የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የ2017 ዓ/ም የሥራ ዘመን አፈጻጸምን አስመልክቶ የምስጋናና የዕውቅና መርሐ ግብር አካሄደ
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የ2017 ዓ/ም የሥራ ዘመን አፈጻጸምን አስመልክቶ የምስጋናና የዕውቅና መርሐ ግብር አካሄደ።
መርሐ ግብሩ በዛሬ ዕለት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የተካሔደ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መጋቤ ስብሐት ዐቢይ ዘለቀ የብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ልዩ ጸሐፊና ፕሮቶኮል፣ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት የሥራ ሐላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ዋና ጸሐፊዎች፣ ቁጥጥሮች ፣ የሒሳብ ባለሙያዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
በክፍለ ከተማው ለ4ኛ ጊዜ በተከናወነው ዓመታዊ የምስጋናና የዕውቅና መርሐ ግብር ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ የ2017 ዓ/ም የአገልግሎት ዘመን የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት አቅርበዋል።
በዓመቱ ለቅዱስ ወንጌል አገልግሎት ልዩ ትኩረት በመስጠት ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት በትኩረት የተከተታቸው የአብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ወንጌል ጉባኤያት ተጠናክረው መከናወናቸውን በሪፖርቱ ገልጸዋል።
በዚህ የወንጌል አገልግሎትም ከ2014 በላይ አዲስ አማኞች ወደ እናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው ተገልጿል።
ሥራ አስኪያጁ አክለውም በዓመቱ በ37 ገዳማትና አድባራት የተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት በመከታታል በውይይትና በንግግር እንዲፈቱ መደረጋቸውን አስታውሰዋል።
አክለውም በኮሪደር ልማት 7 የገዳማትና አድባራት ገቢ እንዳይቀንስ በአፋጣኝ ከተማ አስተዳደሩና ከሚመለከታቸው መ/ቤቶች ጋር ክፍለ ከተማው ቤ/ክ ካለው መልካም የሥራ ግንኙነት በመነሳት ኮሪደር ልማት የነካቸው ገዳማትና አድባራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት እንዲቀጥሉ ተደርጓል ብለዋል።
በመሆኑም ክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ከሠራተኞቹ ጋር መናበብና ከገዳማትና ከአድባራት የሥራ ሐላፊዎች ጋር በመቀናጀት በበጀት ዓመቱ 183,000,000 ብር ፐርሰንት መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ላለፉት ዓመታት ተመድበው መንጋውን የጠበቁ ሀገረ ስብከቱን የመሩ ብፁዓን አባቶች የሠራቸው መልካም ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በአሁኑ ሰዓት የአባትነት ሀገረ ስብከቱን እየመሩት የሚገኙትን ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የታዩት ለውጦች በእጅጉ የሚያስደስቱና ነገን የሚያስናፍቁ ሥራዎች በመሆናቸው በብፁዕነታቸው ብዙ ተስፋ አለን ብለዋል።
በ2017 ዓመተ ምሕረት የአገልግሎት ዘመን ሕያውን የወንጌል ተልእኮ በማስፈጸምና አጋዝ የሆኑ የራስ አገዝ ልማቶችን በመሥራት እንዲሁም የተሰጣቸውን የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ሐላፊነት በአግባቡ አትርፈው ለመለሱ አካላት የዋንጫ ሽልማትና የዕውቅና ሰርተፍኬት ከብፁዕነታቸው እጅ የተቀበሉ ሲሆን ምስጋናም ተችሯቸዋል።
ሽልማቱ የአብያተ ክርስቲያናቱን የአገልግሎት ሁኔታና ደረጃን መሠረት በማድረግ በወጣው መሥፈርት ልክ መሆኑም ሽልማቱን ያስተባበሩት የክፍለ ከተማው ቤተ ክሀነት ቁጥጥር ክፍል ሐላፊ ሊቀ መዘምራን ዕዝራ መሠረት ገልጸዋል።
በመሆኑም ሽልማቱና ዕውቅናው ገዳማትና አድባራት ለአስተዳዳር ሲባል የተመደቡበትን ደረጃዎችን መሠረት በማድረግ በማወዳዳር የላቀ ውጤት ያስመዘገቡት ከ1-3ኛ ደረጃ የወጡት ተሸልመዋል።
ከዚሁ ጋርም የተሰጣቸውን ሐላፊነት በአግባቡ የተወጡ አስተዳዳሪዎች፣ጸሐፊዎች
ዋና ቁጥጥሮች ፣ ሒሳብ ሹሞች፣ ገንዘብ ያዦች፣ አብነት መምህራን፣ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ንስሐ አባቶች፣ ስብከተ ወንጌል ሐላፊዎች፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ለልዩ ልዩ በጎ አገልጋዮች ሽልማቱና ዕውቅናው ተሰጥቷቸዋል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድፍን ንጉሤ በበኩላቸው መርሐ ግብሩ ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ የሠመረ መዋቅራዊ መናበብ መኖሩን የሚያመለከት ነው ብለዋል።
አክለውም ለሁለንተናዊ ቤተ ክርስቲያናዊ ተግባራዊ ውጤት የድርሻቸውን ለተወጡ የክፍለ ከተማው የሥራ ሐላፊዎችና የገዳማትና አድባራት የአገልግሎት መሪዎችና አገልጋዮች ምስጋና አቅርበዋል በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉም አአሳስበዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሁሉም መዋቅር በተናበበና በተጠናከረ መልኩ ለቤተ ክርስቲያናዊ አንድነትና እውነተኛ ተልእኮ ድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ያሉ ሲሆን እንደዚህ ዓይነት መሠል መርሐ ግብሮች ጥቅማቸው ሰፊ እንደሆነ አስታውሰዋል።
ብፁዕነታቸው አገልግሎታችን ቤተ ክርስቲያን በምትከብርበት መልኩ መሆኑ አለበት ለዚህ ደግሞ ራስን በማዘጋጀትና በማክበር አገልግሎቱን ማከናውን ይኖርብናል ብለዋል ምክንያቱንም ይላሉ “#በትሕትና_ራሱን_ያላከበረ_አገልጋይ_ተቋምን_አስከብርም” ነውና ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በብዙ ተግዳሮቶች ታጅቦ በበርካታ በፈተናዎች አልፎ የሚበረታታ የአገልግሎት ውጤት ላስመዘገቡ ከክፍለ ከተማው ሥራ አስኪያጅና ሠራተኞች ጀምሮ አስተዳዳሪዎች፣ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ጸሐፍት፣ ሒሳብ ሹሞች፣ ቁጥጥሮች፣ የአብነት መምህራን፣ የንስሐ አባቶች ፣ የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮች፣ የቅዱሱን አገልግሎት በሁለንተናቸው ለደገፉ፣ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ውስጣዊና ውጫዊ አገልግሎት ተጠምደው ለደከሙ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ሥር ከተቋቋሙ 8 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት መካከል አንዱና በአንድ ዋና ሥራ አስኪያጅ በ15 የክፍል ኃላፊዎች በ5 የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የሚመራና በሥሩም ከ37 በላይ ታላላቅ ገዳማትና አድባራት የሚገኙበት ነው፡፡