የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሰባክያን ጋር ውይይት አደረገ

                                                                    በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

የሀገረ ስብከቱ የሥራ መሪዎች ከገዳማትና አድባራት አስተዳዳረዎችና ሰባክያነ ወንጌል ጋር “የስብከተ ወንጌልና የሚድያ አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን ያለው ሚና” በሚል ርእስ መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ/ም በሀገረ ስብከቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለግማሽ ቀን የቆየ የምክክርና የውይይት መርሐ ግብር አካሂደዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ሂደት ላይ ሰፋ ያለ ትምህርታዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ጳጳስ ስለስብከተ ወንጌል ምንነት ሲገልጹ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ የሕይወታችን አካል ፣ያገልግሎታችን መሠረት ነው፡፡

ለሁለት ሺህ ዓመታት ወንጌል የተዘራባት ፣በተዘራው መልኩ ውጤቱን በፍሬው መገምገም የቻልንበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡

ስብከተ ወንጌል በቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ማንነት ትልቅ ሚና አለው፡፡ስብከተ ወንጌል ለቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ጥንካሬ ፣ለምዕመናን ሕይወት መሠረት መሆኑን ፣ስብከተ ወንጌል ትእዛዘ እግዚአብሔር መሆኑን ፣ይህም በመሆኑ ለስብከተ ወንጌል ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ፣የእግዚአብሔር ቃል ያልገራውና ያልተቆጣጠረው ህሊና ለእግዚአብሔርም ለሰውም የማይመች መሆኑን በመግለጽ ብፁዕነታቸው ጥናታዊ በሆነ አቀራረብ ሰፋ የለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ይቅር ባይ እንዳለ አክለው እንደገለጹት የስብከተ ወንጌል ጉዳይ ከቀን ወደቀን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ፣ቢፅ ሓሳውያን አስተሳሰብን የሚያራምዱ ኃይሎች በቤተ ክረርስቲያን መሰግሰጋቸውን ፣የቅዱሳኑን ስም የመጥራት ፍላጎት የማያሳዩ መሆናቸውን ፣በክብረ በዓላት የሚታየው ከፍተኛ የምዕመናን ቁጥር በሌላ አካሄድ ሲታይ እየቀነሰ ያለ መሆኑን ፣የስብከተ ወንጌል ሙያ የሚያጥራቸው ግለሰቦች የሚሰጡት ትምህርት ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑን ፣ለስብከተ ወንጌል ሥራ የሚበጀተው በጀት አናሳ መሆኑን ፣ የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ዓላማ ስብከተ ወንጌል መሆኑን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አብራርተዋል፡፡

ተሰብሳቢዎችም የተሰጠውን ማብራሪያ በመከተል በገዳማቱና በአድባራቱ የሚመደቡ የወንጌል መምህራን የሙያ ችሎታቸው ፣ሃይማኖታዊ አቋማቸው ሊፈተሽ የሚገባው መሆኑን ፣በሀገረ ስብከቱ መጽሔትና ጋዜጣ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች ኦርቶዶክሳዊ ይዘት እንዲኖራቸው በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እየታዩ እንዲታተሙ መደረግ የሚገባቸው መሆኑን ፣ከዚህ ቀደም መጋቢት ወር ላይ የታተሙት መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ የታዩት ግድፈቶች እርማት እንዲደረግባቸው ወዘተርፈ የሚሉ ሓሳቦች በስፋት ተተንትነዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ በ2011 ዓ/ም የበጀት ዓመት በሚከራየው የቴሌቭዥን አየር የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን በማለት ከተሰብሳቢው ገንቢ የሆነ ሐሳብ ከተሰጠ በኋላ የስብከተ ወንጌሉንና የሚድያውን እንቅስቃሴ የሚያጠናክሩ ስምንት ኮሚቴዎች ማለትም፡-

  1. ሊቀ ኅሩያን ሰርፀ አበበ
  2. መጋቤ ሐዲስ ኀይለ እግዚእ
  3. መልአከ ብርሃን ክብሩ ገ/ፃድቅ
  4. ሊቀ ብርሃናት ቀሲስ ተ/ማርያም
  5. መልአከ ፀሐይ ደሳለኝ
  6. መጋቤ ሥርዓት ወንድወሰን
  7. በኩረ ትጉሃን ደሳለኝ ቶጋ
  8. መጋቤ ሚስጢር ቀለመወርቅ በምልአተ ጉባኤው ከተመረጡ በኋላ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡