የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የአባዶ ገነት አምባ ቅዱስ ሚካአል ቤተ ክርስቲያን ጐበኙ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከሚአስተዳድራቸው ገዳማት፣ አድባራትና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት መካከል በየካ ክፍለ ከተማ የአባዶ ገነት አምባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው፡፡
የአባዶ ገነት አምባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባ በየካ ክፍለ ከተማ በኦሮሚያ ዳሌ በሰላሌ ግዛት ድንበር ላይ የተመሠረተ ሲሆን ከኮተቤ የከተማ መዳረሻ እስከ አባዶ ገነት አምባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ድረስ ከሦስት ኪሎ ሜትር ባላነሰ አጭር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ ከተመሠረተ አስራ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ነባሩን ቤተ ክርስቲያን በአዲስ ሕንፃ ለመተካት የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ እየተከናወነ የሚገኝ በመሆኑና ቤተ ክርስቲያኑ ከከተማው ወጣ ባለ ገጠራማ አካባቢ ላይ በመሠራቱ አብዛኛውን ጊዜም ምዕመናኑ የማይገኙበት በመሆኑና በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ የሚገኘው ሰፊ የቤተ ክርስቲያኑ ይዞታ ምን እንደሚመስል በጥልቀት ለመረዳትና ለማወቅ ሲባል የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ከሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ዋና ክፍል ኃላፊ ከሆኑት ከሊቀ መዘምራን ብርሃኑ ጌጡ ጋር በመሆን ሐሙስ ታህሳስ 21 ቀን 2008 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ከቦታው ድረስ በመሔድ የጉብኝት ሥራ አከናውነዋል፡፡
የአባዶ ገነት አምባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የይዞታ ቦታ ከ30 ሺህ ካሬ ሜትር ያላነሰ መሆኑን ከቦታው ያገኘናቸው የቤተ ክርስቲያኑ የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙሉጌታ አብራርተዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ መቆርቆር በፊት
በሽተኞችን በመፈወስ የሚታወቀውና ባህረ ዮርዳኖስ እየተባለ የሚጠራው የቅዱስ ሚካኤልና የቅድስት አርሴማ ፀበልም በአሁኑ ጊዜ በስኳር በሽታ፣ በኤች አይ ቪ ኤድስና በክፉ መንፈስ የተያዙ በሽተኞች እየተፈወሱ መሆናቸውን የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ገልጸዋል፡፡ በሽተኞቹን የሚያጠምቃቸው ካህን አለወይ ብለን ጥያቄ ያቀረብንላቸው የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ራሱ ቅዱስ ሚካኤል በተአምር በሽተኞቹ እንዲፀበሉ እያደረገ ከመሆኑ ውጭ አጥማቂ ካህን የለም ብለዋል፡፡ የግንባታ ሥራው እየተፋጠነ የሚገኘው የህንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሥራ አስመልክቶ አስተዳዳሪው ሲገልጹ የሕንጻውን ግንባታ የሚከታተለው ባለሙያ አቶ ወንድወሰን ተመስገን የተባለ ግለሰብ ሲሆን ሌት ተቀን የግንባታ ሥራውን የሚአከናውነው ያለምንም ክፍያ ነው፡፡
ይህም ሊሆን የቻለው ካለበት በሽታ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በፀበሉ ስላዳነው ነው ያሉት አስተዳዳሪ በጉልበታቸው የወዛደርነት ሥራ የሚሠሩት ሁሉ በበጐ አድራጐት እንጂ ምንም አይነት ክፍያ አይፈፀምላቸውም፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ምዕመናን ከሩቅ አካባቢ በአህዮቻቸው ውኃ እየጫኑ በነፃ ያገለግላሉ፡፡
የአባዶ ገነት አምባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከመሬት ከፍ ያለ ሲሆን አየር ንብረቱ ወይና ደጋማ ነው፡፡ በአካባቢው የሚነፍሰው የምሕረት ነፋስ ልብን ይመስጣል፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ በቅዱሱ ተራራ በደብረ ታቦር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ሲገልፅ በተሰማው መንፈሳዊ ሐሴት የተነሳ “ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ፈቃድህ ከሆነ አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ” (ማቴ. 17÷4) እንዳለው ሁሉ በዚህ ኮረብታማና ተራራማ ቦታ ላይ መዋልና ማደር መንፈስን የሚያድስ እስኪመስል ድረስ የአካባቢው ውበት ታይቶ አይጠገብም፡፡ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ የተዋቀሩት የአካባቢው የደን ዛፎችም ልብን የሚመስጥ መልካም መዓዛ ያመነጫሉ፡፡ በዚህ ቦታ ሱባኤ ገብቶ ጸሎት ማድረግን ያስመኛል፡፡
በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ ዳገቱንና ቁልቁለቱን፣ ሜዳውንና ጠመዝማዛውን መንገድ እየተመላለሱ የጉብኝት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የነበሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ ባዩአቸውና በተመለከቱአቺው ሎኬሽኖች የተሰማቸውን መንፈሳዊ ደስታ በገለጹበት ወቅት በዚህ ቤተ ክርስቲያን የምታገለግሉ ሁላችሁ ሥራችሁን ያሳካላችሁ! እኛም በቻልነው ሁሉ እንተባበራለን፡፡
ይህ የተፈጥሮ ደን መጠበቅ አለበት፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ሀብት የሆነው በአጥር መለየት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ቦታ ስላየሁት መልካም ነገር ሁሉ ተደስቼአለሁ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡