የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚያስተላልፋቸው መመሪያዎችና አፈጻጸማቸው ዙሪያ ውይይት አደረገ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ያሉበትን የሥራ ጫናዎች ለማቃለልና የባለጉዳዮችን እንግልት ለመቀነስ እንዲሁም ደግሞ የዕዝ ሰንሰለቱን ጠብቆ ሥራዎችን ለመከወን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድረጎ የተሻለውን መንገድ ሁሉ በመከተል ላይ ይገኛል፡፡ ጽ/ቤቱ ከወሰዳቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች መካከል አንዱ በሥሩ ካሉት አድባራትና ገዳማት የሚመጡ ልዩ ልዩ ባለጉዳዮችን የሚያስተናግድበት መንገድ ነው፡፡

 ይህ የአሠራር መንገድ ባለጉዳዮች ከታች ጀምሮ ያሉትን የጽሕፈት ቤቱን መዋቅር ባልጠበቀ መልኩ ከአሁን በፊት እንደነበረው ሊሰተናገዱ እንደማችይሉ ይልቁንም የዕዝ ሰንሰለቱን ጠብቀው ለሚያቀርቡት ጥያቄ ሁሉ ከሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ጽ/ቤት በመጀመርና በክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል አድርገው መስተናገድ እንዳለባቸው የሚያበረታታ ሲሆን በየደረጃው ያሉት የአሰተዳደር አካላትም የባለጉዳዮችን ጥያቄ በአግባቡ ተቀብለው ያለምንም ደጅ ጥናትና እንግልት ሕጉ በሚፈቅደው መንገድ ሁሉ እንዲያስተናግዱ ተደጋጋሚና በፅሁፍ የሆነ የሥራ መመሪያ አስተላልፏል፡፡

 የተላለፉትን የሥራ መመሪያዎች የአፈጻጸም ሂደትና ያስመዘገቡትን አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤት እንዲሁም በባለጉዳዮቹ ዘንድ የተጣቸውን ግብረ መልስ ምን እንደሚመስልና የወደፊት የጽ/ቤቱ  የሥራ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ዓላማው ያደረገ የውይይትና ግምገማ መድረክ ብፁእ አቡነ መልከ ጼዴቅ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጉባኤው ሰብሳቢ፤ መ/ር አባ ሞገስ ኃ/ማርያም (ቆሞስ) የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ መጋቤ ጥበባት ምናሴ ወልደሃና የሀገረ ስብከቱ ም/ሥራ አስኪያጅ፤ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች እና ሠራተኞች  እንዲሁም የሰባቱ ክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆች እና ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ተደረገ ፡፡

   ከላይ ያነሣናቸው የዕለቱ የመወያያ አጀንዳዎች በም/ ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ጥበባት ምናሴ ወልደሀና ከቀረቡ በኋላ የጉባኤው ሰብሳቢ የሆኑት ብፁዕነታቸው በጉባኤው ለተገኙት የጉባኤው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት መዋቅሩን ጠብቀው የተላለፉት የሥራ መመሪያዎች የጽ/ቤቱን የባለጉዳይ መጉላላት ከመቅረፉም ባሻገር ባለጉዳዮች በትምህርት ዝግጅታቸውና  በችሎታቸው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፤ ቀጥተኛ የክንውን የሥራ ሂደት በሕጋዊ አግባብ እንዲከናወን ለማስቻል፤ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ብሎም ለመቀነስና ተገቢ ያልሆነ ከገጠር ወደ ከተማ የአገልጋዮች ፍልሰትን ለመከላከል መሆኑን በሚገባ  አስረድተዋል፡፡

  በጉባኤው ላይ የተገኙ ተሳታፊዎችም የተላለፉት መመሪያዎች ምንም ዓይነት እንከን የሌለባቸው ከመሆናቸውም በላይ የሥልጣን ተዋረድንና የዕዝ ሰንሰለቱን የሚያከብሩ በመሆናቸው አድንቀው በባለጉዳዮች የግንዛቤ ዕጥረትና በሀገረ ስብከቱ አንዳንድ ግለሰቦች ጣልቃ ገብነት የአፈጻጸም ችግር እንደገጠማቸው በውይይቱ ላይ አንስተዋል፡፡ እነዚህንም ችግሮች በጋራ ለመቅረፍም ቃል ገብተዋል፤ ከእነዚህም አጀንዳዎች በተጨማሪ የዚህ ዓመት የዘጠኝ ወራት የፐርስንት ገቢ በክፍላተ ከተሞቹ ሒሳብ ሹሞች ገለጻ ተደርጎ ቀሪውን የገቢ ፐርሰት ለመሰብሰብ በሥራ ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡   

በመጨረሻም በጉባኤው ላይ ተነሥተው ውይይት በተደረገባቸው ውስን አጀንዳዎች ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ የሚከተለውን የጋራ አቋም መግለጫ በማውጣት ጉባኤው ተጠናቋል፡፡ የጋራ አቋም መግለጫዎቹም፡-

1.  ከብፁዕ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ጳጳስና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሚተላለፉ መመሪያዎች ለቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎት ጠቃሚና ለወደፊቱም ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጡ የሚችሉ በመሆናቸው በጋራ ለመፈጸም ቃል እንገባለን ፡፡

2.  ከየካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተላለፉት መመሪያዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ እንቅፋት የሆኑ መሰናክሎችን በመለየት መፍትሔ ለመስጠት በጋራ ጥረት እናደርጋለን፡፡

3.  ከብፁዕነታቸውና ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የሚሰጡ ማንኛውም መመሪያዎች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ለመጨበጥ በክፍለ ከተማ እና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ ውይይት ለማድረግ ቃል እንገባለን ፡፡

4.  ባለ ጉዳዮች የእዝ ሰንሰለቱን ጠብቀው እንዲስተናገዱ የተጀመረውን ጥረት ለማስቀጠል እንተጋለን ፡፡

5.  አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ሲመሰረቱ ቀኖናዊ ይዘቱን የተከተሉ እንዲሆኑና በመስራቾች መካከል የሚፈጠረው አለመግባባት ለመቀነስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲሰጥ ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር የተሰጠውን መመሪያ በጋራ ለመተግበር እንተጋለን ፡፡

6.  ማንኛውም ባለ ጉዳይ የግል ማመልከቻውን ይዞ በመምጣት የሚያቀርበው ጥያቄ የሀገረ ስብከቱ ሥራ ወደ ኋላ የሚጎትትና ጽ/ቤቱን ለአላስፈላጊ ስም መጥፋት የሚዳርግ በመሆኑ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ በክፍለ ከተማ በኩል በውሳኔ በሚቀርበው መሠረት ጥያቄው እንዲስተናገድ በጋራ እንሠራለን ፡፡ 

7.  መመሪያዎች በአንድ ጊዜ ፍጹም ሊሆኑ ስለማይችሉ በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት በጋራ እየተራረምን የቤተክርስቲያናችንን ክብርና ዝና ለመመለስ በጋራ እንጥራለን፡፡   

8.  ፐርሰንት አሰባሰብ ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ ተግባር በመሆኑና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት መሳካት አስፈላጊ ስለሆነ እስከ አሁን ድረስ የተሠራውን ሥራ አመርቂ ቢሆንም ለወደፊቱ የቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ የበለጠ በርትተን ለመስራት ቃል እንገባለን ፡፡

9.  ለክፍለ ከተሞች በየወሩ የሚላከው ሥራ ማስኬጃ ከሥራው ክብደትና ብዛት አኳያ ትኩረት ሊሰጠው ስለሚገባ ለወደፊቱ እንዲስተካከል በአክብሮት እንጠይቃለን ፡፡   

እግዚአብሔር ሥራችንን ይባርክልን!!

  የሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል