የታኅሣሥ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በኮተቤ ደብረ ልዑል ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በድምቀት ተከበረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት፣ በየዓመቱ ታኅሣሥ ፲፱ የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል በዓል ቅዱስ ገብርኤል አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ከእቶን እሳት የታደጋቸውን ዕለት የሚዘክር መሆኑ የሚታወቅ ነው።
በበዓሉ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ፣ መልአከ ምሕረት ዘካርያስ አዲስ የየካ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ መጋቤ ሐዲስ ላእከ ማርያም ተስፋዬ የኮተቤ ደብረ ልዑል ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል እና ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ፣ የአድባራት እና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ካህናት አባቶችና ምዕመናን ተገኝተዋል።
የካቴድራሉ ታቦተ ሕግም ከመንበሩ ወጥቶ ምዕመናን የባረከ ሲሆን በዓሉ በሊቃውንቱ ያሬዳዊ ወረብና በሰንበት ተማሪዎች ዝማሬ ቀርቧል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የንግሥ በዓሉን በሚመለከት በሰጡት ትምህርት “የአናንያን ፣ የአዛርያስንና የሚሳኤልን ታሪካቸውን ከመተረክ ተሻግረን በእምነትና በሕይወታችን” እነሱን መምሰልም ይገባናል ብለዋል።
በተመሳሳይ ከበዓሉ “የእምነት ፅናትን ፣ በጉብዝናችን ወራት አምላካችን እግዚአብሔርን ዘወትር ማሰብና ማምለክ” እንዳለብንም ልንማር እንደሚገባ በመርሐ ግብሩ ላይ በተሰጡ ትምህርቶች በተደጋጋሚ ተገልጿል።
የንግሥ በዓሉ የተከበረበት የኮተቤ ደብረ ልዑል ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ታሪካዊ ቅዱስ ስፍራ ነው።