“የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባለፈው በጀት ዓመት ከ፰ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፐርሰንት ማስገባቱን አስታወቀ

በተጨማሪም ፪፻፳፭ ሠራተኞችን በመመደብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅዱስ ሲኖዶስ ለተፈናቃዮችና ቤተሰቦቻቸውን ዕረፍት በሚሰጥ መልኩ የተፈናቃይን ምዕራፍ ለመዝጋት ተችሏል” ብሏል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሪፖርት
ጥቅምት ፮/፳፻፲፰ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ሦስተኛ ቀኑን የያዘው 44ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በመልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት ቀርቧል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚመራው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የ2017 ዓ/ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ነው፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በስሩ ስምንት ክፍላተ ከተማ ያለው ከ250 በላይ አብያተ ክርስቲያናት ከሃምሳ ሺህ በላይ አገልጋይ ካህናትና ሠራተኞችን ያቀፈ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታይ ያሉባት ፣ ርእሰ መንበሯም ደገኛውና መናኙ የጸሎት አባት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ የሆኑላት ከአራቱ ማዕዘን የሚመነጨውን መጠነ ሰፊ ፍላጎት እንደ ሁኔታው በመያዝና ምላሽ በመስጠት የሚታወቁት የአስተዳደር ጥበብ ከፈጣሪ በተቸራቸው በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀገረ ስብከታችን ሊቀጳጳስ በሳል አመራር እየተመራ ቀን ከሌሊት በመሥራትና በማሠራት የተመዘገበውን ውጤት በአግባቡ የሚገልጥ ዘገባ ቀደም ሲል ከላክነው ሪፖርት ላይ መካተቱ ታሳቢ ሆኖ በሀገረ ስብከቱ የተከናወኑ ችግር ፈች የሆኑና ዘመኑን የዋጁ ዘርፈ ብዙ በርካታ ተቋማዊ ተግባራትን ከብዙ በጥቂቱ እነሆ ብለናል ፡-
የቢሮ እድሳትን በሚመለከት
ላለፉት 17 ዓመታት ምንም ዓይነት እድሳት ሳይደረግለት ቆይቶ እርጅና የተጫጫነውን የሀገረ ስብከቱን ሕንፃ በልማታዊው አባት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አማካኝነት አንድ በጎ አድራጊ ምእመን በማስተባበር የውስጥ ክፍሉን በአዲስ ዲዛይን በመቀየስ ዘመኑን የዋጀና በቴክኖሎጂ የበለጸገ የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ከፍ አርጎ በሚያሣይ መልኩ ጥገናና የውስጥ እድሳት ከተደረገለት በኋላ በብፁዕ አባታችን አቡነ ሕርያቆስ ጋባዥነት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባርከው ጎብኝተዋል ።
በተጨማሪም ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ፤ ብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ሥራ አስኪያጅና የመምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች በተገኙበት በይፋዊ ጉብኝት መልክ ተመርቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡:
ከዚህ በተጨማሪ የሀገረ ስብከቱ ሕንፃ ውጪው በከተማ ማደስ መርሐ ግብር ስለታደሰ ግቢው ደግሞ በአስፋልትና ልዩ ልዩ ተቋማዊ ልማት በዘመናዊ መልኩ ተሠርቷል፡፡
መልካም አስተዳደርን በሚመለከት
በተለያዩ ምክንያት ከመደበኛ ሥራቸውና ደመወዛቸው ተፈናቅለው የነበሩና ጉዳያቸው በቅ/ሲኖዶስ ደረጃ ተይዞ አጀንዳና መነጋገሪያ የነበረው የሀገረ ስብከቱን መልካም ስምና በጎ ገጽታ ያጎደፈውና ለተቋማዊ ሥራ ማነቆ ሆኖ የቆየው ይህው አጀንዳ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ተፈናቃዮች ከአፋቸው ላይ የተነጠቀ እንጀራቸውን ለማስመለስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት፤ በየፍ/ቤቱ በየመንግሥት መ/ቤቶች ፍትሕ እናገኝበታለን ብለው ባመነበት ቦታ ሁሉ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው እሙን ነው፡፡
ይህንን መራራና አሰቃቂ ክስተት ለመፍታትና እንባቸውን ለማበስ ከሥራዎች ሁሉ ለቅዱስ
ሲኖዶስ ውሳኔና ለተፈናቃዮቹ ቅድሚያ በመስጠት እስከ ምሽቱ 3 እና4 ሰአት ድረስ በማምሸትና የማጣራት ሥራ በመሥራት በመጀመሪያ ዙር 68 ለሦስት ዓመታት የተንከባለለ የይጽደቅልን ጥያቄ 60 እና በሁለተኛ ዙር 97 ተፈናቃይ በድምሩ 157 ተፈናቃይ ሰበር ዜና በሚመስል መልኩ በአንድ ቀን ደብዳቤ በማውጣት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በብፁዕነታቸው ቆራጥ አመራር ሰጪነት አንድም ሠራተኛ ሳይፈናቀል በጠቅላላው 225 ሠራተኞችን በመመደብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅዱስ ሲኖዶስ ለተፈናቃዮችና ቤተሰቦቻቸውን እረፍት በሚሰጥ መልኩ የተፈናቃይን ምዕራፍ ለመዝጋት ተችሏል፡፡ለዚህ ታላቅ ስኬትም አዲስ በጀት ከፍተው ተፈናቀይን ለተቀበሉልን የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፡ ምክትል ሊቃነ መናብርትና ባለድርሻ አካላትን ሁሉ ይህ ዓለም አቀፍ ታላቅ ጉባኤ እንዲያመሰግንልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
የተጀመረው መልካም አስተዳደር ከዚህ ይበልጥ ዘምኖ ይቀጥል ዘንድ ሥልጠናና ምክክር ጉባኤ አስፈላጊ መሆኑን በማመን በብፁዕነታቸው ሐሳብ አመንጪነት በአስተዳደር ጉባኤ ጸድቆ የሀገረ ስብከቱና የክፍላተ ከተማ የሥራ ኃላፊዎችና መላው ሠራተኞች፤ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ዋና ዋና ጸሐፊዎች፤ምክትል ሊቃነ መናብርትና የሰንበት ት/ቤት
ተወካይ፤ ሒሳብ ሾሞችና ቁጥጥሮች ከነምክትሎቻቸው እንዲሁም በሀገረ ስብከታችን ውስጥ የሚገኙ ሊቃውንትን ተደራሽ ለማድረግ የጉባኤና የመንፈሳውያን ኮሌጆች መምህራንን በማሳተፍ ለዚህ ጉባኤና ምክክር የሚመጥኑ ታዋቂ መምህራንን በመጋበዝ በልዩ ልዩ አርእስተ ጉዳዮች ዙሪያ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ሥልጠናና ምክክር ተካሂዷል፡፡
ልማትን በሚመለከት
አሮጌው ቄራ በሚባል ሥፍራ ለመሥራት የታቀደው የሀገረ ስብከቱ 3B+G+14 ሚክስድ ሕንፃ ሥራ ከስምንት ዓመታት በፊት ተጀምሮ የቅድሚያ ክፍያ ተከፍሎና የሳይት ርክክብ ተደርጎ ግንባታው ቢጀመርም ከመሬት እንኳን መውጣት ባለመቻሉ ጉድጓድ ውስጥ ውኃ ሞልቶበት ግንባታው ሙሉ በሙሉ በመቆሙና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳይደረግበት በመቆየቱ ኮንትራክተሩ ባሣየው ከፍተኛ የአፈጻጸም ድክመት ቀደም ሲል ውሉ መቋረጡ ግልጽ ነው።
በመሆኑም ውል መቋረጡን ተከትሎ ቅድሚያ ክፍያውንና ያልተሠራበትን ገንዘብ ለማስመለስ ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱን እንደተረከቡ ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ በመሥጠት የሙያ ስብጥር ያለው ቡድን አቋቁመው ውይይት በሚደረግባቸው ነጥቦች ላይ እንዲሁም ሳይቱን ከተረከበው ኮንትራክተር ጋር በአጠቃላይ ከ19 ቀናት በላይ እልህ አስጨራሽ ውይይት ከተደረገ ቦኃላ
ሳይቱን መረከብ ተችሏል፡፡
ሥራ ላይ ያልዋለውን ገንዘብ በተመለከተ ገንዘቡን ለማስመለስ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ልጆች በሆኑት የምህንድስናና የሕግ ባለሙያዎች አማካኝነት ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ ምክክር ላይ እንገኛለን። ቀሪ ሥራውንም ለማስቀጠል የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ወስኖ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሀገረ ስብከቱ እንዲሁም ከበጎ ፈቃደኛ የቤተ ክርስቲያን ልበ ቅን ባለሙያዎች የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ በጨረታ ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡
የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ቢሮዎችን ከኪራይ ለማላቀቅ በማሰብ በወቅቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አሁን የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሄኖክ ጥረት መንግሥት ለሁለት ክፍላተ ከተማ በሰጠን ቦታ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠ በመሆኑ ግንባታውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነን፡፡
በሌሎችም ገዳማትና አድባራት የቤተ ክርስቲያንና የልማት ሥራዎችን ለመገንባት በርካታ ዕብነ መሠረት ተባርከው ተቀምጠዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ፕሮግራሙ ያስገኘልንን በረከት እንደ በጎ አጋጣሚ በመጠቀም በተለያዩ አድባራትና ገዳማት ተሠርተው የተጠናቀቁ ግዙፍ የልማት አውታሮችን በብፁዕ አባታችን አቡነ ሕርያቆስ ጋባዥነትና መሪነት በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተባርከውና ተመርቀው ገቢ በማስገኘት ላይ የገኛሉ፡፡ሌሎችም በተመሳሳይ መልኩ በአባቶቻችን እጅ ተባርከው ወደ እራስ አገዝ ልማት ገብተዋል፡፡
ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ
ወንጌል ያለውንና የሚመጣውን ትውልድ መቅረጫ ማሽንና ድጂታሉን ዓለም ማያ አጉሊ መነጽር እንደ መሆኑ መጠን በበጀት ዓመቱ ከአድባራትና ገዳማት ሰባክያነ ወንጌልን በማቀናጀት በሁሉም ገዳማትና አድባራት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ለምእመናን በአግባቡ ተሰጥቷል፡፡ በውጤቱም ምእመናን ሃይማኖታቸውን ጠብቀዋል በጽድቅና በትሩፋት ሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡
ካህናት አስተዳደርን በተመለከተ፤
የመስቀል ደመራ የበዓለ ጥምቀት ፣የገብረ ሰላም ፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በዓለ ሲመት ዲፕሎማት የምንግሥታ ባለሥልጣናት ለቁጥር የሚታክቱ ካህናትና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት መርሐ ግብሩን ጠብቆ እጅግ በደመቀ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እንዲከበር ሆኗል፡፡
በሕግ አገልግሎት በተመለከተ
በኩል በሀገረ ስብከቱ የሕግ አገልግሎት በኩል ያሉ ውስን የክስ መዝገቦች እንዳሉ ሆነው 19 አብያተ ክርስቲያናት የሚጠቀሙበትን የባሕረ ጥምቀት ቦታ ላይ ይዞታው*የኛ ነው ከሚሉ ግለሰቦች ጋር ከፍተኛ ክርክር በማድረግ ስፋቱ 12687 ካሬ ሜትር የሆነ ቦታ ማስከበር ተችሏል፡፡
ሰበካ ጉባኤ በተመለከተ
በበጀት አመቱ የምርጫ ጊዜያቸው ያጠናቀቁ በስምንቱም ክፍለ ከተማ አድባራትና ገዳማት ሃምሳ ሁለት አዳዲስ ምርጫና አሥራ አንድ የማሟያ ምርጫ በሰላምና በቃለ ዓዋዲው ሕግ መሠረት ተከናውኗል።
ምግባረ ሠናይ አልግሎትን በተመለከተ
በርከታ ተቋምና ግለሰብ ተኮር ስራዎች በሰፊው ተሰርተዋል፡፡ ከነዚህ መካከል በእንጦጦ ደ/ኃ/ቅ/ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ከሰበካ ጉባኤው ጋር ስምምነት በማድረግ የአብነት ት/ቤትና ሌሎች ግንባታዎችን ለማካሄድ 49 ሄክታር መሬት ቦታ ለመረከብ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ቅርስ እና ቱሪዝምን በተመለከተ፡-
ጥንታዊውና የባለብዙ ታሪክ ባለቤት የሆነው ለኢትዮጵያ ቅብዐ መንግሥት የጎላ ድርሻ ያለው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ እና የመንበረ መንግሥት ግቢ ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት በዘመን ርዝማኔ እድሳት ያስፈለጋቸው በመሆኑ ከሀገረ ስብከቱና ከሚመለከተው ባለድርሻ አካል ፈቃድ በመውሰድ ቀና ልብ ባላቸው ምእመናን የገንዘብና የዕውቀት አስተዋጽኦ ቅርስነታቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ በመታደስ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሰንበት ት/ቤትን በተመለከተ
በአዲስ ሥርአተ ትምህርት የጀመሩ በ225 ገዳማትና አድባራት በመማር ላይ ያሉ 45000 በተምሮ ማስተማር ተምረው ያጠናቀቁ 6200 በላይ ወጣቶች ተካታትለው ያጠናቀቁ ወጣቶች ቅዱስነታው በተገኙበት በሚሊኒየም አዳራሽ ተመርቀዉ ወደ አገልግሎት ተሰማርተዋል ፡፡
ከዚሁ ጋር በሕንፃ ጥበቡ የተደነቀው በቱሪስት መስህብነቱ የዓለምን ቀልብ የሣበው የመንበረ ፀባዖት ቅ/ሥላሴ ካቴድራልም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ንቅናቄ ተደርጎ ቅርስነቱ እንደተጠበቀ ሙሉ እድሳት ተደርጎለት ቅዳሴ ቤቱ ቅዱስነታቸውና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የውጪ ሀገር አምባሰደሮች ቱሪስቶች እጅግ በርካታ ምእመን በተገኘበት በደመቀ መንፈሳዊ ሥነ ሥርአት ተከብሯል።
ሌሎችም በመታነጽ ላይ የነበሩ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ግንባታቸው ተጠናቆ ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
ሒሳብና በጀትን በተመለከተ፡-
ከአምናው ከ2016 ዓ/ም በብልጫ ብር 175,362,250.095 ብር በማስመዝገብ ብር ብር 807,039,766.435 ገቢ ተደርጓል።
ለዚህም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ሰበካ ጉባኤ ማኅበረ ካህናት እና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆችና የክፍል ሐላፊዎች እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ የዋና ዋና ክፍል ሐላፊዎችና ሠራተኞች በእጅጉ ተመስጋኞች ናቸው።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት!