የአስተዳደር በደል ደርሶብናል በሚል ቅሬታ ያቀረቡ የአብያተ ክርስቲያናት ሠራተኞች ጉዳይ በሀገረ ስብከቱ ውሳኔ እንዲፈጸም ልዩ ጽ/ቤት መመሪያ አስተላለፈ

0122

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚያስተዳድራቸው የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተለያየ የሥራ መደብ ተሠማርተው ከሚሠሩት በርካታ ሠራተኞች መካከል ቁጥራቸው ከ20 የማይበልጡ ሠራተኞች የአስተዳደር በደል ደርሶብናል በሚል ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት አቤቱታ ሲያቀርቡ የቆዩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ገዳያቸው በሀገረ ስብከቱ በኩል ተጣርቶ እንዲላክ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ባሰተላለፈው መመሪያ መሠረት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቁጥር 999/546/09 በቀን 19/5/2009 ዓ.ም በተጻፈ መሸኛ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የተላከው ውሳኔ እንደሚገልጸው ደመወዛቸው ተቀንሶ የተዛወሩት የሁለት ዋና ጸሐፊዎች ደመወዝ እንዲስተካከል፣ በመደበኛ ፍ/ቤት ክስ የመሠረቱ ክሳቸውን ዘግተው የይቅርታ ጽሑፍ ሲያቀርቡ በሥራ እንዲመደቡ፣ ቀላልና ከባድ ጥፋት የሚታይባቸው ሌሎች ሠራተኞች አድራጎታቸው እየተመረመረ እንደ ሁኔታው ሊፈጸም የሚችል መሆኑን አብራርቶ ያስረዳል፡፡
በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተመድበው ከሚሠሩት ሠራተኞች መካከል የአስተዳደር በደል ደርሶብናል ብለው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ቅሬታ ያቀረቡት ሠራተኞች፡-
ሊቀ ሥዩማን ተስፉ ደጀኔ፣ መልአከ መዊዕ በቃሉ ያለው፣ ሊቀ ሥዩማን ደነቀ ተሾመ፣ መጋቤ ሃይማኖት ስምዖን ነጋሽ፣ ርዕሰ ደብር ፍሥሐ ትኩዕ፣ መጋቤ ሥርዓት ዮሐንስ አሰሙ፣ መ/መንክራት አባ ሥምረተ አብ እሸቱ፣ ዲያቆን ጸጋዬ ካሣሁን፣ ዲያቆን ካሣሁን ደሳለኝ፣ ዲያቆን ብርሃኑ ተረፈ፣ መ/ሃ መንግሥቱ ደረሰ፣ መ/ስብሐት ዓለማየሁ አምሳል፣ ሊ/ስ ሙሉጌታ መኮንን፣ መምህር አዳም አእምሮ፣ መሪጌታ ኅሩይ ዓለማየሁ፣ መ/ር ቀለመወርቅ ተመስገን፣ ቄስ ሲሳይ ቸኮል፣ መምህር ዓቢይ ዝቢ፣ ቄስ ፍቅረ ዮሐንስ ሀብተ ሚካኤል፣ ዲያቆን ዮሐንስ ተ/ጻድቅ  ሲሆኑ ከሀገረ ስብከቱ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት በተላከው ውሳኔ መሠረት ደመወዛቸው ተቀንሶ የተዛወሩት የሁለት ዋና ጸሐፊዎች ደመወዝ እንዲስተካከል፣ በመደበኛ ፍ/ቤት ክስ የመሠረቱ ክሳቸውን ዘግተው የይቅርታ ጽሑፍ ሲያቀርቡ በሥራ እንዲመደቡ፣ ቀላልና ከባድ ጥፋት የሚታይባቸው ሌሎች ሠራተኞች አድራጎታቸው እየተመረመረ እንደ ሁኔታው ሊፈጸም የሚችል መሆኑን በመግለጽ እና የሀገረ ስብከቱን የአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ በመደገፍ አፈጻጸሙ እንዲገለጽልን ይደረግ በማለት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት በቁጥር ል/ጽ/202/116/2009 በቀን 29/5/2009 ዓ.ም የተጻፈ መመሪያ አስተላልፏል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትም ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ጸድቆ የተላለፈለትን መመሪያ በመቀበል በዝውውር ሂደት ወቅት ደመወዝ የተቀነሰባችሁ ካላችሁ መረጃችሁን በማቅረብ እንዲስተካከል፣ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ የመሠረታችሁ ክሳችሁን ዘግታችሁ የይቅርታ ጽሑፍ ስታቀርቡ በሥራ እንደምትመደቡ፣ ቀላልና ከባድ ጥፋት የሚታይባችሁ ሌሎች ሠራተኞች ጉዳያችሁ እየተመረመረ እንደ ሁኔታው እየታየ ይፈጸምላችኋል በማለት የግለሠቦቹን ስም ዘርዝሮ ግልጽ ማስታወቂያ አውጥቷል፡፡
በሌላ ዜና የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጥር 27 ቀን 2009 ዓ.ም ባወጣው ጽሑፍ ላይ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ታምራት ዳግማዊት ጻድቃኔ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ሠራተኞች ለተፈቀደላቸው የደመወዝ ጭማሪ ማጽደቂያ ለሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎች የተሰጠው ብር 50,000 (ሃምሳ ሺህ ብር) ጉቦ እንዲመለስ ታዘዘ በሚል ለሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎች ለዋና ሥራ አስኪያጅ እና ለሂሳብ እና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ሳይሰጥ እንደተሰጠ አስመስሎ አስነብቧል፡፡
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኗ ካላት ከማንኛውም ገቢ ላይ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት 20% እንድትከፍል በቃለ ዐዋዲው በተደነገገው መሠረት ከደብሩ የተላከው ብር 50,000 (ሃምሳ ሺህ ብር) የፐርሰንት ክፍያ እንጂ ጉቦ አለመሆኑን በመግለጽ እና ገንዘቡ ወደ ባንክ የገባበትን የባንክ ደረሰኝ ፎቶ ኮፒ በማያያዝ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቁጥር 1185/546/2009 በቀን 02/06/2009 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ይሄንን ገልጾ ማስተባበያ እንዲጽፍ አሳስቦታል፡፡