የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለገዳማትና አድባራት የቁጥጥር ሠራተኞች የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መስጠት ጀመረ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ከተመረጡ ገዳማትና አድባራት ለተውጣጡ ስድሳ የቁጥጥር ሠራተኞችና ለሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የቁጥጥር ክፍል ኃላፊዎች በድምሩ ለ67 ሰልጣኞች ለአስር ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መስጠት የጀመረ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ቀደም ሲል ሀገረ ስብከቱ ለገዳማትና አድባራት የሒሳብ ሠራተኞች ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን አሁን ደግሞ ለቁጥጥር ሠራተኞች ባለፈው ሳምንት በጥሩ ሁኔታ የሰጠ መሆኑ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በያዘው ዘላቂ ዕቅድ መሠረት ከገዳማቱና ከአድባራቱ ለተውጣጡ 60 የቁጥጥር ሠራተኞችና ለ7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የቁጥጥር ክፍል ኃላፊዎች ከግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ ግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የኦዲትና ቁጥጥር የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና እየሰጣቸው ነው፡፡
የሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር ዋና ክፍል ስልጠናው በተሳካ መልኩ እንዲከናወን በማሰብ ስለኦዲትና ቁጥጥር ሙያ በቂ ስልጠና የሚሰጡ ባለሙያዎችን በማካተት የተሻለ ስልጠና እንዲካሄድ አድርጓል፡፡ የሚሰጠውን የኦዲትና ቁጥጥር ስልጠና በአግባቡ መቀበል የሚችሉ የቁጥጥር ሠራተኞችን ከገዳማቱና ከአድባራቱ በመመልመል የስልጠናው ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ የሰባቱም ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የቁጥጥር ክፍል ኃላፊዎች የዚህ ስልጠና ተሳታፊ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ የሀገረ ስብከቱ የቁጥጥር ዋና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ትጉሃን ገብረ መስቀል ድራር እንደገለጹት የስልጠናው ይዘት የውስጥ ኦዲት ችግሮች፣ አነስተኛ የሒሳብ እንቅስቃሴ ቅድመ ምርመራ፣ ከፍተኛ ወጪዎች፣ የሃብትና ንብረት ምርመራና ቁጥጥር በስልጠናው ይዳሰሳሉ፡፡ ደንብና መመሪያን መተግበር፣ የተቋሙን ያላማ ማሳካት፣ የሙያ ብቃት ክህሎትን መሠረት ያደረገ የስልጠናው ዋና ትኩረቶች ይሆናሉ፡፡
ኦዲት ምን እንደሆነ ለይቶ ማወቅ፣ በመንግሥት ያለው አሠራርና በእኛ ዘንድ ያለው አሠራር እንዴት እንደሚታይ፣ የሂሳብ ሪፖርትን ማረጋገጥ በስልጠናው ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል፡፡ ስልጠናው የሚሰጠውን ጥቅም አስመልክቶ የቁጥጥር ዋና ኃላፊው ሲገልጹ ስለኦዲትና ቁጥጥር ሰልጣኞቹ በቂ ግንዛቤ በማግኘታቸውና ሥጋቶችን በማዎቃቸው ወደ መፍትሔ አቅጣጫ እንዲመጡ ያግዛቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሀብትና ንብረት አጠባበቅ የተሻለ እና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን ይረዳቸዋል፡፡ የተሻለ ውጤት ያለው የሀብትና ንብረት ዕድገት እንዲኖር ስልጠናው ቁልፍ ሚና ይጫዎታል ብለዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጐይቶኦም ያይኑ ስልጠናው በተጀመረበት ወቅት ለሠልጣኞቹ ባስተላለፉት መልእክት ይህ አሁን የሚሰጠው የኦዲትና የቁጥጥር ሙያ ማሻሻያ ስልጠና የገዳማቱና አድባራቱ ሀብትና ንብረት በአግባቡ እንዲያዝና ወደተሻለም እድገት እንዲጓዝ የሚአግዝ ስልጠና ነው፡፡
ሀገረ ስብከታችን ለዚህ የስልጠና ተግባር ቅድሚያ በመስጠትና አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ የተጀመረው የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊው ሁሉ እየተደረገ ነው፡፡
ሀገረ ስብከቱ የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ልዩ ሀገረ ስብከት እንደመሆኑ መጠን ከቅዱስነታቸው የሚሰጠንን የዕለት ከዕለት መመሪያ በመከተል ልማት እንዲስፋፋ፣ መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋና እንዲህ አይነቱ ዘመናዊ የኦዲትና የቁጥጥር ስልጠና ከሀገረ ስብከታችን እስከ ገዳማትና አድባራት ድረስ ዘልቆ እንዲሄድ ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡