የአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ለገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መስጠት ጀመረ

09240

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከሰኔ 19-23 ቀን 2009 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የሥራ ፈጠራ፣ የሊደርፕ ማኔጅመት፣ ሕግ፣የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እና ስርጭት ሥልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኀበር ተወክለው ሥልጠናውን የሚከታተሉት  መ/ር አቢይ ሀረጉ በማኅበሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዴስክ ኃላፊ በስተላለፉት መልእክት ለሥልጠና ሂደት የሚውሉ የጽሕፈት መሣሪያዎችንና የሰማንያ አሀዱ መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ሰልጣኞች በነፃ እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ማኅበሩ በዚህ ሥልጠና ላይ ለማሳተፍ የቻለበት ዋና ዓላማ ማኅበረሰቡ የእኔ ነው ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገዛና እዲጠቀምበትም ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ነው፡፡ ሰማንያ አሀዱ መጽሐፍ ቅዱስ ታትሞ የሚመጣው ከሀገር ውጭ በመሆኑ ታትሞ ሀገራችን እስከ ሚደርስ ድረስ ዋጋው መቶ አሥር ዶላር ይደርሳል፡፡በኢትዮጵያ ብር ደግሞ እስከ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ይደርሳል፡፡ በዚህ ዋጋ ሕብረተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስ የመግዛት አቅም ስለሚአጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኀበር አባል እንዲሆንና ሕብረተሰቡ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በአቅሙ እንዲገዛና እግዚአብሔርን እንዲአውቅ፣ እምነቱንም እንዲያፀና፣ ሥልጠናውን የወሰዱት ሁሉ ለምዕመናን አስፈላጊውን ትምህርት እንዲሰጡ ለማድረግ ነው፡፡ ማኀበሩ በቀጣዩም ለገዳማቱ እና ለአድባራቱ ሰባክያን መጽሐፍ ቅድስ እንዲሰጣቸው ያደረጋል፡፡ በሞባይላችንም ሆነ በላኘቶፓችን የጫነው መጽሐፍ ቅዱስ ቶሎ ስለሚጠፋ ከዚያ ይልቅ ራሱን መጽሐፍ ቅዱሱን መያዝ ይመረጣል ብለዋል፡፡በመቀጠል መምህር ጎይቶኦም ያይኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የስልጠናውን ይዘትና ዓላማ አስመልክተው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቴሌቬዥን ሥርጭት አገልግሎትና ለሀገረ ስብከቱ ሕትመትና ሥርጭት ክፍል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሥልጠናው ዋና ዓላማ የሰልጣኞችን አእምሮ ማነሳሳት፣ መቀየር፣ ለሥራ ተነሳሽነት እንዲዘጋጁ ማድረግ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በዚህ ዓመት ትልቅ ዓላማ አድርጐ የያዘው የሥልጠና ሁኔታን ነው፡፡ ለቤተክርስቲያን የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ስልጠና መስጠት አለብን ከሚል አንጻር ከመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ የሥልጠና ሥራዎችን ሥናከናውን ነው የቆየነው፡፡
ከዚህ አንጻር በመጀመሪያ አካባቢ ለአድባራትና ገዳማት ሒሳብ ሠራተኞች ስለዘመናዊ የሒሳብ አሠራር በተመለከተ የተለያዩ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ሥልጠናው የተሰጠው በቲኦሪና በተግባር በተደገፈ በኮምፒውተር ነው፡፡ በተጨማሪ ለገዳማቱና ለአድባራቱ የኦዲት ሠራተኞች ስለ ኦዲት ሲስተም፣ እንዴት አድርገው ኦዲት ማድረግ እንዳለባቸው ፣እንዴት አድርገው ሒሳብ መዝጋት እንዳለባቸው በባለሙያዎች ሥልጠናውን ለአስር ቀናት ያህል ወስደዋል፡፡ ከዚያም በመቀጠል ለገዳማትና አድባራት የዕለት ገንዘብ ተቀባዮችና ገንዘብ ያዦዎች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ስለንብረትና ገንዘብ አያያዝ በተመለከተ ሥልጠናው ተሰጥቷል፡፡ሠራተኞችን ካሰለጠንን በኋላ የገዳማቱን እና የአድባራቱን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎን ማሰልጠን ችለናል፡፡ ሁል ጊዜ ችግር አለ እያልን ማውራታችን ችግሮችን ሊቀርፍልን ስለማይችል የግድ የአሠራር ሲስተሞችን በመዘርጋት እና የተለያዩ የእውቀት ዘርፎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ የዕውቀት ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ ስለሆነ በአሁኑ ሰዓት ሥልጠናውን እየሰጠን እንገኛለን፡፡
በዚህ ሥልጠና በኃላፊነት ላይ ያሉ የሁሉም ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ይሳተፋሉ፡፡አሰልጣኞችን በተመለከተ የቤተክርስቲያናችን ልጆች የሆኑ የተለያዩ ሙያ ያላቸው ሲሆኑ በራሳቸው ሥራን የፈጠሩ እና ለኢትዮጵያ ምሳሌ የሆኑ እነ ዶክተር  ወረታው አሰልጣኝ እንዲሆኑ ተመርጠዋል፡፡  በቀጣዩ የሥልጠና ጊዜያትም ስለመልካም አስተዳደር ፣ ስለሊደርሽኘ፣ስለ ቼንጅ ማኔጅመንት፣ስለሕግ ስልጠና ይሰጣል፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ የሚመጡ አሰልጣኞች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅድስ ማኀበር ስለመጽሐፍ ቅዱስ ሥርጭት በተመለከተ በሥልጠናው ይሳተፋል፡፡ ከሀገረ ስብከትም የሚገኙ ባለሙያዎች ሥልጠናውን ይሰጣሉ፤ ይህ ሥልጠና የመጀመሪያችን እንጂ የመጨረሻችን አይደለም፡፡
በመጀመሪያ ትኩረት ያደረግነው ከፋይናንሱ ላይ ነው፡፡ ሠራተኞቹ ዘመኑን እንዲከተሉ ለማድረግ የተለያዩ አሰልጣኞችን እየመረጥን ነው የምናሰለጥነው፡፡ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኀበር ዋና ሥራው የተለያዩ መንፈሳዊ መጻሕፍትን መተርጎምና ማሰራጨት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር በከተማችን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስ በማሰራጨት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በተክርስቲያን ስም የታተመው ሰማንያ አሀዱ መጽሐፍ ቅዱስ ለሥልጠናው ተሣታፊ ሁሉ በነፃ ይታደላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ሥልጠና የምንጠብቀው ትልቁ ውጤት የተሻለ አሠራር፣ ግልጽነትና ለሕሊና ተገዢ የሆነ አሠራር እንዲፈጠር ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች በካህናትም በምዕመናንም የተለያዩ ችግሮች እንደሚከሠቱ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በየጊዜው ችግሩን ከማንሳት ይልቅ ችግሩን ሊቀርፍልን የሚችል ሲስተም መዘርጋት አስፈላጊ ነው፡፡ ትልቁን ችግር ሊቀርፍልን የሚችለው ደግሞ ሥልጠና መሆኑ  በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ካለመማር የተነሣ ሕዝብ ሊጠፋ እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስም ይናገራል ፡፡ ካለማዎቅ፣ ካለመረዳት እና ከግንዛቤ ማነስ የተነሣ የአሠራር ክፍተት ይፈጠራል፡፡ የተሻለ ፣ዘመናዊ፣ ግልጽነት ያለውና ቤተክርስቲያንን የሚጠቅም አሠራር ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
የዚህ ስልጠና ቀጣይነት ቀደም ሲል የተለያዩሥልጠናዎች እንደተሰጡ ሁሉ በቀጣዩም በገዳማትና አድባራት ደረጃ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሰባክያን፣ሠራተኞች፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ ካህናትና ልዩ ልዩ አገልጋዮች ስልጠና ይካሄዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የሀገረ ስብከቱም የፋይናንስ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ሥራ እንዲሠሩ እያደረግን ነው፡፡እነዚህ ሁሉ በእቅዳችን ላይ የተካተ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሻለ አሠራርና የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ጥረቶችን እያደረግን ስለሆነ የቤተክርስቱያንን የልማት ዕድገት ከፍ ለማድረግ፣ ዘመናዊና የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ቁጭት ያለባቸው ባለሃብቶችም፣ ባለሙያዎችም ይኖራሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ሀገረ ስብከቱ ለውጥ ለማምጣት በሂደት ላይ ስለሆን ሀገረ ስብከቱንና ቤተክርስቲያንን ለማገዝ ካህናትም፣የሰንበት ተማሪዎችም፣ ምዕመናንም የተሻለና ዘመኑን የዋጀ አሠራር ለመፍጠር አብረን ብንሠራ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ስለዚህ በአንድ ተሰልፈን ለውጥ ለማምጣት አብረን ብንሠራ የተሻለ ነው በማለት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሙሉ የሥልጠናውን ማንዋል ለማንበብ እዚሁ ላይ ይጫኑ/to read all the training manual click here (leadership and change mgt)