የአክሱም ጽዮን ዶክመንተሪ ፊልም ተመረቀ
“አክሱም ጽዮን የሁለቱ ኪዳናት ማኅደር” በሚል ርእስ ታሪካዊ ዶክመንተሪ ፊልም የካቲት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የቅርስና ጥናት ባለሥልጣን ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ የአክሱም ጽዮን ንቡረ እድና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተመረቀ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ግንባታ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስተባባሪነት የተዘጋጀው ይህ ዶክመንተሪ ፊልም በአክሱም ጽዮን እየተገነባ ለሚገኘው ቤተ መጻሕፍትና ወመዘክር ሕንፃ ማጠናቀቂያ ገቢ ማስገኛ እንዲውል ሲሆን፤ ከገቢ ምንጭነቱ ባለፈም ታሪካዊ ዶክመንተሪ ፊልሙ መቅረቡ ለእምነቱ ተከታዮች፣ ለሃይማኖትና ለታሪክ ተመራማሪዎች ከፍተኛ መረጃ ይሰጣል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምእዳን “ከጥንት ጀምሮ ከአባቶቻችን በመጣው መንፈሳዊ ሥርዓት መሠረት የተዘጋጁት ልዩ ልዩ የወርቅና የብር መስቀሎች፤ ዘውዶችና የብራና መጻሕፍት ከልዩ ልዩ ጎጂ ነገሮች ያልተጠበቁ ናቸው፡፡ ዓለምን የሚያስደንቁት እነዚህ ቅርሶች ከአባቶቻችን እንደተረከብነው ለትውልድ የማስተላለፍ ሓላፊነት አለብን፡፡ ይህ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ግንባታው መጀመሩም ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ የታሪክና የቅርስ ማኅደር እንዲኖራት የሚያስችል ነው፡፡ ቅርሶቹ ዓለምን የሚያስደንቁ በመሆናቸውለሀገራችንና ለሃይማኖታችን ክብር የሚሰጡ፤ ለቀደምትነታችንና ለታላቅነታችን ምሥክሮች ናቸው” ብለዋል፡፡
በምረቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ግንባታ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ሰሎሞን በቀለ ባቀረቡት ሪፖርት “አባቶቻችን ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩበትና ኢትዮጵያ ሀገራችን የሥልጣኔ ቁንጮ ያስደረጉበት ዘመን ቢያልፍም የማያልፈውንና ዘመን የማይሽረውን ታሪካቸው ግን በአክሱም ሐውልቶች፤ በቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፤ በጎንደር አብያተ መንግሥታት ግንባታዎችና ሌሎችም ቅርሶቻችን ጎልተው በመታየት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ አስደናቂ ቅርሶች በተጨማሪ በአክሱም ከአንድ ሺሕ በላይ የብራና መጻሕፍት፤ የወርቅና የብር መስቀሎች፤ ሌሎችም የሚገኙ ቢሆንም ለደኅንነታቸው እጅግ አሳሳቢና አስጊ በሆነ ሁኔታ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ የዘመኑ ትውልድ የአባቶቹን ገድልና የሥራ ፍሬ በመጠበቅ እርሱም ታሪክ ሠሪ እንዲሆን ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ ተግባራት እንዲፈጽም የሚያስገድዱት በመሆኑ እነዚህን ቅርሶች ከደረሰባቸው አሳሳቢ ሁኔታ በማውጣት በተደላደለና ምቹ ሥፍራ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል” ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ የፈቀደውን ብር ጨምሮ 68 ሚሊዮን 574 ሺሕ 156 ብር ከ20 ሣንቲም ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 63 ሚሊዮን 901 ሺሕ 450 ብር ከ70 ሣንቲም ወጪ በማድረግ የግንባታውን 70 በመቶ ለማጠናቀቅ መቻሉን ቀሲስ ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡
ቀሪውን 30 በመቶ ግንባታ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ሰፊ ትኩረት ከሰጣቸው ዘዴዎች ዋነኛው በዛሬው እለት በይፋ የሚመረቀው “አክሱም ጽዮን የሁለቱ ኪዳናት ማኅደር” በሚል የተዘጋጀው ዶክመንተሪ ፊልም መሆኑን የገለጹት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሳቢ የተጀመረውን ግንባታ ለማጠናቀቅ ዶክመንተሪ ፊልሙን ከማሰራጨት ጀምሮ በሌሎችም ፕሮጀክቶች በመሳተፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዶክመንተሪ ፊልሙ የተዘጋጀበት ምክንያትና ዋነኛ ዓለማ አስመልከቶ ማብራሪያ የሰጡት መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በዓይነቱ፤ በይዘቱ፤ እና በአመሠራረቱ በሀገራችን ለየት የሚለውና የመጀመሪያ የሆነውን ሙዚየም ግንባታ በሰፊው ለማስተዋወቅ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ሙሉ ሀሳብ፤ የሙያ፤ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማግኘት ታስቦ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የዶክመንተሪ ፊልሙ አሠራርን በተመለከተም አስፈላጊ ናቸው የተባሉ የታሪክ ቅደም ተከተል የዳሰሳ ጥናት ማድረግ፤ በአክሱም ያለውን በየዘመኑ የተከሰቱ ታሪኮች በአጭሩ መዳሰስ፤ ቃለ መጠይቆችን፤ የሙዚየሙ ግንባታ አጀማመርና አሁን ያለበት ደረጃ፤ የመስክ ጉብኝትና መረጃ ማሰባሰብ ሥራ፤ ለዶክመንተሪ ፊልሙ ጥናታዊ ጽሑፍ የማዘጋጀት፤ ታሪካዊ ቦታዎች የድምጽ ወምስል ቀረጻ ማድረግ፤ የታሪክ፤ የቀረጻ፤ የሥነ ጽሑፍ ዝግጅት፤ የእርማት፤ የድምጽ ትረካና ቀረጻ፤ ፊልም ቅንብር፤ ክትትልና ዳይሬክቲንግ ሥራዎች በመሥራት ለዛሬው ምርቃት ማብቃት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
{flike}{plusone}