የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ክርስትና ካልተስፋፋባቸው ብሔር ብሔረሰቦች ካህናትን ለማፍራት እየሠራ ነው

000340
ፎቶ ፋል

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ክርስትና ያልተስፋፋባቸው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ለማስፋፋት ከየብሔረሰቡ ካህናትን ለማፍራት ተግቶ እየሠራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እንደገለፁት ከጋምቤላ ክልል 18 ከደቡብ ሱዳን 3 ደቀመዛሙርትን መልምሎ ከትውልድ አካባቢያቸው ድረስ ሄዶ በማምጣት በአዲስ አበባ ከተማ በሰዓሊተ ምሕረት ቅድስተ ማርያም የአብነት ት/ቤት በአደራነት አስገብቶ እያስተማረ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ለሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪ በቅርቡ ከስልጤ ብሔረሰብ፣ ከቤንንሻንጉል ጉሙዝ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦችና ከኩናማ ብሔረሰብ በርካታ ታዳጊዎች በማምጣት መደበኛ ትምህርት በአደራነት እንዲማሩ የሚደረግ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በብዙ መመዘኛ የሊቃውንት ችግር የሌለበት ቢሆንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበት ሐዋርያዊ ዓላማ እንዲሳካ በየብሔረሰቡ ወንጌልን የሚያስፋፉ መምህራንና ካህናትን ማፍራት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ሀገረ ስብከቱ ለዚህ ሥራ ትኩረት መስጠቱን አስረድተዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ ከየብሔረሰቡ አምጥቶ ለሚያስተምራቸው ደቀመዛሙርት በጀት መመደቡንና የደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ካቴድራል ሰበካ ጉባኤም ከፍተኛ ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልፀው የካቴድራሉ አስተዳደር በዚህ በኩል ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልፀው አመስግነዋል፡፡

{flike}{plusone}