የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በወይብላ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ላይ በተፈጸመው ግፍ ልጆቻቸውን ላጡት ቤተሰቦች ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገለጸ!
በማኅደረ መለኮት ወይብላ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ላይ የተፈጸመው ግፍ መላውን ሕዝበ ክርስቲያን ያሳዘነ እና ያስቆጣ እጅግ አስነዋሪ ተግባር መሆኑ የሚታወስ ነው።
ያ ሁሉ ሰቆቃ እና ግፍ አልፎ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍት በሰላም ተከብሮ ውሏል።
ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በደብሩ ከዋዜማው ጀምሮ በመገኘት ማኅሌቱን፣ሥርዓተ ቅዳሴውንና አጠቃላይ የበዓሉን አከባበር ሥርዓት መርተዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙትን የአከባቢውን ምእመናን በትምህርተ ወንጌልም አጽናንተዋል።
የበዓሉ መርሐግብር ከተፈጸመ በኋላም ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ ደከመኝ ሳይሉ የክንፈገብርኤል(ወጣት ሩፋኤል) እና የኃይለሚካኤል (ወጣት ስመኘው) ቤተሰቦቻቸው ቤት ድረስ በመሄድ በቃለ እግዚአብሔር ኅዘንተኞች እንዲጽናኑ አድርገዋል።
በቀጣይ ሀገረ ስብከቱ ልጆቻቸውን ላጡት ቤተሰቦች ድጋፍ እንደሚያደርግም ሊቀ ጉባኤ ገልጸዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ታደሰ እና በሀገረ ስብከቱ እውቅና አግኝቶ ችግሩን እንዲያጣራ ከደብሩ የተቋቋመው ኮሚቴ ከክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር ኅዘንተኞች ቤት ተገኝተዋል።
የተቋቋመው ኮሚቴ እያንዳንዱን የተከሰተውን ችግር በሰከነ መንፈስ በጥንቃቄ እያጣራ እንደሆነም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ከመንግሥት ከተዋቀረው ኮሚቴ ጋር እየተነጋገረ ከሥር መሠረቱ ያለውን ችግር እያጠና እንደሚገኝም ተገልጿል።
ምእመናን ያሳዩት ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የሚበረታታ መሆኑ ተጠቅሶ አሁንም እንዲረጋጉ እና ትዕግሥተኛ እንዲሆኑ መልእክት ተላልፏል።
በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
የዜናው ምንጭ፦ ችግሩን እንዲያጣራ የተቋቋመው የደብሩ ኮሚቴ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ:-
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
- ትዊተር :-www.Twitter.com/AddisDiocese