የቴክኖሎጂ ጥቅም በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና እይታ

የሰው ልጆች በምድራውያኑ ፍጥረታት ውስጥ ካሉት ድርሻዎች ውስጥ መሪነት እና ገዢነት ይጠቀሳሉ፡፡ “ምድርን ሙሏት … ግዟትም” የሚለው ቃል ለሰው ልጅ የተሰጠውን ኃይል፣ ዕውቀትና ሥልጣን የሚገልጥ ነው፡፡ (ዘፍ. ፩፥፳፰)፡፡ ይህ ገዢነትና በእነዚህ ፍጥረታት ላይ የተሰጠው ሥልጣን በምን ይገለጣል? ሰው ይህን ለማድረግ የሚያበቃ ምን ነገር አለው? እንዲገዛቸውና እንዲጠቀምባቸው ከተፈጠሩት ፍጥረታት መካከል ከእርሱ የሚበረቱ፣ የሚፈጥኑ እና የሚገዝፉ ፍጥረታት እንዴት ከበታቹ ሊሆኑ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን፡፡

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው የሰውን ጥንት ተፈጥሮ በማስተዋል ነው፡፡ ሰውን ይህን ክብር ያቀዳጀው የሰው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል መፈጠሩ ነው፡፡ (ዘፍ. ፩፥፳፮-፳፯)፡፡ ሰው በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ተፈጠረ ስንል የእግዚአብሔር የባሕርይው መገለጫዎች ወሰን የሌላቸው እና ከማንም ያልተቀበላቸው ናቸው፤ ባሕርይውን ደግሞ ለሰው ልጅ በፀጋ ሰጥቶታል ለማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው አዋቂ እንደሆነ ሁሉ ሰውም የፀጋ አዋቂነት ተሰጥቶታል፤ እግዚአብሔር በባሕርይው ገዥ(ንጉሥ) እንደሆነ ሁሉ ለሰውም በፀጋ በምድራዊው ሁሉ ገዥነት ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር የባሕርይ አምላክ በመሆኑ ሁሉም ፍጥረታት በፍርሃት እና በአክብሮት ሆነው በፊቱ እንደሚቆሙ ሁሉ ሰውም እግዚአብሔር ከሰጠው የፀጋ አምላክነት እና ግርማ የተነሣ በኃጢአት ከመጎስቆሉ በፊት ምድራውያን ፍጥረታት በአክብሮትና በፍርሃት ይታዘዙት ነበር፡፡ ይህም የሚታወቀው አስፈሪ የሆኑ አራዊት እንኳን ሳይቀሩ ለቅዱሳን በሚያሳዩት አክብሮትና መታዘዝ ነው(ዘፍ. ፪፥፳)፡፡

ለሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ዕወቀት፣ ጥበብ እና ማስተዋል አለው፡፡ ሰው ቢበድለውም እንኳን የሰጠውን ዕውቀት፣ ጥበብ እና ማስተዋል አለመግፈፉ ከቸርነቱ የተነሣ ነውና ይህ የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ ለሰው ያለውን ርኅራኄ እና መግቦት ያሳያል፡፡ በዓለማችን በዘመናት የምናያቸው ዕውቀቶች፣ ጥበቦች እና በማስተዋል የተገኙ ግኝቶች ሁሉ ከዚህ ከእግዚአብሔር ሥጦታ ምንጭ እንደ ወንዝ የሚፈሱ የፀጋ ሥጦታዎች ናቸው፡፡

በዘመናችን ተስፋፍትው የምናያቸው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግኝቶችም የዚሁ አካል ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ይህ በተፈጥሮ የተሰጠውን አዋቂነት እና ጥበብ ተጠቅሞ በየዘመኑ ሕይወቱን ያሳልጥበታል፤ የየዘመኑን ፈተናዎች ይቋቋምበታል፤ በአጠቃላይ ሕይወቱን በአግባቡ ለመምራት ይጠቀምበታል፡፡

ጠለቅ ብለን ስናየው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት እግዚአብሔር በሰው ውስጥ ያስቀመጠው መግቦት ነው፡፡ ይህን በጥንት ተፈጥሮ የሰጠውን ፀጋ በበደለው ጊዜ እንኳን አልነሳውም፤ ይህም ከላይ እንዳልነው የቸርነቱ ውጤት ነው፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ለሰው የመግቦት አካል ይሆን ዘንድ፣ በኑሮው የሕይወቱን ውጣ ውረድ እንዲያቀልለት ዕውቀትንና ጥበብን በመስጠቱ ሰው በአእምሮው የዕውቀት ምጥቀትና በጥበቡ እየታገዘ እግዚአብሔር የፈጠራቸውን ፍጥረታት በመጠቀም ብዙ ድንቅ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አስገኝቷል፡፡ ይህ መልካም ነገር ነው፤ እግዚአብሔርንም የምናመሰግንበት አንድ ትልቅ ምክንያትም ነው፡፡ በመልካም ልቡና ስናስተውለው የእግዚአብሔርን ቸርነት እና ኃያልነት የምናስብበት ሥጦታ ነው! የፈጠረው ሰው ይህን ያህል ጥበብና ኃይል እንዲኖረው ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

ነገር ግን ቴክኖሎጂ መልካም የሚሆነው ለመልካም ነገር ስንጠቀምበት ነው፡፡ ዕውቀቱንና ማስተዋሉ ሲሰጠን ለመልካም እንድንጠቀምበት ቢሆንም ለክፉም ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ይህም ከነፃ ፈቃድ የተነሣ ነው፤ እግዚአብሔር ለሰው የሰጠው ዕውቀትን ብቻ ሳይሆን ወደ ፈለገው የሚሄድበትን ነጻ ፈቃድም ጭምር ነውና፤ ለመልካም ብንጠቀምበት እግዚአብሔርንም ሰውንም እናስደስታለን፤ ለበለጠ ሰማያዊ እና ዘለዓለማዊ ዕወቅትም የተገባን ሆነን እንገኛለን፡፡ ለኃጢአት ብንጠቀምበት ግን እንኳን የሠራነው ቴክኖሎጂ ቀርቶ የገዛ ሰውነቶቻችንም ይረክሳሉ፤ ከሰማያዊው ርስት ዕድል ፈንታ አይኖረንም፡፡ ስለዚህ ቴክኖሎጂ በመልካም ኅሊና ሊመራ ይገባዋል ማለት ነው፡፡

አሁን የምናየው የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚመራው በምን ኅሊና ነው? ይህ በተለይ በክርስቲያኖች ዘንድ ሊስተዋል የሚገባው ጠቃሚ ጥያቄ ነው፡፡ ቴክኖሎጂን የሚመራው የሰው ኅሊና ለመልካምነቱ ወሳኝ ነው፤ ኅሊና ጤናማ ከሆነ ቴክኖሎጂም ጤናማ አገልግሎት ይሰጣል፤ ካልሆነ ግን ወደ ሞት ይዞን ሊወርድ ይችላል፡፡

ይህን የተክኖሎጂ ጤነኛነት ቢያንስ በሁለት መንገድ ልንመዝነው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ለስንፍና፣ ለኃጢአት፣ ለትዕቢት እና ለአምባገነንነት መሣሪያ ከሆነ ጤናማ አይደለም፡፡ ሰው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ኃጢአት የሚሠራ እና ሌሎችን የሚበድል ከሆነ ለራሱ መጥፊያ እየተጠቀመበት ነው ማለት ነው፡፡ በቴክኖሎጂ ብዛት የማይዳንባት የእግዚአብሔር ፍርዱም የኋለ ኋላ ታጠፋዋለች፡፡

ሁለተኛው ችግር ደግሞ ቴክኖሎጂን ከመጠን በላይ ቦታ ሰጥቶ እንደ አምላክ ማየት ነው፡፡ የሕይወት መጨረሻ መንግሥተ ሰማዯትን ወርሶ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንጂ ቴክኖሎጂን እንደ ምኞት መዳረሻ ቆጥሮ በዚህ ምኞት ውስጥ ራስን አስክሮ መኖር አይደለም፡፡ “በሰለጠነው ዓለም” ሰዎች ለራሳቸው ለፈጠሯቸው ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ሥራዎች ለፈጣሪ የሚሰጠውን ዓይነት አክብሮትና ምስጋና ሲቸሯቸው እናስተውላለን፡፡ ቴክኖሎጂ ጣዖታችን ከሆነ መሞቻችን ሆኗል ማለት ነው፡፡

እኛ ክርስቲያኖች ግን ቴክኖሎጂን መጠቀም ያለብን የምኞታችን ሁሉ መዳረሻ አድርገን ሳይሆን በዚህ ምድር ለምንኖረው ኑሮ ለመልካም ሥራ መሣሪያ እንዲሆነን እንጂ በራሱ ግብ ስለሆነ አይደለም፡፡

ይህች ዓለም በቴክኖሎጂ ሳይሆን በእግዚአብሔር ኃይል እና መግቦት እንደምትኖር ያለ ግብዝነት ልናምን ይገባል፡፡ ቴክኖሎጂ ራሱ እግዚአብሔር ለሰው ከሰጠው ዕውቀት የተነሣ እንደሆነና በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለመልካም ነገር መሣሪያ የሚሆን የሰው ልጅ ሀብት እንደሆነ ሁል ጊዜ ማሰብ ማሰላሰል ይኖርብናል፡፡ ካልሆነ ግን መልካም ሥጦታነቱ ቀርቶ ለሰው ልጅ የከንቱነት ምክንያት እንዲሁም ለጥፋቱ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን፡፡

የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም

ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እውነተኛና ሐሰተኛ መረጃዎችን በጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በምስል ወድምጽና በመሳሰሉት መንገዶች ለሕዝብ የሚሰራጭበት የመገናኛ ዘዴ ነው። ሆኖም አንድ ሰው ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሲጠቀም በሐሰቱ እንዳይጎዳ፣ በእውነቱ እንዲጠቀም እውነቱን ከሐሰት የሚለይበት ማንጸሪያ ወይም መመዘኛ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ የተጻፈ ወይም የተነገረና የታየ ሁሉ እውነት አይደለምና።

የሰው ልጅ ለተለያየ ዓላማ አንድን ሐሳብ በፈለገው መንገድ ሊገልጽ ይችላል፡፡ ነገር ግን የገለጸበት መንገድና ሁኔታ ምን ዓይነት መረጃ፣ ለማን፣ እንዴት፣ ወዘተ ለሚሉት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ምላሽ የሚሰጥ መሆን ይገባዋል፡፡ መረጃውም ሊጠቅምና ሊጎዳ እንደሚችል በቅድሚያ መረዳት ይገባል፡፡ እውነትን ቢናገር እንኳ የተናገረው ምን አስቦ ወይም ለምን ዓላማ እንደሆነ ስለማናውቅ የመታለል ዕድላችን ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚለቀቁ መረጃዎች ትክክለኛ ከሆኑ አዎንታዊ ተጽእኖ በሐሰት የተሞሉ ከሆኑ ደግሞ አሉታዊ ተጽእኖ በማኅበረሰቡ ላይ የማሳደር አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የተጻፉ ጽሑፎችን፣ የተለጠፉ የምስል ወድምጽ መልእክቶችን ስናይ ስለ ማንነታቸውና ስለ ውጤታቸው አዎንታዊነትና አሉታዊነት ለመረዳት መጠየቅ ያለብን ጥያቄዎች አሉ። ጥቂቶቹን ብንመለከት፡-

፩. መልእክቱ ምንድን ነው?፡- በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን የተላለፈው ጉዳይ መልእክት ምንነት እና ፍሬ ነገር ምንድን ነው? የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል። ዝም ብለን የጉዳዩን ምንነት ሳንረዳ ሌሎች ስላራገቡት የምንቀበለው መሆን የለበትም። በተአምረ ኢየሱስ የተጻፈ አንድ ታሪክ አለ።

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አብነት ለመሆን ትምህርት ይማር ዘንድ ወደ መምህር ሄደ። (አስተውል ለመምህሩ ዕውቀትን የሰጠ ጌታ ለእኛ አብነት ለመሆን ሲል ሄደ እንጂ አዲስ ዕውቀት ለመገብየት አይደለም)። ከዚያ መምህሩ ፊደል ሊያስተምረው “አሌፍ” በል አለው። ጌታም “አሌፍ” አለ። ከአሌፍ ቀጥሎ ያለው ፊደል “ቤት” ነውና “ቤት” በል አለው።

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መጀመሪያ የአሌፍ ትርጉሙ ምንድን ነው? የዚህን ምሥጢር ንገረኝና ቀጣዩን እለዋለሁ ብሎታል። ስለዚህ እኛም ጉዳዩን በቅርበት በስሜት ሕዋሳቶቻችን ዳስሰን፣ ዐይተንና ቀምሰን ያላረጋገጥነውን ጉዳይ ወይም በሃይማኖት ትምህርት ያልተማርነውን ጉዳይ የሆነ አካል ጽፎት ብናገኝ ስለተጻፈው ጽሑፍ ምንነት የጻፈውን አካል ጠይቀን ወይም በሌላ መንገድ መረዳት ይጠበቅብናል፡፡ ይህም የመልእክቱን ምንነት መለየትና መገንዘብ ያስችለናል፡፡

፪. ማን ጻፈው?፡- ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ “ይደልዎ ለዘያነብብ ቅድመ ይዝክር ስሞ ለበዓለ መጽሐፍ ወእምዝ ያንብብ ወይምሀር፤ የተጻፈን ነገር ለሚያነብ ሰው የተጻፈውን ጉዳይ ከማንበቡ በፊት የጸሓፊውን ማንነት ይወቅ፣ ካወቀ በኋላ አንብቦ ያነበበውን ያስተምር” ይላል። የጸሓፊውን ማንነት ማወቅ የጽሑፉን ስሜት እንድንረዳው ይረዳናል። ከዚያም ጽሑፉን አንብቦ የተጻፈበትን ዐውድ ተረድቶ ምን ለማለት እንደፈለገ በቀላሉ መረዳት ያስችላል፡፡ ክርስቶስን ሐዋርያት ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ነበር። ነገር ግን የሚከተለው ሕዝብ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የነበረው አመለካከት የተለያየ ነበር። “መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉ አሉ፤ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ፡፡”(ማቴ.፲፮፥፲፬)፡፡ አስተውል የሚከተሉትን ሰው ማንነት አለማወቅ ከትልቅ ክሕደት ውስጥ ይከታል። ፈጣሪያቸውን እንደ ፍጡር አቅርበውት ነበር። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ ቢላቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” ብሎ ቢመልስ “አንተ ብፁዕ ነህ” ተብሎ ክብር ተሰጥቶታል።

በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ባለቤታቸው የማይታወቁ ብዙ ጽሑፎች እና የድምጽ እንዲሁም የምስል ወድምጽ መረጃዎች ይለቀቃሉ። በዚህን ጊዜ በአእምሯችን የሚጭኗቸው መልእክቶች ይኖሯቸዋል። ስለዚህ መልእክቱ ከእውነተኛነቱ አልፎ ክርስቲያናዊ ወይም ኦርቶዶክሳዊ ነው ወይ? የሚለውን መመዘን ያስፈልጋል። ስለዚህ ማኅበራዊ መገኛ ብዙኃን ስንጠቀም መምረጥ አለብን ማለት ነው።

፫. የት ተጻፈ?፡- ድርጊቱ የተፈጸመው የት ነው? የሚለው መታወቅ አለበት። በውጭ ሀገር የተደረገውን ድርጊት በሀገራችን እንደተደረገ እያደረጉ እያቀረቡ ሰውን ስሜታዊ የሚያደርጉ፣ ዋሽተው የሚያስዋሹ ብዙ ሰዎች አሉ። ስለዚህ የሆነን ድርጊት ወይም ጉዳይ አምነን ከመቀበላችን በፊት በተለያየ መንገድ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይገባል። ለማረጋገጥ በቂ ማስረጃ ካላገኘን ጉዳዩን ለሌሎች ከማካፈል መቆጠብ፣ እኛም ከመደናገጥና ከስሜታዊነት ርቀን በሰከነ መንገድ ልንጓዝ ያስፈልጋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ የሶስናን ታሪክ ሙሉውን ስናነብ የምናስተውለው አንድ ነገር አለ። ረበናት ከሶስና ጋር መተኛት ይፈልጋሉ። እርሷ ግን እምቢ ትላቸዋለች። በዚህ ምክንያት በሐሰት ይከሷታል። የሚመለከታቸው አካላትም ጉዳዩን ሳይመረምሩ ሶስናን ለመግደል ይዘጋጃሉ። ዳንኤል ግን ጉዳዩን እንመርምረው ብሎ የት አገኛችኋት ብሎ ሲጠይቃቸው ከተለያየ ቦታ ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ውሸታቸው ታውቋል። ስለዚህ እኛም በውሸት እንዳንታለል “የት?” ብለን መጠየቅ አለብን።

፬. መቼ ተጻፈ? የሰማነው ወይም ያየነው ነገር መቼ የተፈጸመ ነው? የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከዓመታት በፊት የተደረገውን ጉዳይ ዛሬ እንደተደረገ አድርገው ከዚህ ቀደም ያላየውን ሰው ያታልሉበታል። ከውጭ ሀገርም ይሁን በሀገር ውስጥ ከዓመታት በፊት የተቃጠለውን ቤት፣ የሞተውን ሰው ዛሬ የተደረገ አስመስለው ሰውን ከሰው ያጣሉበታል። ስለዚህ የምንሰማውን ነገር መቼ እንደተደረገ ማወቅ ያስፈልጋል። ጌታችን ሐዋርያትን በደብረ ዘይት ሰብስቦ ስለ ዳግም ምጽአት እና ምልክቶቹ ሲነግራቸው ይህ መቼ ይሆናል? ብለው ጠይቀውታል። (ማቴ. ፳፬፥፫) እኛም መረጃን ለማጣራት መቼ ብለን መጠየቅ አለብን። አለበለዚያ ግን ተሳስተን ልናሳስት የተሳሳተ መረጃ አጋርተን እኛንም ሌላውንም ልንጎዳበት እንችላለንና መጠንቀቅ አለብን።

፭. ስንት?፡- ብዙ ጊዜ አንዱ የሠራውን በደል ብዙ ሰው እንደሠራው አድርጎ ማቅረብ እና ብዙ ሰው የሠራውን አንድ ሰው ወይም ጥቂት ግለሰቦች እንደሠሩት አድርጎ መረጃ ሊለቀቅ ይችላል።

ለምሳሌ በአንዱ ሰው ወንጀል ያ ሰው የተወለደበትን ሰፈር ወይም ብሔር መስደብ ትልቅ ችግር ሊያስከትል የሚችል ነው። ተጠያቂም መሆን ካለበት ራሱ ተናጋሪው አካል ወይም ቡድን እንጂ በጅምላ የተወለዱበትን ቦታ መስደብ ትልቅ በደል ነው። ምናልባት ወንጀል ፈጻሚው ሰው በሥነ ምግባሩ ምክንያት ሕዝቡ የናቀው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንድን ጉዳይ ዝም ብለን ከመቀበላችን በፊት ስንት ሰው አደረገው? የሚለውን መረጃ ጠይቀን ማወቅ ይጠበቅብናል ማለት ነው። ስንት የቦታን ስፋት፣ የጊዜን መጠን፣ የሰውን ብዛት ሊያሳውቀን ይችላልና። ብዙዎች የሠሩትን ወንጀል አንድ ሰው እንደሠራው አድርጎ ማቅረብም ሊኖር ይችላል።

፮. እንዴት?፡- በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚለቀቁ አንዳንድ መልእክቶች ደግሞ ከነባራዊው እና ከተፈጥሯዊው ጉዳይ ያፈነገጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ዝም ብለን የምንቀበላቸው አይደሉም። እኛ ከለመድነው እንዲሁም ከተማርነው እና ካየነው የተለየ ነገር ሲነገር እና ሲተላለፍ እንዴት? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።

፯. ለምን?፡- በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ብዙ መረጃዎች በተለያየ መንገድ ይለቀቃሉ። መልእክቶቹን የሚለቀው ሰው ግን ምክንያት አለው። እውነቱንም ይሁን ሐሰቱን መረጃው ለሚደርሳቸው አካላት ማሥረፅ የፈለገው ጉዳይ አለው። ስለዚህ አንድን መልእክት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጽፎ ስናገኘው ቀጥታ በእኛ አረዳድ ብቻ ሳይሆን በጸሓፊው አረዳድ ልንረዳው ይገባል። መልእክቱን ዐይተን ቀጥታ ማመን የለብንም። ለምን ብለን መጠየቅ አለብን። አንድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተማሪዎች የሚነገር ቀልድ (ተረት) አለ። በአንድ ወቅት ምሽት ላይ አንድ የተማሪዎች ማደሪያ ክፍል መቃጠል ይጀምራል። ከዚያ ተኝተው የነበሩ ተማሪዎች ይነቁና ማደሪያ ክፍላቸው እየተቃጠለ መሆኑን ሲያውቁ ራሳቸውን ለማትረፍ ተደናግጠው ራቁታቸውን እየሮጡ ይወጣሉ፡፡ ከዚያ ቤተ መጻሕፍት ቆይቶ የመጣ ተማሪ ወደ ቤቱ ሲመለስ ብዙ ሰው ራቁቱን እየሮጠ ያያል። ይህን ጊዜ እርሱም ልብሱን አውልቆ ተከተላቸው ይባላል። አሁን ይህ ሰው ያለ ምክንያት የሚንቀሳቀስ ሰው ነው። እነርሱስ ከምንቃጠል ብለው ለማምለጥ በደመ ነፍስ ያደረጉት ነው። እርሱ ግን ዝም ብሎ እነርሱን ብቻ ዐይቶ ምክንያቱን ሳይረዳ አውልቆ ተከትሏቸዋል። እኛም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነ ታወቂ ሰው ወይም የማኅበራዊ አንቂ(Activist) ግለሰብ ስለጻፈው እሱን ተከትለን የምናስተጋባና ለሌሎች የምናጋራ መሆን የለብንም።

ግለሰቡ ለሆነ ዓላማ ውሸቱንም ይሁን እውነቱን መረጃውን ሲያዘጋጀው የሚያስከትለውን ችግር ተረድቶም ሆን ሳይረዳ ወይም ሆነ ብሎም ሲያደርገው ተከፍሎት ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ከየት ወደ የት፣ ከምን፣ በምን፣ እስከምን…. ወዘተ” እያልን ነገርን አጥርተን ለነፍሳችንም ለሥጋችንም የሚጠቅመንን መረጃ ልንይዝ ይገባናል።

ከላይ እንደተገለጸው መረጃ ስላገኘን ብቻ የሚያስከትለውን ችግር ሳንረዳ በማኅበራዊ ሚዲያ መልቀቅ በርካታ ችግሮችን በግለሰቦች፣ በቤተሰብ፣ በአካባቢና ብሎም በሀገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት መዝነን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የምንጠቀምበት ሰዓትም ገደብ ሊኖረው ይገባል። ቀኑን ሙሉ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ተጠምዶ መዋልና መከታተል ሱስ እንዳይሆንብንም መጠንቀቅ አለብን።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ:-https://gibi.eotcmk.org/a/የቴክኖሎጂ-ጥቅም-በኦርቶዶክሳዊ-ክርስት/ https://gibi.eotcmk.org/a/የማኅበራዊ-መገናና-ብዙኃን-አጠቃቀም/