የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአድባራትና ገዳማት ለሚገኙ ሠራተኞች ያዘጋጀው ፎርም (ክሊራንስ) በሥራ ላይ እንዲውል መመሪያ ሰጠ!!
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሥራ ላይ ለሚገኙ ገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ያዘጋጀው ፎርም (ክሊራንስ) ሳምፕል በሥራ ላይ እንዲውል ሐምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ሁለገብ አዳራሽ ለተገኙ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ ጸሐፍያን ፣ ምክትል ሊቃነ መናብርት ፣ የሒሳብ ሠራተኞችና ተቆጣጣሪዎች መመሪያ ተላልፎአል፡፡
በተዘጋጀው የፎርም (ክሊራንስ) ማንዋል ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና መግለጫ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በዚህ ዘመን ሰው ከደረሰበት ደረጃ መድረስ አለብን ፤ በተለይም በፎርም ልንበለጥ አይገባንም ፤ ይህ ፎርም አሠሪውንም ሠራተኛውንም ሊጠቅም ይችላል፡፡ ሠራተኛው ሥራ ሲቀይር ወደ ተቀየረበት ቦታ ፎርሙ ካልሄደለት ቅያሪው ተፈጻሚ አይሆንም፡፡
ስለዚህ ሠራተኛው ራሱ ፎርሙን በሥራ ላይ እንዲውል የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊአበረክት ይችላል፡፡ ዛሬ የተሟላ መረጃ ካላስቀመጥን ነገ ቤተ ክርስቲያንን ተጠያቂ ልናደርግ እንችላለን፡፡ ፈቃድ የሚወጡ ሠራተኞች ይህ ሰነድ ከሌላቸው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ በፎርሙ ዙሪያ ማብራሪያቸውን ከሰጡ በኋላ አያይዘው የ2007 ዓ.ም የፐርሰንት አሰባሰብን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት የፐርሰንቱን አሰባሰብ ጥናት የሚአደርግ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሥራ ላይ ይገኛል ፤ በበጀት ዓመቱ ምን ያህል ፐርሰንት መሰብሰብ እንዳለበት ፣ ምን ያህሉ እንደተሰበሰበ ፣ ምን ያህል ሳይሰበሰብ እንደቀረ ኮሚቴው የማጣራት ሥራውን ያከናውናል፡፡
በመጨረሻዎቹ የበጀት ዓመት ወራትና ቀናት ያለባቸውን ውዝፍ የከፈሉ ምስጋና ይገባቸዋል፣ በማለት ኃላፊነታቸው በአግባቡ ለተወጡ የአድባራት እና ገዳማት ኃላፊዎች ሥራ አስኪያጁ ምስጋና አቅርበውላቸዋል፡፡ቀደም ሲል እንዳሰብነው የ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት ዕዳ የለሽ ዓመት ምሕረት እንዲሆን ታስቦ ነበር ፤ ሌሎች የ2005 እና የ2006 ዓ.ም የበጀት ዓመት የተጠራቀሙ ውዝፎች ሊኖሩበት እንደሚችል ይታመናል፡፡
ከሥራዎቻችን አንዱ ፐርሰንት መሰብሰብ በመሆኑ ይህንን ዓላማም ስለደገፋችሁ አብዛኞቻችሁ ልትመሰገኑ ይገባችኋል ፤ ይህንን በተመለከተ ራሱን የቻለ መድረክ ከፍተን እንመሰጋገናለን፡፡ የ2008 ዓ/ም የበጀት ዓመትንም ዕዳ የለሽ የበጀት ዓመት ለማድረግ ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል ፤ ዕዳው የሚጀምረው አሁን በመሆኑ መነጋገርም ያለብን አሁን ነው ፤የዚህን ወርህ ዕዳ በሚቀጥለው ወርህ መክፈል ይኖርብናል ፤ ገንዘባችንን መሰብሰብ በጀመርንበት ወቅት 20% የሀገረ ስብከቱ ድርሻ መሆኑን መረዳት አለብን ፤ የተሰጠንን አእምሮ ተጠቅመን ዘመናዊ አሠራርን ማስፈን አለብን ፤ በተለይም ኃላፊ የሚሆን ሰው ከራሱ በላይ ማሰብ ፣ ስለሌሎች ሰዎች ማሰብ አለበት ፤ ፐርሰንትንም ጭምር የምንበላ መሆን የለብንም ፤ ፐርሰንት ለከፍተኛ ኃላፊዎች የዕድገት አሰጣጥ የመገምገሚያ ነጥብ ነው፡፡
በሌላ ዜና የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ ጸሐፍያን፣ ምክትል ሊቃነ መናብርት ፣ የሒሳብ ሠራተኞችና ተቆጣጣሪዎች ሐምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ሁለገብ አዳራሽ ባደረጉት ስብሰባ ሀገረ ስብከቱ ሲአሰለጥናቸው የነበሩት የሒሳብ ሠራተኞች በሥልጠናው ተግባር ጠንክረው እንዲቀጥሉበት በጭብጨባ በታገዘ የማበረታቻ ሐሳብ ድጋፍ ሰጥተዋቸዋል፡፡ በየአድባራቱና በየገዳማቱ የሚገኙ ቀሪ የሒሳብ ሠራተኞች ለሚአከናውኑት የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና አስፈላጊውን ማቴሪያል እንደሚአሟሉላቸው የአብያተ ክርስቲያናቱ ተወካዮች ቃል ገብተዋል፡፡ሥልጠናውን ሲመሩ የቆዩት የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊው ሊቀጠበብት ኤልያስ ተጫነ የስልጠናውን አስፈላጊነት በገለፁበት ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ያቆየችው አሠራር መልካም ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ሲንግል ኢንትሪ (ነጠላ የሒሳብ አሠራር) ነበር፡፡ ስለሆነም ሀብት ለብቻው ፣ ጥሬ ገንዘብ ለብቻው አልነበረም ፤ የቀድሞው አሠራር የተሻለ ነበር ፤ በእኛ ዘመን ግን ያለው አሠራር የተስተካከለ አልነበረም ፤ ምክንያቱም ዘመናዊነት የጎደለው ነበር ፤ ይህንን አሠራር መቀየር ባለመቻላችን ልንወቀስ ይገባናል፡፡ በመጀመሪያ አሠራራችን ትክክል ነው የሚለውን አስተሳሰብ ማስወገድ አለብን፡፡ ያለብንን የአሠራር ችግር ካመንን በራሳችንም ሆነ በምሁራኑ አቅም ወደ መፍትሔ አቅጣጫ እንሄዳለን ፤ ያን ጊዜ የጎደለው ይስተካከላል፡፡ በ2001 ዓ.ም አሠራራችንን ለመለወጥ ታስቦ ነበር ፤ ነገር ግን ጊዜው አልነበረም ፤ አሁን ግን ጊዜው ነው ፤ ችግሮችን ለመፍታትና አሠራራችንን ለማዘመን የሚከደብን የለም፡፡
በመሆኑም ሀገረ ስብከታችን ለለውጡ ቆርጦ ተነስቷል፡፡ በመጀመሪያ ለውጡን ከራሱ ይጀምራል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያልተሟላልንን ሁሉ እንዲሟላልን አድርጓል ፤ ከፍተኛ ድጋፍም አድርጎልናል፡፡
የሀብት ትመናውን በተመለከተ ሕጋዊ ሰውነት ባላቸው ክፍሎች ይመዘናል፡፡ ሁላችሁም በአጭር ጊዜ የሀብት ትመና ልታደርጉ ይገባል በማለት አብራርተዋል፡፡
በማያያዝም ሠልጣኞቹ ከ800 በላይ በሚሆን ተሰብሳቢ ፊት ቁመው የስልጠናውን ጠቀሜታ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ሀገረ ስብከቱ ባዘጋጀው የሒሳብ ሠራተኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና በጣም ረክተናል ፤ ሥልጠናው ሊአነሳሳ የሚችል ነው፤ የሒሳብና በጀት ኃላፊው ሊቀጠበብት ኤልያስ ተጫነ በኮምፒውተር የታገዘ ሥልጠና እየሰጡን ነው ፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ ዕለት ዕለት ይጎበኙናል ፤ ምክትል ሥራ አስኪያጁም ሒሳብና መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን ዝምድና (ግንኙነት) እየጠቀሱ ያስረዱናል፡፡
ከዚህ ቀደም የተማርንበትን ደብተር ከወደቀበት ማንሳት ጀምረናል፡፡ ሙያችንን ለማሻሻል ቆርጠን ተነስተናል ብለዋል፡፡ ከሠልጣኞቹ ሐሳብ በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የጎላ ሚካኤል ሰበካ ጉባኤ ም/ሊቀመንበር ልማትን የሚአግዙና በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ያደጉ ሊአማክሩን እና በነጻ ሊሠሩልን ቃል የገቡልን ግለሰቦች ቢኖሩም ነገር ግን ከላይ አልተፈቀደም ስለተባለ ሥራውን ሣንሠራ ቆይተናል፡፡ አሁን እየተሰጠ ባለው ስልጠና በግሌ ማጨብጨብ እፈልጋለሁ በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል:: የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ከዚህ በፊት ሰዎች የለውጥ ሐሳብ ይዘው መጥተው ነበር ፤ ይዘውት በመጡት የለውጥ ሐሳብ ውስጥ ግን ክፍተቶች ነበሩ ፤ ቤተ ክርስቲያንን በሁለንተናዋ ማወቅና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመኖር የሆነ ነገር በማወቅ ሁሉን ነገር እንዳወቁት አድርጎ ማሰብ ልዩነት አላቸው ፤ ዘመናዊነት የሚጎድለው የካህን ዕውቀት ስለአለ እኔ ነኝ የማውቀው የሚል መንፈስ ይታያል፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ አስተሳሰብ የለውጥ ሽግግር አይታይም፡፡ ካህናት ያልተለወጡበትና ካህናተ የማይመሩት ለውጥ ለቤተ ክርስቲያን ጎጂ ነው ፤ በመጀመሪያ ለውጥ ለማን ነው? የለውጥ መሪ ማን ነው? የለውጥ አራማጅ ማነው? የሚሉት ጥያቄዎች በትክክል ካልተመለሱ ተቋም ይፈርሳል፡፡ ለምሳሌ ያህል ብንመለከት ሊቢያና ሱማሌ ሀገራቸውን ያፈረሱት ለውጥ እናመጣለን በሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህ የለውጥ ሐሳቦች በትክክለኛው ሰው ካልተመሩ ይፈርሳሉ፡፡ የለውጥ አራማጅ የሆነው ሰው ለውጡ ይጠቅመኛል ብሎ ሲአስብ ብቻ ነው ለውጥ የሚመጣው ፤ ጎደሎ ነገር ይዞ የሚመጣ የለውጥ ሐሳብ ግጭትን እንጂ ለውጥን አያመጣም፡፡
ለውጥ በአስተሳሰብ ላይ ሊመሠረት ይገባል ፤ የሰው አስተሳሰብ ካልተቀየረ ኮምፒውተር አይሠራም ፤ አውሮፕላን አይበርም ፣ መርከብ አይንሳፈፍም፡፡ ፀሐይ ፣ ጨረቃና አየር ብቻ ናቸው የሰውን ለውጥ የማይፈልጉት፡፡ ስለዚህ የሚአስፈልገንና የምንፈልገውን ለይተን ልናውቅ ይገባናል በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ መልእክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት ተሰብሳቢዎች በጋለ ጭብጨባ ድጋፋቸውን ለግሰዋቸዋል፡፡
{flike}{plusone}