የአቃቂ ቃሊቲ የጥምቀት ባህር ቦታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይዞታ ሆኖ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ፈቃድ ሰጠ

የአቃቂ ቃሊቲ የጥምቀተ ባህር ቦታ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትና በክቡር አቶ ደሪባ ኩማ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ከንቲባ የጋራ ምክክርና ውይይት በኋላ 25ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የጥምቀተ ባህር ቦታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ ሆኖ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፈቃድ የሰጠ በመሆኑ ሰኞ ጥር 9 ቀን 2008 ዓ.ም ከመቶ ሺህ በላይ የሚገመት ምዕመናን፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመገኘት የጥምቀት ሥርዓት በሚፈጸምበት ቦታ ላይ የተጀመረውን የሐውልት ግንባታ ባርከው ሪቫን ቆርጠዋል፡፡
በክርክሩ  ወቅት ከፍተኛ ዕገዛ ሲአደርጐ የነበሩት የአቃቂ ቃሊቲ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ አባ ኃይል መለኮት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደገለፁት በአቃቂ ቃሊቲ ከሚኖረው ነዋሪ ሕዝብ መካከል 81% የኢ.ኦ.ተ.ቤ. እምነት ተከታይ ነው፡፡ የጥምቀተ ባህሩ ቦታ የቤተክርስቲያናችን ይዞታ ሆኖ እንዲቀጥል በብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩ ለመንግሥት የተጻፉት ደብዳቤዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲመጣ አድርገዋል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ደሪባ ኩማና ሌሎችም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለቀረበው አቤቱታ አውንታዊ ምላሽ በመስጠታቸው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቋሚ አባላትና አፈ ጉባኤዎች ከቦታው ድረስ በመምጣት አቤቱታውን በማዳመጥ ተገቢ የሆነ እገዛ አድርገዋል የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች የፖሊስ መመሪያ ኃላፊዎች እና የፍትሕ ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን አሳይተዋል በክርክሩ ወቅት የነበረው የምዕመናን ስሜት የጋለ ቁጣ፣ ያለመረጋጋትና ግራ የመጋባት ነበር፡፡የአካባቢው ወጣቶች የላቀ ትዕግሥት አሳይተዋል ብለዋል::

ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በአስተላለፉት መልእክት በዚህ ቦታ ላይ ተገኝተን በቅዱስ አባታችን እንድንባረክና በውጤታችን እንድንረካ ያደረገን አምላካችን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት ክፍላተ ከተማ ትልቅና ሰፊ ክፍለ ከተማ ነው በ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት በሥራ አፈጻጸም ከፍተኛ ለውጥ  በማምጣት በቅዱስነትዎ የተሸለመ ክፍለ ከተማ ነው በዚህ ክፍለ ከተማካሉት ገዳማትና አድባራት ውስጥ በዚህ ቦታ ላይ ለበርካታ ዓመታት የጥምቀት በዓልን ሲአከብሩ ኖረዋል ቅዱስነትዎ ከክቡር ከንቲባ ደሪባ ኩማ ጋር ከጥንት ጀምሮ የጥምቀተ ባህር ቦታ የነበረ መሆኑን መስክረዋል ይህ ጥያቄ እንዲመለስ በቅዱስነትዎ የሚሰጥዎን መመሪያ ተከትለው ሥራውን ለውጤት ያደረሱትን ሁሉ ለማመስገን እወዳለሁ፡፡
መንግሥት የሕዝብ ነው የሀገራችን ሕዝቦች በየ5 ዓመቱ ያቋቋሙትን መንግሥት በመተማመን ጥያቄአችንን ይዘን እንሄዳለን:: መንግሥትም ይህን አካሄድ ተቀብሎ የችግሩን ሁኔታ ተገንዝቦ ተገቢ ምላሽ ሰጥቶናል::ክቡር አቶ ደሪባ ኩማ የአደስ አባባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እንዲመሰገኑልኝ በዚህ ታላቅ ሕዝብ ስም እጠይቃለሁ፡፡በማንኛውም ሥራችን ከጎናችን የማይለዩትን ኮማንደር መኮንን አሻግሬን ላመሰግን እወዳለሁ የክፍለ ከተማውን ኃላፊና ሌሎችንም የሥራ ሂደት ኃላፊዎች ላመሰግን እወዳልሁ አቶ ሙሉጌታ አስፍንም ላመሰግን እዋዳለሁ ከቤተክርስቲያችን ሊቃውንት አንዱ የሆኑትንና የክፍለ ከተማ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አምኃ መኳንንት ውጤታማ የሆነ ሥራ በመሥራታቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል በማለት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልክታቸውን አስተላልፈል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩ ለተሰበሰበው በርካታ ምዕመናን ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት በዚህ የሰላም ጉዞ የተባበሩን አቶ ደሪባ ኩማ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ዋና ከንቲባ ኮማንደር መኮንን አሻግሬ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ፍትሕ ቢሮ የፀጥታ አስተዳዳር ጉዳዩች ዋና ሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ሙሉነህና ሌሎችም የሰላም ተባባሪዎችና የቤተክርስቲያን መብት አስከባሪዎች እግዚአብሔር አምላካችን በበረከቱ ይባርካቸው
በዚህ አካባቢ የምትኖሩ ማህበረ ምዕመናንም ሃይማኖታችሁ አንድነታችሁና ፍቅራችሁ በዓለም ተሰምቶአል ሁሉ ነገር የሚገኘው በፍቅር ነው ወጣቶቹም ሽማግሌዎቹም ድርሻችሁን ስለተወጣችሁ በቤተክርስቲያናችን ስም እናመሰግናችኋለን፡፡
ይህ ቦታ ለብዙ ዘመን የእግዚአብሔር ስም የሚጠራበት ቦታ ሆኖ ቆይቷል በቀጣዩም የእግዚአብሔር ስም የሚጠራበት ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ሀገር ሰላም እንዲሆንና ፀጥታ እንዲሰፍን ቤተክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ተሰልፋ ትኖራለች መንግሥት የቤተክርስቲያን ቦታ እንዲከበር በማድረጉ እናመሰግነዋልን ዛሬ ከዚህ ቦታ የመጣነው በጥምቀት ዕለት መምጣት ሰላልቻልን ነው ብዙ የተደከመበትና የተጸለየበት የሥራ ውጠት በመሆኑ ነው ቀድመን ለመምጣት የቻልነው የተሠራው ሥራ እግዚአብሔርም ሰውም የሚደሰትበት ሥራ ነው በአሁኑ ጊዜ ልማት እየተፋጠነ ነው ሁላችሁም ይህንን ልማት መደገፉ አለባችሁ የልማት ቃል ኪዳናችን እንዳይታጠፍ ከመንግሥት ጐን በመሰለፍ ሀገራችንን ማልማት አለብን ችግሮችን በውይይትና በምክክር ብቻ መፍታት ይገባል፡፡በዚህ ሰላም ትብብር ያደረጉት ሁሉ እግዚአብሔር ይባርካቸው በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ ቡራኬና መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በሌላ ዜና ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩ በዚህ ዕለት ከብፁዓን አባቶች፤ ከሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስና ከሌሎች ልዑካን ጋር ከአቃቂ ቃሊቲ በቀጥታ ወደ ሰአሊተ መሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል የጥምቀተ ባህር ቦታ ወደ ሆነው ቦታ በማምራት በአንድ አንድ ኃላፊነት የጎደላቸው የክፍለ ከተማው የመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል የሕዝብ መገልገያ በሆነው የጥምቀተ ባህር ቦታን አስመልክቶ የሚሠነዘረው አሉታዊ አስተሳሰብ በትዕግሥትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተገቢ ምላሽ ለማግኘት የሚቻል መሆኑን ቅዱስነታቸው ለምዕመናን በመግለጽ ቦታው የእግዚአብሔር ስም የሚጠራበትና የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታ ሆኖ እንዲቀጥል ባርከነዋል በማለት ቡራኬአቸውን አስተላልፈዋል፡፡
{flike}{plusone}