የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

ብፁዕነታቸው “በእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው” እንደገለጹት የጌታችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት ስናከብር ” ሕጻን ተወልደ ለነ ወልድ ተውህበ ለነ” (ት.ኢሳ 9፥6) ሕጻን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና የሚለውን መለኮታዊ ቃል በውስጣችን በማሰብ ማክበር እንደሚገባን መልእክት አስተላልፈዋል።
ክብረ በዓላትን ስናከብር በአንዳንዶች ዘንድ እንደሚታው ሥጋዊ ነገሮች ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ተቆጥበን፤ይልቁንም ከምንም በላይ መንፈሳዊ መልእክቱና ይዘቱ ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል ሲሉም አጽንዖት ሰተው ገልጸዋል።
ዕለቱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የተሰጠበት መሆኑን በማስታወስ፣ ወደ ዓለምም የመጣበት ዓላማ ” ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴዎስ 1፥21)ተብሎ በቅዱሱ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው እርሱ የመጣው ከኃጢአታችን ሊያድነን እንደሆነ፤ ስለ ሁላችንም ብሎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቶ እንዳዳነን፤ ሞትንም ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን በመነሣት በትንሣኤው ሕያዋን እንዳደረገን ከልባችን በማመን በዓሉን ማክበር ይኖርብናል በማለት አብራርተዋል።
እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ከሰጠን እኛ ደግሞ ምግብ ላጡት ምግብ በመስጠት፣ አልባሳት ለሌላቸው አልባሳት በመስጠት፣የታሰሩትን በመጠየቅ፣ወላጅ የሌላቸውን ልጆች በመንከባከብ፣በብቸኝነትና በኃዘን ላይ ያሉትን በመምከርና በማጽናናት በዓሉን ማክበር እንደሚገባን መክረዋል።
አያይዘውም በሀገራችን ብሎም በዓለም ላይ ሰላምን ላጡትና ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ዘርፈ ብዙ በሆኑ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙት ምእመናን ጸሎትን በማድረግ እንድናከብር አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ