የአንጋፋው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሁለገብ ሕንፃ ተመረቀ
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ(MA)
ኮሌጁ ያስገነባው እጅግ ዘመናዊ ሁለገብ ሕንፃ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ መምህር ጎይትኦም ያይኑ እና የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የኮሌጁ ማኅበረ ሰብ በተገኙበት ጥር 26/2010ዓ.ም በታላቅ ምንፈሳዊ ሥነ ሥርዓትና እጅግ ባማረ ሁኔታ በቅዱስነታቸው ፀሎተ ቡራኬ ተመርቋል፡፡
በዚሁ እለት ቅዱስነታቸው በዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የኮሌጁ የበላይ ኃላፊና በመ/ር ግርማ ባቱ የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲን አማካኝነት በእለቱ የተመረቀውን አዲሱ ሁለገብ ሕንፃ ዞረው ጎብኝተዋል፡፡
የእለቱን መርሐ ግብር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በፀሎት የከፈቱት ሲሆን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ካህናትም ፀሎተ ወንጌል አድርሰዋል፡፡
የልማት አባት የሆኑት ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የኮሌጁ የበላይ ኃላፊ የእንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን መንፈሳዊ ኮሌጁ ከብዙ ውጣ ውረድ ለዚሁ እለት መድረሱ እግዚአብሔርን ካመሰገኑ በኋላ ለዚሁ ወርቃማ ሥራ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉ ቅዱስ ፓትርያርኩን፣ የኮሌጁ የቦርድ ሥራ አመራር፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ለሥራው ከፍተኛ ሙያዊ እገዛ ላደረጉ ባለሙያዎ እና ለኮሌጁ ማኅበረ ሰብ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ብፁእነታቸው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሃያ ዓመት እመርታ የህንፃ ምረቃ ልዩ እትም በሚል መጽሔት ባስተላለፉት መልእክት”ያቀዱት ሲሠምር የወጠኑት ሲሳካ የሚኖረው ደስታ ከቃላት ሁሉ በላይ ነው፤ይህ የሥራ ፍሬ የረጅም ጉዞና የአድካሚ ውጣ ውረድ ውጤት እንጅ በፍላጎት ብቻ የመጣ ቀላል ነገር አይደለም፤ለትልቅ ሥራ የሚነሳ ሰው የማይናውጥ የዓላማ ጽናት ያስፈልገዋል፤እንደ አንድ የትምህርት ተቅዋም ኮሌጃችን እየሄደበት ያለው የልማት ጎዳና በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያናችን ያለው የትምህርት ሥርጭት ትርጉም ባለው መልኩ ያሳድገዋል”በማለት ሰፊ እና አስተማሪ የሆነ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ከብፁእነታቸው በመቀጠል ስለ ሥራው አስመልከተው አጠቃላይ ሪፖርት ያቀረቡት የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲን መ/ር ግርማ ባቱ ሲሆኑ ” በዛሬው እለት ለምረቃ የበቃው ባለ4 ፎቅ ሁለገብ ግዙፍ ሕንፃ በነበሩት ተደራራቢ ችግሮች ለዚህ ይደርሳል ብሎ ማሰብ ከባድ የነበረ መሆኑን ገልፀው በኮሌጁ ቁርጠኝነትና ጽኑ ዓላማ ሁሉን አልፈን ለዚሁ ስኬት በቅተናል፤ይህ ስኬት የሕንፃ ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ከማብቃት አንፃር የሚገለጽ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያናችን የሚያስፈልጋትን የትምህርት ተቋም ከማደራጀትና ከማሳደግ አንፃርም ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያለው ነው፤በዚሁ መሠረት ሕንፃው የተሠራበት ዓላማ 50% ለኮሌጁ ተጨማሪ ገቢ ሲሆን 50% ደግሞ ለመማር ማስተማር ሂደት የሚውል ነው ብለዋል፡፡ሕንፃው ለመጠናቀቅ 4 ዓመታት መውሰዱን ገልፀው ለዚሁ ታሪካዊ ሥራ እገዛ ያደረጉትን ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ባለፉት 4 ዓመታት ከግንባታው ጎን ለጎን ኮሌጁን ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ላማሸጋገር የሚያስችሉ ጥናቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመው በዚሁም መሠረት ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ በሚል ስያሜ በሥሩ 5 ኮሌጆች እንደሚኖሩ በሪፖርታቸው ገልፀዋል እነዚህም፡-
1.የትምህርተ መለኮት ኮሌጅ/College of Theology
2.የነገረ ሰበእና የማህበረሰብ ሳይንስ ኮሌጅ/ College of Social Science and Humanities and Fine Arts
3.ቅዱስ ያሬድ የፀዋትወ ዜማና የሥነ-ጥበብ ኮሌጅ/ St.Yared’s College of Hymnology
4.የሕዝብ አስተዳደር እና የሥራ አመራር ኮሌጅ/ College of Management & Public Administration
5.የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ትምህርት ቤት/ School of Higher Education Studies መሆናቸውን ገልፀው የዚሁም ዓላማ ለቤተ ክርስቲያናችን ሁሉን አቀፍ አገልግሎት፣ዘርፈ ብዙ እውቀትና ክህሎት ይዘው የሚገኙ አገልጋዮችን ማበርከት መሆኑን ገልፀው፤ይህን ለማሳካት እህታችን ከምትሆን ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በተፈፀመ ስምምነት በታዋቂ ተቋምና ምሁራን የ3ኛ ዲግሪ/ዶክትሬት መርሐ ግብር መስጠት እንደሚጀመር በዚሁ ሪፖርታቸው አብስረዋል ፡፡”
በዚሁ እለት ለሥራው እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለደረጉ አባቶችና ወንደሞች የምስጋና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን በኮሌጁ አማካኝነት፤ በሰሜን ሆቴል አቅራቢነት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ሁሉ በኮሌጁ አዲሱ ሕንፃ ምሳ ተጋብዘዋል ፡፡
በመጨረሻም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ትምህርትና ፀሎተ ቡራኬ የእለቱን መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡