የአየር ጤና አንቀጸ ብርሃን ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በታላቅ ድምቀት ተከበረ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር የምትገኘው የአየር ጤና አንቀጸ ብርሃን ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በዐል ሰኞ ጥር 19 ቀን 2006 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡር ሊ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ከአምስት መቶ ሺ በላይ የሚገመት ቁጥር ያለው ማህበረ ምዕመናን በተገኙበት የተከበረ ሲሆን ለበዐሉ የሚስማማ ያሬዳዊ ወረብ በሊቃውንቱ እና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ቀርቧል፡፡
በማያያዝም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ናትናኤል መልአኩ የሚከተለውን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ ቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ክቡራን ሕዝበ ክርስቲያን ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ ወደ ተራራውም ውጡ እንጨትንም አምጡ ቤቴንም ሥሩ ተብሎ በነቢዩ ሐጌ በተላለፈልን አምላካዊ ቃል መሠረት የአየር ጤና አንቀጸ ብርሃን ኪዳነ ምህረት የአጥቢያ ነዋሪ አምላካዊ ቃሉን እና የሀገረ ስብከቱን መመሪያ በመቀበል ይህንን የምታዩትን ታላቅና ግሩም የሆነውን የእግዚአብሔርን ማደሪያ ሠርተው ለዚህ ደረጃ ሲደርስ የእግዚአብሔርን ቤት አሳምሮና አስጊጦ የእጅ ስራውን እንደ ጠቢቡ ንጉሥ እንደ ሰለሞን ሁሉም ነገር ስለተትረፈረፈለትና ስለሞላለት ሳይሆን ደግሞም እንደ ድሮው ዘመን ከቤተ መንግሥቱ የተበጀተለት በጀት ኑሮ ሳይሆን የአካባቢው እና አንድ አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በጐ አድራጊዎች ከራሳቸው እና ከልጆቻቸው ምግብ ላይ በመቀነስ የሥጋ ፍላጐት ጐደሎ ከመሟላቱ በፊት የእግዚአብሔር ቤት ሊሠራ ይገባዋል በማለት በቆራጥነት እና በፍጹም ተነሳሽነት የእግዚአብሔርን ቤት ጀምሮ ለዚህ ያበቃ ታላቅ ሕዝብ መሆኑ እንዲሠመርበት እፈልጋለሁ፡፡
ሌላው በትኩረት እንዲደመጥልኝ የምፈልገው ጉዳይ ይህ የተሠራው ታላቅ እና የዘመኑ ቴክኖሎጂ ወቅቱ ባፈራቸው ጠበብት እጅግ አምሮና ተውቦ የተሠራው ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳን በአሁኑ ሰአት ያላለቁ እና ሊሠሩ የሚገባቸው እጅግ ብዙ ስራዎች ቢኖሩትም እነዚህን ያለተሟሉትን ሥራዎች በቅርብ ጊዜ ማሟላት የምንችል መሆኑን ኃላፊነቱ የሚመለከተን ሁሉ ከሀገረ ስብከቱ መመሪያዎችን እየተቀበልን ሀላፊነቱን የምንወስድ ሆኖ ህንፃው ግን የካቴድራል ደረጃና ስም እንዲሰጠው ስል በአክብሮትና በታላቅ ትህትና ከእግረ መስቀልዎ ሥር በመሆን በካህናቱ እና በአጥቢያ ህዝበ ክርስቲያን ስም እጠይቃለሁ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ በቅዱስነትዎ ዘመነ ፕትርክና ይህ ታላቅ እና ግዙፍ ሕንፃ ለዚህ ደረጃና ለቡራኬ መድረሱ ቅዱስነትዎ ዕድለኛ መሆንዎን ያሳያል ብፁዕ አባታችን አቡነ እስጢፋኖስ እና የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የሀገረ ስብከት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን ወልደ ሰንበት አለነ እና የየመምሪያው ኃላፊዎች መመሪያ እየሰጣችሁ ከጐናችን ሳትለዩ ከህዝቡ እና ከሰበካው ጋር አስፈላጊ በሆኑ ጊዜያቶች እየተገኛችሁ ችግሮችን ሳይውሉና ሳያድሩ እየፈታችሁ ለፍጻማው ትጓጉለት የነበረው የአየር ጤና አንቀጸ ብርሃን ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በቅዳሴ ቤቱ በዓል ላይ ደርሳችሁ ሀሳባችሁ ሀሳቦችን ምኞታችሁ ምኞታችን በመሆኑ እና የሁላችንም ሀሳብ ስለተሳካ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩኝ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክቴን ከዚህ ላይ እቋጫለሁ በማለት የእንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ከዚሁ ጋር የደብሩ የሰበካ ጉባዔ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አዲስ መርሻም በበኩላቸው የህንፃውን የሠራ ሪፖርት ሰፋ አድርገው ከገለፁ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ጊዜአችሁን፣ ገንዘባችሁን በማውጣት እና በመሰዋት ይህንን ቤተ ክርስቲያን በመሥራታችሁ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ ምኞታችሁ ከግብ ደርሶ የዚህን አስደናቂ ቤተ ክርስቲያን ፍጻሜ በማየታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡
ይህ ህንፃ ቅዱስ ቁርባን የሚሰጥበት፣ ጸሎት የሚደረግበት፣ በመሆኑ እግዚአብሔር ይደሰትበታል እኛም ደስ ብሎናል፡፡ እኛ ዛሬ በዚህ ቦታ ላይ በመገኘታችን ደስ ብሎናል ህንፃውም ወደ ቤተ ክርስቲያንነት ተለውጧል፡፡ ይህ ህንፃ ለእናንተ መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ሥራ የሠራችሁት እምነታችሁ ቀስቅሶአችሁ ነው፡፡ ይህንን ታሪካዊ ቤት በመሥራታችሁ ታሪካውያን ናችሁ ቀሪውን ሥራ እንደምትፈጽሙት እምነታችን ነው፡፡ ሥራው የተሠራው በመካከላችሁ የሠመረ ህብረት ስላለ ነው ሃይማኖታችሁም የጠበቀ ነው፡፡ ይህ ህንፃ ለሚመጣው ትውልድ የሚተላለፍ ሀብት ነው፡፡ ልጆቻችሁን አስተምሯቸው ሰውነትን ከሚጐዳ፣ አእምሮን ከማያናውፅ ነገር እንዲርቁ አድርጉአቸው ህፃናቱ የእናንተን ፈለግ እንዲከተሉ የማድረግ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ ዛሬ በዘመናችን አንድ አንድ አስከፊ ነገሮች እየታዩ ናቸው፡፡ ልጆቻችሁ ወደ አረብ ሀገር እየሄዱ ሕይወታቸውን እና ገንዘባቸውን እያጡ ነው ያሉት መብትም የላቸውም፣ ዳኝነትም የሚአይላቸው የለም ከእነሱ ትምህርት ውሰዱ በሀገራችሁ ሠርታችሁ አግኙ እንጂ ዋስትና ወደ ሌለበት ሀገር አትሂዱ ወደ ዛሬው በዓላችን ስንመለስ ወገኖቻችን ለዚህ በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡ ይህ አዲሱ ህንፃ ካቴድራል ተብሎ እንዲሰየም የደብሩ አስተዳዳሪ እናንተን ወክለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ቤተ ክርስቲያኑ ትልቅ ሥራውም ትልቅ ሆኖ አይተነዋል ምንም እንኳን አንድ አንድ ያልተሰሩ ሥራዎች ቢኖሩትም ያንን እንደምታሟሉት በማመን እና ከዚህ የበለጠ ዕለትም ስለማይኖረን ከዛሬ ጀምሮ ካቴድራል ብለን ሰይመነዋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ስም ቢኖርም እንሰጠው ነበር፡፡
በማለት ቅዱስነታቸው እጅግ አስደሳች የሆነ አባታዊ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ በጸሎት እና በቃለ ምዕዳን የቤተ ክርስቲያኑ የቅዳሴ ቤት ኩራኬ በዐል ተጠናቅቋል በማግሥቱም ጥር 20 ቀን 2006 ዓ.ም የቅዳሴ ቤቱ በዓል በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል፡፡
{flike}{plusone}