የአርሲ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል አረፉ

0029

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ባገኘነው መረጃ፥ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በትናንተናው እለት ከቀኑ 10 ሰዓት ከ30 ላይ በአሰላ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ነው ያረፉት።

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በምሥራቅ ትግራይ ክለተ አውላሎ አውራጃ አውዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ከአባታቸው ከአቶ ገብረ ሕይወት ፀዓዱ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወለተ ክርስቶስ ቢሻው በ1923 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
ዲቁናን ከአቡነ ይስሐቅ፣ ቅስና፣ ቁምስና እና ምንኩስና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ተቀብለዋል፡፡
ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የትግራይ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ተሹመዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት በመሆን ለ30 ዓመታት አገልግለዋል።
የቀድሞ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሲያርፉም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቤ መንበር ፓትርያርክ ሆነው ማገልገላቸውም ይታወሳል።

ሥርዓተ ቀብራቸው ሐሙስ የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም በሀገረ ስብከታቸው እራሳቸው በገደሙትና ከፍተኛ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡበት በነበረው ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃማኖት ገዳም ብፁዓን አባቶች፣ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡
{flike}{plusone}