የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሁለተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የገዳማትና አድባራት የሒሳብ ሠራተኞች በሠርተፍኬት አስመረቀ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ከገዳማቱና አድባራቱ ለተውጣጡ ቁጥራቸው 30 ለሆነ የሒሳብ ሠራተኞች ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር፤ የቋሚና የአላቂ ንብረት አያያዝና አወጋገድን አስመልክቶ ለ3 ወራት ያህል የሰለጠኑ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት ሰኞ ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም በሰርተፍኬት አስመርቋል፡፡
ሰልጣኞቹ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ባደረጉት ንቁ ተሳትፎ በሀገረ ስብከቱ በኩል ተሻላሚ ሲሆኑ የሰልጣኞችን የስልጠና ጥራትና ብቃት በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በአንደኛ ዙር ሠልጣኝ የነበሩት የገዳማትና የአድባራት የሒሳብ ሠራተኞች ብቃት ያለው ግንዛዜ ያገኙ በመሆናቸው በሁለተኛው ዙር ረዳት አሰልጣኞች ሆነዋል፡፡
ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሥልጠናውን በመስጠት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የተወጡት የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ በማሰልጠን ሙያቸው ከቅዱስነታቸው ዕውቅና እንዲያገኙ ዋና ሥራ አስኪያጁ አሳስበዋል፡፡
በሌላ ዜና የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት በሥራ እንቅስቃሴአቸውና በፐርሰንት ክፍያ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ አድባራትና ገዳማት የዋንጫ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡
የክፍለ ከተማው ቤተክህነት ለሀገረ ስብከቱ ለዋና ክፍል ኃላፊዎችና በወቅቱ ክፍለ ከተማው ሲመሰረት የላቀ አስተዋጽዖ ለነበራቸውና በሀገረ ስብከቱ ከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት ላላቸው የክፍል ኃላፊዎችም ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት ይትባረክ እግዚአብሔር ዘባረከነ የዛሬው ቀን በጣም ያስደስታል ይህን መንፈሳዊ ጉባኤ ያዘጋጁ ክፍሎች ለሌሎች ሞራል የሚሰጥ ነው፡፡ በፐርሰንት፣ በልማት፣ በሰላም፣ በፍቅር የሚሠራ ሥራ ሁሉ እጅግ አስደሳች ነው፡፡
የልማቱ ውጤት ሰላም ስላለነው ከሁሉም በላይ ሰላም የሰፈነበት ሥራ የሠራችሁ የንፋስ ስልክ የሥራ ኃላፊዎችና የመንግሥት ተወካዮች እግዚአብሔር ይባረካችሁ፡ ሕዝብን በማስተባበር ለአንድነትና ለሰላም ትምህርት የሚሰጡ የተባረኩ ናቸው በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ {flike}{plusone}