የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን አዲሱን ዓመት አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ
ከሁሉ በፊት ባንድነትና በስምምነት ጠብቆ ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ (2007 ዓ.ም) ያሸጋገረን አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡
በመቀጠልም ሕዝበ ክርስቲያኑን እንኳን ለ2007 ዓ.ም አዲሱ ዓመት አደረሳችሁ እላለሁ፡፡
አዲሱ ዘመን የሰላም፣የአንድነት፣የፍቅርና የብልጽግና ዘመን እንዲአደርግልን እየተመኘሁ በ2006 ዓ.ም የተሠሩ ሥራዎችን በመገምገም ማለትም በቢሮም ሆነ በተናጠል ምን ሠራሁ? ምን አቅጄ ነበር? ምንስ አሣካሁ? ያላሳካሁትስ ምንድነው? የገጠመኝ ፈተናስ ምንድነው? የገጠመኝ ፈተናስ እንዴት ተወጣሁት? ያልተወጣሁት ካለ ደግሞ ለምንድነው ያልተወጣሁት? ብሎ መገምገም ይህ ሕይወት ነው፡፡ ሰዎች ራሳቸውን ባስተሳሰብ ለውጠው ውጤት ከላሳዩ በስተቀር ዘመን ተለወጠ ቢባል ትርጉም አይኖረውም፡፡ ያለፈው ሕይወታችን የሥራ ጊዜአችንን ከገመገምን በኋላ በቀጣዩ 2007 ዓ.ም የምንሠራውን ሥራ ልናቅድ ይገባናል፡፡
ለእቅዳችን መነሻው ያለፈው ሥራ ነው፡፡ ማለትም ያሳካነውና ያላሳከነው ነው፡፡ ምን አልባት ሳናቅድም ያከናወናቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ እንዲዚሁም ሳንገምተው የሚገጥሙን ችግሮች ይኖራሉ፡፡
ስለዚህ ዓለም በፈተና የተሞላች ስለሆነ ከዓለም ችግር ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ወደፊትም ችግር ሊመጣ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ችግር ሲከሰት በመደናገጥ ማሳካት የሚገባውን ሥራ ቸል ማለት አይገባም፡፡ ሕይወትን አስከማጣት ሊደርስም ይችላልና፡፡ በተለይም ወደራሳችን ሕይወት ስንመለከት ክርስትናችን እንዴት ነው? እኛ የዘለዓለምን ሕይወት ለመውረስ የሚአበቃ ተግባር ሠርተናልን? ድነናልን ብለን ራሳችንን መፈተሸ ይገባናል፡፡ የሥጋ ኑሮአችንን ስናስተካክል ከዚህ ጋር ጎን ለጎን ስለሕይወታችን ማሰብ አለብን፡፡ በተለይም ካህናት የበለጠ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ስለሆነ የሌላውን ሕይወት ማስተካከል አለባቸው፡፡ በመጨረሻም ወደ ሀገረ ስብከታችን ስንመለስ በ2007 ዓ.ም በርካታ እቅዶችን አቅደናል፡፡ ይህ እቅድ ዱሮ በነበረው ሁኔታ ሳይሆን ማለትም ባለጉዳዮችን ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን የልማት ሥራዎችን እንደ ህንጻ መገንባት እና የመሳሰሉት በመስራት ነው፡፡ አዲሱን ዓመትም በተመለከተ የማስተላልፈው መልእክት በእስር ቤት፣የሚገኙ ወገኖቻችንን እግዚአብሄር በሰላም እና በጤና ጠብቆ የእርምት ጊዜአቸውን ጨርሰው በሰላም ወደቤታቸው እንዲመለሱ፣ በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ የተኙትንም አረጋውያን እና ወጣቶችን እግዚአብሔር ይፈውስልን፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚጓዙ መንገደኞችንም ጉዞአቸውን ያቀናላቸው፡፡ በግብርናም ሆነ በንግድ ሥራ የተሠማሩትን ዜጎቻችን ሁሉ አምላካችን እግዚአብሄር ይጠብቅልን ሥራቸውን ይባርክልን፡፡ ቤተክርስቲያናችንንም ይጠብቅልን፡፡
የ2007 ዓ.ም አዲሱ ዘመን የሰላም የብልጽግና፣የስምምነት የምቾት እና የበረከት ዘመን እንዲሆንልን እየተመኘሁ የሕዝብ አገልጋይ የሆኑ በመንግሥትም ሆነ በሌላ ማንኛውም የሥራ ኃላፊነት ወገኖቻችን በትክክል ማገልገል እንዲችሉ እና ሕዝብ የሚረካበትን ሥራ እንዲሠሩ እግዚአብሔር ከእሱ ጋር እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም ጤናማ አስተዳደር እንዲኖረው፣ ባለጉዳዮችም እንዳይጉላሉ ምንም እንኳን የጠየቀው ሁሉ ያገኛል ተብሎ ባይገመትም፡፡ ነገር ግን ባለጉዳዩች ለጥያቄአቸው መልስ ማግኘት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ የተወሰኑ ሥራዎችም ወደ ክፍለ ከተማ ወርደው እንዲሠሩ እየታሰበ ነው፡፡
ሰላምን በተመለከተ ካለፉት ዘመናት አሁን የተሻለ ነው፡፡ ወደፊት ከዚህ የበለጠ የተሻለና የተስተካከለ አስተዳደር እንዲኖርና ለብዙ ጊዜ የተጠራቀሙት ችግሮች እንዲወገዱ ይደረጋል የሚል እምነት አለን፡፡ ይህንንም ለማድረግ እንድንችል አምላካችን እግዚአብሄር ይርዳን፡፡
{flike}{plusone}