተ አመጋገባቸውን የአስተዳደር ጉባኤው ጐብኝቷል፡፡
የሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ለወጣቶቹ አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ ማህበረ ምእመናንም ለወጣቶቹ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እያደረጉላቸው ነው፡፡ ሁለት የሕክምና ባለሙያዎች በወር ሁለት ጊዜ የወጣቶቹን ጤንነት በበጐ አድራጐት ለመከታተል ቃል የገቡ መሆናቸውን የካቴድራሉ ጽ/ቤት አብራርቷል፡፡

{flike}{plusone}