የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳሰ ብፁዕ አቡነ መልከፄዴቅ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው በቃሉ ተራራ አቡነ ኃብተማርያም ገዳም የሥራ ጉብኝት አደረጉ
ታኅሣሥ 26 ቀን 2013 ዓ/ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳሰ ብፁዕ አቡነ መልከፄዴቅ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው በቃሉ ተራራ አቡነ ኃብተማርያም ገዳም የሥራ ጉብኝት አድርገዋል። ብፁዕነታቸው በገዳሙ በሌሊት ተገኝተው የነግህ ጸሎተ ኪዳን አድርሰዋል።
በቦታው መልአከ ሕይወት ቆሞሰ አባ ወልደ ኢየሱስ የሀገረ ስብከቱ የካህናት አሰተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የገዳሙ አሰተዳዳሪ ክቡር መላከ ምህረት አበበ የሺንጉሥ፣ የገዳሙ አገልጋዮች ካህናት፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የሰንበት ት/ ቤት አባላትና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል
በዕለቱ የእንኳን ደና መጡ መልክት በገዳሙ አሰተዳዳሪ በክቡር መላከ ምሕረት አበበ የሺንጉሥ የተደረገ ሲሆን በገዳሙ የተሰሩ አጭር ሪፖርትና ሊሠሩ የታቀዱ ሥራዎች በደብሩ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ቀርቧል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ “የጻድቅ መታሠቢያ ለዘለዓለም ነው”፤ ጻድቅ ማለት እውነተኛ ማለት ነው፤ እውነተኛ ማለት ደግሞ ለእውነት የቆመ እውነትን የሚፈልግ ቅዱስ ማለት ነው ካሉ በኃላ እኛም የጻድቁን ፈለግ ልንይዝ ይገባል ብለዋል።
አያይዘውም ቦታው ለቱሪዝም ምቹ በመሆኑ ከመንግሥት ጋራ በመነጋገር የምታደርጉትን ሥራ ሁሉ ሀገረ ስብከቱን የሚያግዝ መሆኑን ልናረግጥላችሁ እንወዳለን በማለት በገዳሙ ላለው የአብነት ትምህርት ቤት መደገፊያ ከግል ገንዘባቸውን 10ሺ ብር ሰጥተዋል።
እንዲህ ዓይነት በጎ ሥራ ከአንድ ብፁዕ አባት የሚጠበቅ ሆኖ ለሌሎች አባቶችም ትልቅ አርአያነታቸውን ማሳየታቸው ይበል የሚያሰኝ በጎ ተግባር ነው።
በመጨረሻም ምእመናን በማስተባበርና ከመንግሥት ጋር በመተባበር በገዳሙ የተሠራ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚያደርስ መንገድና የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
መ/ር ደምስ አየለ የሀገረ ስብከቱ ሚድያ ክፍል ኃላፊ