የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ በመካኒሳ ምዕራፈ ጻድቃን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ካቴድራል በመገኘት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴንና የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በዛሬው ዕለት ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥር በሚገኘው በመካኒሳ ምዕራፈ ጻድቃን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ካቴድራል በመገኘት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴንና የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝት መርሃግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰው ኃይል አስተዳደር መ/ር አይናለም ተጫኔ፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ፣ የካቴድራሉ ዋና ጸሐፊ መ/ር እዝራ ንዋይ፣የካቴድራሉ ሰባክያነ ወንጌል፣ የካቴድራሉ ካህናትና ዲያቆናት፣ዘማሪ ዳግማዊ ደርቤ እንዲሁም በርካታ ምእመናን የተገኙ ሲሆን በመምህራን ስብከተ ወንጌል በሰፊው ተላልፏል።
ካቴድራሉ በስብከተ ወንጌል ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን፣ ዘወትር አርብ በካቴድራሉ አዳራሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለምእመናን እንደሚሰጥ፣እሁድና ረቡእ ሳምንታዊ ታላቅ ጉባኤ እንደሚካሄድ፣በየወሩ ብሮሸር(በራሪ ወረቀት) እየታተመ ለምእመናን እንደሚሰራጭ፣በሶስት ወር አንድ ጊዜ መጽሔት እየታተመ ወደ ምእመናን እንደሚደርስ የካቴድራሉ ጸሐፊ መ/ር እዝራ ንዋይ ገልጸውልናል።
አያይዘውም የካቴድራሉ ቢሮዎች ኮምፒውተር ያላቸውና ዋይፋይ የተገጠመላቸው መሆናቸውን፣ ዩቲዩብ ተከፍቶ የካቴድራሉን የወንጌል እንቅስቃሴ በውጪና በሀገር ውስጥ ያሉ ምእመናን በቀላሉ እንደሚከታተሉ፣ ካቴድራሉ የአብነት ትምህርት መዋቅራዊ መመሪያ ፕሮጀክት መንደፉንና ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑን፣ ካቴድራሉ በአሠራሩ የዘመነና ዘመኑን የዋጀ ሥራ እየሠራ ከመሆኑም ባሻገር ለሌሎች አድባራትና ገዳማት አርአያ መሆኑን አብራርተውልናል።
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ስለ ምእመናኑ ወንጌል ወዳድነት፣ምእመናኑ በልማት ሥራ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦና በካቴድራሉ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን አብራርተው ገልጸዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ” በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ ” (የማቴዎስ ወንጌል 16:18) በሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ ተነስተው ትምህርተ ወንጌልን ለምእመናን አብራርተው አስተላልፈዋል፤ አያይዘውም የቤተክርስቲያን መሠረትና ክብር ኢየሱስ ክርስቶስን አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ማመንና ማስተማር እንደሆነ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ ጸሎት ተደርጎ መርሃግብሩ ተፈጽሟል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ