የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በልደታ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኘው የገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ጎበኙ

ታኅሣሥ 25 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በልደታ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኘው የገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ጎብኝተው ምእመናኑን ባርከዋል። በቦታው መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፣ ሊቀ ትጉኃን ደማሙ የልደታ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሰው ኃይል ክፍል ኃላፊ፣ የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ዘማርያምና በርካታ ምእመናን ተግኝተዋል።
የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ዘማርያም ስለ ገደሙ አመሠራረትና በገዳሙ ያለውን አሁናዊ እንቅስቃሴ አብራርተዋል።
ገዳሙ በ1983 ዓ/ም ተመሥርቶ ገዳመ ኢየሱስ እንደተባለ፤ ገዳሙ ብዙ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን፣ ከነዚህም መካከል የሕጻናት የቀን ውሎ መከታተያና እስከ 6ኛ ክፍል የያዘ ት/ቤት እንዳለውና ት/ቤቱን ወደ ኮሌጅ እንደሚያሳድጉት ገልጸዋል።
በገዳሙ የሚጠመቁ ሕጻናት ዕድሚያቸው አምስት ዓመት ሲሆናቸው ለትምህርት የሚጠሩበት ዳታ ቤዝ ሲስተም(data base system) መዘርጋታቸውን አብራርተዋል።
የመስቀል ቅርጽና (skylight) የጣሪያ ላይ መስኮት ያለው በጣም የሚያምር ህንጻ ቤተ ክርስቲያን እየገነቡ እንደሆነም አብራርተዋል። ከዚህ ጋር አያይዘውም ዋና ዓላማችን የሰውን አእምሮ በወንጌል ማነጽና በመንፈሳዊ ትምህርት ኮትኩቶ በማሳደግ ማብቃት ነው ብለዋል።
በመቀጠልም በደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በበገና የታጀበ “የአባታችን ሆይ” መዝሙር ቀርቧል።
ዕለቱን በተመለከተ ትምህርት በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የተሰጠ ሲሆን “አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር፡ መልካም እረኛ እኔ ነኝ” (ዮሐ 10፥11) በሚል መነሻነት ስለ መልካም እረኛ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው የመልካም እረኛ ዋና ዋና ሥራዎች በጎቹን ማሰማራት፣ መመገብና መጠበቅ ናቸው፤ እግዚአብሔርም እነዚህን ሁሉ አድርጎልናል ብለዋል።
ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚመጡበት ዋና ዓላማ ቃሉን ለመማርና በተማሩት ትምህርት ጸንተው ለሥጋሁና ደሙን በቅተው በጽድቅና በቅድስና እየተመላለሱ እንዲኖሩ መሆኑን አብራርተዋል።
በገዳሙ እየተከናወኑ ያሉት መንፈሳዊና ማሕበራዊ የልማት ስራዎችን የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና ዓላማ የሚያስቀጥል መሆኑን በማውሳት ለገዳሙ አስተዳዳሪ መ/ገነት ዘማርያም ሳያመሰግኑ አላለፉም። በተለይ በመንፈሳዊና በዕውቀት ተኮር ዙርያ ላይ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በእጅጉን አመሥግነዋል። “ሰውና ሥነ ምግባሩ” የሚል መጽሐፋቸውን አይተው ከአንድ መሪ የሚጠበቅና ቆንጆ መጽሐፍ መሆኑን ለምእመናኑ ገልጸዋል።
ሥራውን በይበልጥ ለማስቀጠል የጀመሩትን እንቅስቃሴ በብርታት መቀጠል እንዳለባቸው፤ በተለይ ለአገልጋዮች ተከታታይ ሥልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል።
በመጨረሻም አዲሱን እየተሠራ ያለውን ህንጻ ቤተ ክርስቲያንና የህጻናት ትምህርት ቤት ጎብኘተዋል፤ አሠራሩ እጅግ የተለየና ያማረ መሆኑን መስክረዋል።
መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ