የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት ጠንክሮ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ

                                                                                                በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

640

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘትና የተሻለ የሥራ መነቃቃትን ለመፍጠር በማሰብ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ አድባራትና ገዳማት የደረሰ የሠራተኛ ዝውውር ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተገልጿል፡፡
ሀገረ ስብከቱ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት ባለው ቁርጥ አቋም መሠረት ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ከአንዱ የሥራ ክፍል  ወደ ሌላው ሥራ ክፍልና ወደ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ቁጥራቸው ከ4 ያላነሱ ሠራተኞች ተዛውረው  እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡
መልካም አስተዳደርንና ልማትን አጠናክሮ ለመቀጠል ቆርጦ የተነሳው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሻለ የሥራ ተነሳሽነትንና መነቃቃትን ይፈጥራሉ ያላቸውንና ቁጥራቸው ከ24 ያላነሱ የአድባራትና የገዳማት ጸሐፍያንንና ሰባክያነ ወንጌልን ከአንዱ ደብር ወደ ሌላው ደብር፣ ከአንዱ ገዳም ወደ ሌላው ገዳም አዛውሮአቸዋል፡፡
ዘመናዊ አሠራርን በማምጣት፣ ልማትን በማስፋፋት፣ ሰላምን በማስፈን፣ የፐርሰንት ክፍያን ወደ ላቀ ዕድገት በማሳደግ የተመሠከረለትና ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ምስጋናን የተቸረው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለውጥ አሠራሩን በበለጠ እውን ለማድረግ ሥራና ሠራተኛን የማገናኘት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አንድነትና አስተዳደር ለማጠናከር በ1991 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በወጣው በቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 60 ንዑስ ቁጥር (ሰ) ላይ የተመለከተው ድንጋጌ “ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ የሚገኙት ማናቸውም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች እንደአስፈላጊነቱ ከአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ተዛውረው የመሥራት ግዴታ አለባቸው ይላል”፡፡
በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር (ሸ) ላይ በተቀመጠው ድንጋጌ “ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ የሚገኙት ማናቸውም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች የተመደቡበትን ሥራ በትክክል የማከናወን፣ ሥራውን በሚመለከት ጉዳይ ለበላይ ኃላፊ የመታዘዝና መመሪያ የመቀበል፣ ግብረ ገብነትንና ቅን አገልግሎትን የማሳየት፣ ሥራውንና የሥራ ሰዓትን የማክበር ግዴታ አለባቸው” ይላል፡፡
ከላይ በተቀመጠው የቃለ ዓዋዲ ድንጋጌ መሠረት በዝውውር ሥርዓት ከአንድ የሥራ መስክ ወደ ሌላ የሥራ መስክ ተዛውረው እንዲሠሩ በበላይ ኃላፊ የታዘዙ የቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ልዩ ሠራተኞች ትእዛዙንና መመሪያውን አክብረው ሊሠሩ እንደሚገባቸው ያመለክታል፡፡
በመጨረሻም ሀገረ ስብከቱ ለለውጡ ተግባር እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍና አስተዋጽኦ ሊአበረክት ይገባል እንላለን፡፡ {flike}{plusone}