የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ለተመደቡት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

ጥቅምት 2013 ዓ/ም ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ በመደበው መሠረት ጥቅምት 21/2013 ዓ/ም የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ ሠራተኞች፣ የክፍላተ ከተሞች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል::

በአቀባበል መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ባደረጉት አጭር ንግግር “በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በየዓመቱ ከሚነሱ አጀንዳዎች መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይ ነበር ሆኖም ግን ለተነሣው አጀንዳ በቂና አግባባዊ ምላሽ ሳይሰጠው እስካሁን ድረስ ቆየ፣ በዚህም የዘገየ አሠራር የተነሣ የሀገረ ስብከቱ ሁለንተናዊ ችግሮች እየተባባሱ መጡ፣ በዚህ ዓመት የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልዓተ ጉባኤ ላይ በተደረገው ውይይት ግን ሕገ ቤተ-ክርስቲያኑን በማሻሻልና ሀገረ ስብከቱ ራሱ ችሎ እንዲተዳደር ለማድረግ ምርጫ ተከናውኖ በአብላጫ ድምፅ ያሸነፉትን ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ መድቧል፣ በዚህ የሀገረ ስብከቱ ችግሮች ምላሽ ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል::

በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ኩሎ ዘፈቀደ ገብረ እግዚአብሔር” እግዚአብሔር የፈቀደውን ያደርጋል፣ ከአሁን በፊት በዚሁ ቦታ ተመድቤ ለዘጠኝ ወራት ያክል ሀገረ ስብከቱን መርቻለሁ፣ አሁን ደግሞ እኛ እና መንፈስ ቅዱስ ወስነናል በማለት ስልጣን የተሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ በድጋሚ መርጦ ለዚህ ትልቅ ቦታ ሲመድበኝ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ተረድቼ ለማገልገል መጥቻለሁ፣ እግዚአብሔር በሰጠን መልካም ዕድልና ጊዜ ተጠቅመን የቻልነውን ሁሉ በጋራ እንሰራለን፣ ሀገረ ስብከቱንም ወደተሻለ ደረጃ ከፍ እናደርጋለን፣ በቻልነው መጠን ችግሮችንም እንፈታለን፣ የእናንተ አብሮነትና ጸሎት እንዲሁም ምክር ግን አይለየኝ በማለት አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል::

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን የተሾሙት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ከአሁን በፊት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ጳጳስ በመሆን ሀገረ ስብከቱን በመሩበት ወቅት በቀድሞ የሀገረ ስብከቱ መሪዎች ተጀምረው የነበሩትን ቴክኖሎጅ ተኮር ሥራዎችን ማለትም:-

  1. የሰው ሀብት አስተዳደር ሲስተም/ Human Resource management system
  2. የንብረትና ሀብት አስተዳደር ሲስተም/ Asset Management System
  3. የመዝገብ ቤት ፋይል አስተዳደር ሲስተም/Archive File Management system እና
  4. እስቶክ አስተዳደር ሲስተም/ Stock Management System የመሳሰሉትን አዳዲስ የአሠራር መተግበርያ ሲስተም ሶፍት ዌሮችን ሥራ ላይ ያዋሉ ተራማጅ የቤተ ክርስቲያን አባት መሆናቸው የሚታወስ ነው::

ለብፁዕ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ መልካም የሥራ ዘመን ይሆንልዎት ዘንድ እንመኛለን!!!

በሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል