የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት “አገልግሎቴን አከብራለሁ” በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ የምስጋና የእውቅና መርሐግብር አካሄደ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት “አገልግሎቴን አከብራለሁ” ( ሮሜ 11፥13-14) በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ ኅዳር ፳፬ /፳፻፲፰ ዓ/ም በቃሊቲ መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት የምስጋና የእውቅና መርሐግብር አካሄደ።
በመርሐግብሩ ላይ ክቡር መልአከ ገነት ልሳነወርቅ ተስፋ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት አቅርበዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ በክፍለ ከተማው ቤተክህነት ጽ/ቤት ስር 27 አድባራትና ገዳማት እንደሚገኙ ገልጸው በመልካም አስተዳደር፣በስብከተ ወንጌል፣በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ፣ በትምህርትና ሥልጠና፣ በሒሳብና በጀት ክፍል፣በቁጥጥር ክፍልና በሌሎችም የሥራ ዘርፎች የተሠሩትን ሥራዎች ዕጥር ምጥን አድርገው አሰምተዋል።
አድባራቱና ገዳማቱ ባለፈው በጀት ዓመት በግጭት አፈታት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት፣በራስ አገዝ ልማት፣ሕንጻ ቤተክርስቲያንን በወራት ጊዜ ውስጥ ሠርቶ በማጠናቀቅ፣የይዞታ ማስፋፊያ በማድረግ፣ፐርሰንትን በወቅቱ በመክፈል፣ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለሠሩ፣ በትምህርተ ኖሎትና ሥልጠናዎችን ለካህናት በመስጠት ላስመዘገቡት ውጤት የምስጋና የእውቅና ሰርተፊኬት ከብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ በክፍለ ከተማው ቤተክህነት ጽ/ቤት መሪነት በአድባራቱና በገዳማቱ በመንፈሳዊው አገልግሎትና በልማት ሥራው ለተመዘገበው ውጤት አመስግነዋል።
ወደፊትም ከዚህ የበለጠ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲካሄድና የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል።
ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገ/መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ባስተላለፉት መልእክት የክፍለ ከተማው ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች ከአድባራቱና ገዳማቱ ጋር ተቀራርበው በፍቅርና በሰላም መሥራታቸው የሰማናቸው ውጤቶች እንዲመዘገቡ አድርጓል ብለዋል።
ዘመኑን በመዋጀት የተጣለብንን መንፈሳዊ አደራ በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገ/መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ክቡር መልአከ ገነት ልሳነወርቅ ተስፋ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣መጋቤ ሐዲስ ጊዜው አሸናፊ የክፍለ ከተማው ቤተክህነት የሰው ኃይል አስተዳደር፣የክ/ከ/ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ምክትል ሊቃነ መናብርት ተገኝተዋል።