የትንሣኤን በዓል አስመልክተው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ያስተላለፉት መልእክት

ተንሥአ በከመ ይቤ” (ማቴ ፳፰፥፮)
እንደ ተናገረ ተነሥቶአል (ማቴ 28፥6)


ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱና ዋነኛው የትንሣኤ በዓል ነው። ትንሣኤ “ተንሥአ” ከሚለው የግዕዝ ግስ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም መነሣትን ያመለክታል፤ ከሞት በኋላ በነፍስ ብቻ ሳይሆን በሥጋም ጭምር ሕያው ሆኖ መነሣትን የሚገልጽ ቃል ነው።


“ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው ” (1ኛ ጢሞ 1:15) ተብሎ እንደተጠቀሰው የክርስቶስ ወደ ምድር የመምጣቱ ዋነኛ ዓላማ እኛን ከኃጢአታችን ሊያድነን በመሆኑ ምክንያት ይህንኑ ቅዱስና መለኮታዊ ዓላማ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቶ ፈጽሞታል።
በሞቱ ሞታችንን ከደመሰሰ በኋላ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል። ቅዱስ መጽሐፍም የክርስቶስ ትንሣኤ በተዘገበበት በማቴዎስ ወንጌል ምስክርነቱን እንዲህ ሲል ያስቀምጣል፦ “መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ” (ማቴ 28፥5-6)። የክርስቶስ ቃል እንደሰው ቃል አይደለም። ሰው የተናገረውን ሊረሳ ይችላል፣ መርሳት ብቻም ሳይሆን ከአቅም ማነስ የተነሣ የተናገረውንም መፈጸምም ሊሳነው ይችላል። ክርስቶስ ግን የተናገረውን አይረሳም፤ ሁሉን ቻይ ነውና የተናገረውን ይፈጽማል።


ከስቅለቱ በፊት ከሞት እንደሚነሣ በተደጋጋሚ የተናገረው ጌታ ከሞት ተነሥቷል። መልአኩም በማለዳ ተነሥተው የክርስቶስን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ወደ መቃብር ለሄዱት ሴቶች የተናገረው ይህንኑ እውነት ነው። ምንም እንኳ እነርሱ የሄዱበት ዓላማ ሥጋውን ሽቶ ለመቀባት ቢሆንም ከሄዱበት ዓላማ የሚበልጠውንና ከደስታዎችም ሁሉ በላይ የሆነውን ደስታ ማለትም የክርስቶስን ትንሣኤ ሰምተው ተመልሰዋል።
የክርስቶስ ከሞት መነሣት የክርስትና ጽኑ መሠረት ከመሆኑም ባሻገር የክርስትናን ሕያውነት ያረጋገጠ ግልጽ መለኮታዊ ማስረጃ ነው። ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኩር ነው፤ በኩር ማለት የመጀመሪያ ማለት ሲሆን ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣቱ የትንሣኤያችን በኩር ሆኗል። ሐዋርያውም ” አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል ” (1ኛ ቆሮ 15:20) በማለት ማረጋገጫ ሰጥቷል።
አይሁድ በመቃብሩ ላይ ያስቀመጡት ድንጋይ ክርስቶስን ሊይዘው አልቻለም፣ መቃብሩን እንዲጠብቁ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ጥበቃዎችም እርሱን መጠበቅ አልቻሉም ምክንያቱም ክርስቶስ እነርሱን የሚጠብቅ እንጂ በእነርሱ የሚጠበቅ አይደለም። ድንጋዩን አንሱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ። መላእክቱም የእርሱን ከሞት መነሣት ስላረጋገጡ ወደ መቃብሩ ማልደው ለሄዱት ሴቶች “ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም” (ሉቃ 24፥5) በማለት ነግረዋቸዋል።


የእርሱ ከሞት መነሣት ለእኛ በኩራችን ነው። እኛም ሞተን በዚያው አንቀርም እንነሣለን። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል ” (ዮሐ11:25) በማለት ተናግሯል። የእርሱ መነሣት ለእኛ መነሣት ፍጹም ማረጋገጫ ነው።


የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ወቅቱ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የምናከብርበት ልዩ ወቅት እንደመሆኑ መጠን ሁላችንም እርሱ ከሞት የተነሣው መድኃኔዓለም የከፈለልንን የደም ዋጋ ከልብ በመነጨ እምነት በማሰብ ደግሞም በደም ዋጋ የተገዛን የራሳችን ሳንሆን የእርሱ የአምላካችን መሆናችንን መረዳት ያስፈልጋል።
ሲቀጥልም የሆነው ሁሉ በእርሱ መሆኑን አውቀን ከክርስቶስ በተሰጠን ጸጋ ሌሎችን በመርዳትና በማገዝ ማለትም የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጨነቁትን በመምከር፣ የታሰሩትን በመጠየቅ፣ በሀገራችን ብሎም በዓለም ላይ ሰላምን ላጡትና ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ዘርፈ ብዙ በሆኑ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙት ምእመናን በቻልነው መጠን ድጋፍንና ጸሎትን በማድረግ በዓሉን እንድናከብር አባታዊ መልእክቴን አስተላልፋለሁ::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ።