አ/አ/ሀ/ስብከት“የሕጋዊነት መርሕ”በሚል ርእስ ለገዳማትና አድባራት የሥራ መሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥናታዊ ውይይት አካሄደ
በመ/ር ሣህሉ አድማሱ
ሀገረ ስብከቱ ሰኔ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ከገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ሒሳብ ሹሞች ጋር የሕጋዊነት መርሕ በሚል ርእስ ለግማሽ ቀን የቆየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥናታዊ ውይይት አድርጓል፡፡የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ በውይይቱ መክፈቻ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት በአሁኑ ጊዜ ሀገረ ስብከቱ ሆስፒታል ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሆስፒታል በየቀኑ በሽተኞች ይታዩበታል እና ነው፡፡ ባለ ጉዳዮቹ ሥራ አስኪያጁን ማግኘት አልቻልንም በማለት ያማርራሉ፡፡ በየደረጃው ያሉ የሥራ ሐላፊዎች ባለጉዳዮችን በአግባቡ ማስተናገድ አለባቸው፡፡ ጉዳዩንም በወቅቱ መፈጸም አለባቸው በማለት አብራርተዋል፡፡
የመወያያ ጥናቱን ያቀረቡት የሀገረ ስብከቱ የሕግ ክፍል ሐላፊ መምህር ባሕሩ ተፈራ ባቀረቡት የመወያያ ጥናታዊ ዝግጅት ቤተ ክርስቲያናችን የሕግ ምንጭ ለመሆኗ ምሁራን ይመሰክራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ፍትሐ ነገሥትን ቀርፃ ትውልድን ስታስተምር ቆይታለች፡፡ ሕገ መንግሥቷም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው ሕግ እየቀረጸ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ አሁን እየሰጠ ይገኛል፡፡
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ብትርክና የቃለ ዐዋዲ ሕግ ተቀርጾ ቤተ ክርስቲያናችን በዚሁ ሕግ አገልግሎት እየፈጸመች ትገኛለች፡፡ በዓለም ላይ ሕግ አስፈላጊ ነው፡፡ ፈላስፋዎች ሰው በማኅበራዊ ኑሮ የሚኖር እንስሳ ነው ይላሉ፡፡ ለአንድ ኅብረተሰብ ሕግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዲሞክራሲና በነፃነት ላይ የተመሠረተ ሕግ የሠሩ ምሁራን ቢኖሩም አጠቃላይ ሰውን ነፃ ሊያወጣ የሚችል ሕግ ግን አላወጡም፡፡ ሕግ አስፈላጊ ሰይጣን ነው የሚሉ አሉ፡፡ ምክንያቱም ሕግ ስለሚቀጣ ነው፡፡ የሕግ ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ከ335 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ “ከእሱ በበላህ ጊዜ ሞትን ትሞታለህ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አጠቃላይ የዓለም ሕጎች ተመሥርተዋል፡፡ አድርግ የተባለውን አለማድረግ፣ አታድርግ የተባለውን ማድረግ ያስቀጣል፡፡ የሕግ አላማ የሰው ልጅ በፈጣሪና በሰው መካከል ያለውን ኅብረት መጠበቅ ነው፡፡
ዋናው ጉዳያችን በሀገረ ስብከታችን ስር ያሉት የአስተዳደር ሕጎች ምን መምሰል አለባቸው? የሕግ መርሕ የአስፈልገናል፡፡ የአስተዳደር ሕግ አስተዳዳሪዎች በሕጉ የተሰጣቸውን ሕግ ተከትለው እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ ፍትሕን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ በአንድ ሀገር ሕገ መንግሥት እንደሚፈጸም ሁሉ እኛም የእግዚአብሔርን ሕገ መንግሥት ማስፈጸም ይኖርብናል፡፡ ዓለምን መምራት የሚችሉ አስተዳዳሪዎች እንዳሉ ሁሉ እንዴት እንዴት ተሾሙ የሚያሰኙ እና ቃለ ዐዋዲን የማያውቁ አስተዳዳሪዎችም አሉ፡፡
የአስተዳደር ተግባራት ሥልጣንን ያለ አግባብ አለመጠቀም፣ ከሥልጣን በላይ አለመሄድ፣ የሥልጣንን እርከን አለመተላለፍ፣ የፈለገውን አለመጣል፣ የፈለገውን አለማንሣት ነው፡፡ ተሰፍሮ እና ተለክቶ የሚሰጥ ስልጣን ያስፈልጋል፡፡ የሕጉ መኖር ጉዳት የደረሰበትን ሠራተኛ ፍትሕ ያመጣል፡፡ ነገር ግን ተሰፍሮ እና ተለክቶ የተሰጠ የሥልጣን እርከን ስለሌለ ከሥልጣን ዘለን እንድንወጣ አድርጎናል፡፡ ለተበደለ ወገን ፍትሕ መስጠት ይገባል፡፡ የሚታየው ሁኔታ ግን የሚሠሩ ይበደላሉ፣ የማይሠሩ ደግሞ በነፃነት ይኖራሉ፡፡ ትችትን መፍራት ሥራን አለመሥራት ነው፡፡ የባለሥልጣን ዘመድ ነው እየተባለ እስከ መቼ ድረስ ነው እንዲአይነቱ የተበላሸ አሠራር የሚቀጥለው? ሥራ ሳይሠሩ ደመወዝ የሚያገኙ አሉ፡፡
ሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ሀገረ ስብከት በመሆኑ እና የበርካታ ምሁራን ካህናትና ምዕመናን መገኛ በመሆኑ ከሌሎቹ አህጉረ ስብከት ልዩ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ለሌሎቹ አህጉረ ስብከቶች ምሳሌና አርአያ ልንሆን ይገባናል፡፡ በአጠቃላይ የሰበካ መደበኛ ጉባኤ ጊዜ ትኩረት የሚሰጠው የፐርሰንት ሪፖርት ነው፡፡ እድገት ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሆዱ ብቻ እየገፋ እግሩ የሚቀጭጭ ሰው አደገ አይባልም፡፡ በሰላም፣ በአስተዳደር እና በደመወዝ ማደግ አለብን፡፡ ሐላፊነት በሥራ አስኪያጁ ላይ ብቻ መውደቅ የለበትም፡፡ እኔና የሥራ ባልደረቦቼ ሠራን ማለት ነው እንጂ የሚገባን እከሌ ሠራ ማለት አይገባንም፡፡
ጥናቱ የቀረበበት ምክንያት ቅጥር፣ እድገት፣ ሽግሽግ እና ማሰናበትን ለማስተካከል ይቻል ዘንድ ነው፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ የሚመጡ ባለ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሥራ አስኪያጁ ከቢሮ ውስጥ መሆናቸውን ከሰሙ እሁድና ቅዳሜም የሚመጡ ባለጉዳዮች አሉ፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቅጥር በፈተና ብቻ እንዲሆን ቃለ ዐዋዲ ይደነግጋል፡፡ በአንዳንድ ገዳማትና አድባራት ቅጥር ይፈጸምና እንደ አጋጣሚ ከአራት፣ ከአምስት ወይም ከስድስት ዓመት በኋላ አስተዳዳሪው ሲነሣ ሌላ አስተዳዳሪ ቅጥረኛውን ሕጋዊ አይደለህም በሚል ያሰናብተዋል፡፡ ያ የተሰናበተ ሠራተኛ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ይከሳል፡፡ በዚህ አሠራር ፍ/ቤቶች እኛን እያማረሩ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ በአዳዲስ ሥራ ፈላጊዎች ሲጨናነቅ ይውላል፡፡ ሥራን የምናስንቅም የሥራ መሪዎች እንኖራለን፡፡ አንድ ሰው በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም ሲለይ ገና ጸሎተ ፍትሐት እየተደረገለት በአለበት ሁኔታ የቅጥር ደብዳቤ ይጻፋል፡፡ ቅጥር በማስታወቂያ አለመሆኑም ችግሩን አባብሶታል፡፡ ዕድገት አንድ ሠራተኛ ብቁ ሆኖ ሲገኝ ያድጋል፡፡ መብታችንን በብር መግዛት የለብንም፡፡ መብት ይጠየቃል እንጂ በብር አይገዛም፡፡ በዚህ መንገድ የተቀጠሩ፤ ሠራተኞችም ባቅም ማነስ ለሥራው ዕንቅፋት ይሆናሉ፡፡
የምሥክር ወረቀት አቅርበው ሰማይ ብልጭ ቢል በስመአብ የማይሉም አሉ፡፡ በዚህ አሠራር የመልካም አስተዳደር ፀሐይ ሊመጣ አይችልም፡፡ ተራርመን ሥራችንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ መነጋገርና መተሳሰብ አለብን፡፡ ትክክለኛ ሰው በትክክለኛ ቦታ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
በቃለ ዐዋዲ እንደተደነገገው ዝውውር ግዴታ ቢሆንም ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የሥራ ደረጃ፣ ደመወዝ፣ የመኖሪያ ሠፈር ታሰቢ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ነገር ታሳቢ ከሆነ ማገድና ማሰናበት የሀገረ ስብከት የቤት ሥራ ከዚህ ላይ ነው ያለው፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 12 ቃለ ዐዋዲ አንቀጽ 60 ላይ ማንኛውም ሠራተኛ ሠርቶ ደመወዝ ማግኘት ይገባል ይላል፡፡ ደንቡን ቢተላለፍ እንደጥፋት ደረጃ በደረጃ ነው ሊዛወር እና ሊታገድ ሚችለው፡፡
የመጨረሻው ውሳኔ የሚጸናው በሀገረ ስብከቱ ነው፡፡ በገዳማትና በአድባራት በአንድ ወር ውስጥ እስከ 25 ሠራተኛ ይታገዳል፡፡ ይህ አሠራር በሀገረ ስብከታችን የአሠራር ችግር ያለ አስመስሎታል፡፡ ሀገረ ስብከቱ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ያስፈጽማል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጠው ውሳኔ እንደ ሕግ ሆኖ ያገለግላል በማለት መምህር ባሕሩ ተፈራ በመረጃ የተደገፈ ጥናታዊ ዝግጅት አቅርበዋል፡፡
የተለያዩ አስተያት ሰጪዎችም በሰጡት አስተያየት ሀገረ ስብከቱ ጥያቄዎችን በወቅቱ ሊፈጸምልን ይገባል፡፡ በሀገረ ስብከቱ መልካም አሠራሮች ይታያሉ፡፡ በቀረበው ጥናታዊ ዝግጅት መሠረት መሥራት ቢቻል ብዙ ሰዎች ከችግር ይድናሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ የሚመጣው ከታች ነው፡፡ ነገር ግን ሀገረ ስብከቱ የማስታረቅ ተግባር ሊሠራ ይገባል፡፡ ችግር እየተፈጠረ ያለው የሕግ አለመጻፍ አይደለም፡፡ ቃለ ዓዋዲው የተሻሻለው ከምን ላይ ነው? እስከመቼ ድረስ ተሸፋፍነን እንኖራለን? ዘመኑ የሚጠይቀውን አሠራር ልንከተል ይገባናል፡፡ ሰላም የሚአመጣ አመራር መስጠት የመሪው ድርሻ ነው፡፡ የመሪዎች ብቃት ሊፈተሽ ይገባል፡፡ በማለት ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎ የዕለቱ የጥናታዊ ውይይት ስብሰባው ተጠናቋል፡፡