የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሠራተኞች ሙሉ መረጃ እንዲላክለት ገዳማትና አድባራት መመሪያ አስተላለፈ

640

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አሠራሩን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ እየጣረ የሚገኝ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ገዳማትና አድባራት ያለውን አጠቃላይ የሰው ኃይል በኮምፒዩተራይዝድ ሲስተም (ዳታቤዝ) መዝግቦ ለመያዝ ያመች ዘንድ በገዳማቱና በአድባራቱ የሚገኙትን ሠራተኞች ሙሉ ስማቸውን፣ የሥራ መደባቸውን፣ ዕድሜአቸውን፣ ጾታቸውን፣ የትምህርት ደረጃቸውን(በመንፈሳዊና በዘመናዊ) የአገልግሎት ዘመናቸውን፣ የሚከፈላቸውን ወርሐዊ ደመወዝ ጭምር በመግለጽ የተሻለ መረጃ በአጭር ጊዜ ለሀገረ ስብከቱ መዝገብ ቤት ገቢ እንዲሆን በቁጥር 1178/482/08 በቀን 27/03/08 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ መመሪያ ተላልፏል፡፡
ሀገረ ስብከቱ አሠራሩን ለማዘመን በማሰብ ያለውን የሰው ኃይል ከማንዋል ሲስተም ወደ ኮምፒውተራይዝድ ሲስተም (ዳታቤዝ) በመቀየር ላይ መሆኑን እና ይህም ሒደት ከሁለት ዓመታት በፊት ባዘጋጀው ድህረ ገጽ በስሩ የሚገኙ ገዳማትና አድባራት የሚያከናውኑትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራ ለሕዝብ በማሠራጨትና በማሳወቅ ላይ የሚገኝ መሆኑ በደብዳቤው ተብራርቶ ተገልጿል፡፡
ከሠራተኞቹ መረጃ በተጨማሪ በካቴድራሎች፣ በገዳማትና በአድባራት ከአሁን በፊት የሥራ ላይ የዋለ ድህረ ገጽ ካለ ሙሉ አድራሻውን ተገልጾ እንዲላክ፣ በቪዲዮም ሆነ በኦዲዮ እንዲሁም በጽሑፍ በድህረ ገጹ ላይ የሚጫኑ ወይም የሚለቀቁ ዜናዎች፣ መልእክቶችና በትምህርተ ሃይማኖት ላይ የተመሠረቱ መንፈሳዊ መልእክቶች ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከተው አካላት ዕውቅና ሳያገኙ በአየር ላይ እንዳይውሉ በጥብቅ ተከልክሏል፡፡
ካቴድራሎቹ፣ ገዳማቱና አድባራቱ በጽ/ቤታቸው ድህረ ገጽ ለመክፈት ሲፈልጉ ለሀገረ ስብከቱ ፕሮጀክት ፕሮፓዛል አቅርበውና ሙሉ ዲዛይኑ አፀድቀው ድረ-ገጽ መክፈት የሚችሉ ሲሆን ከዚህ ውጭ ግን የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይገባቸው ሀገረ ስብከቱ በመመሪያው ላይ አስምሮበታል፡፡
በ2008 ዓ.ም በጥቅምት ወር የተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤም ሳይፈቀድላቸው በቪድዎም ሆነ በኦድዮ፣ በቴሌቭዥንም ሆነ በተለያዩ የጽሑፍ ሕትመቶች ስርጭት የሚአደርጉ ክፍሎች በሕግ እንዲጠየቁ ውሳኔ ማስተላለፉ ይተወቃል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየካቴድራሎች፣ በየገዳማትና በየአድባራት የሚገኙ አጠቃላይ የሠራተኞችን መረጃ መሰብሰብ ያስፈለገበ ዋና ዓላማ፡-
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ”… የራሴን በጎች አውቃለሁ፣
የራሴን በጎች ያውቁኛል … ድምጼንም ይሰማው፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ”፡፡ (ዮሐ. 10÷15-16) በማለት እንዳስተማረን ሁሉ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም
የቤተ ክርስቲያንዋን ቋሚ ሠራተኞች ለይቶ ለማወቅ፣ ሠራተኞቹ በሚደርስባቸው ማንኛውም ድንገተኛ ችግር ጊዜ ሀገረ ስብከቱ ለሠራተኞቹ አስፈላጊውን ትብብር ለመስጠት፣  ሠራተኞቹ ባቀረቡት መረጃ መሠረት ወደተሻለ የሥራ እድገት ከፍ ለማድረግ እንዲቻል እና የሠራተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር፣ ሠራተኛ ሳይሆኑ ሠራተኛ በመምሰል የሚንቀሳቀሱ ክፍሎችን ለመለየትና  ለመሳሰለው ተግባር እንዲረዳ ለማድረግ ነው፡፡
ካቴድራሎች፣ ገዳማትና አድባራት ሀገረ ስብከቱ የዘረጋውን ዘመናዊ ቀልጣፋና አስተማማኝ የመረጃ አያያዝ እንቅስቃሴን በመደገፍ የተጠየቁትን መረጃ በወቅቱና ጥራት ባለው አሠራር፣ እንዲሁም ታማኝነት ባለው ሁኔታ መረጃዎቹን ለሀገረ ስብከቱ መዝገብ ቤት ማድረስ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ 

{flike}{plusone}