የታቦት ክብር በመጽሐፍ ቅዱስ

ታቦት፡- ቃሉ ግእዝ ነው፡፡ ቤተ = አደረ ከሚለው ግሥ የወጣ ሲሆን ታቦት ማለት የእግዚአብሔር ማደሪያ ማለት ነው ታቦት የጽላቱ ማደሪያ ሲሆን ጽላቱም አሠርቱ ቃላትን የያዘ የእግዚአብሔር ስም የተጻፈበት ስለሆነ ለስሙ መስገድ ይገባል ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ጉልበት ሁሉ ለክርስቶስ ስም ይስገድ” ሲል ተናግሯል፡፡ /ፊልጵ2÷10/ ለታቦት መስገድ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አለ ይኸውም “ ኢያሱና የእስራኤልም ሽማግለዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ” /ኢያ 7÷6/
ታቦት እንደሚያስፈልግ ያዘዘውና የፈቀደው ልዑል አግዚአብሐር ነው /ዘጸ 25÷10-22/ ከዚህ ቀጥሎ በታቦት የተደረጉትን ተአምራት እናያለን እስራኤል የዮርዳኖስን ባሕር ለመሻገር በተቸገሩ ጊዜ ኢያሱ እግዚአብሔር በነገረው መሠረት ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው በሕዝቡ ፊት ወደዮርዳኖስ እንዲሄዱ ነገራቸው እነርሱም ሄዱ ታቦቱን የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ /ኢያ 3÷1-17/
ልዑል እግዚአብሔር ሕዝበ እስራኤል ስለበደሉት እንዲሁም የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በደላቸውና ክፋታቸው ስለበዛ ታቦተ ጽዮን ተማርካ ወደ ፍልስጥኤም ሄደች በዚያም ዳጎን የተባለውን ጣኦት  አውርዳ ጥላ ቀጥቅጣ ለእስራኤል ደሰታን አጎናጽፋቸዋለች /1ኛ.ሳሙ5÷1-15/፡፡
የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረው የተከበሩ ብዙዎች ናቸው ከእነዚህም አንዱ አቢዳራ ነው “ የእግዚአብሔር ታቦት በአቢዳራ ቤተሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ እግዚአብሐርም የአቢዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ “ /1ኛ ዜና መዋ 13÷14/ በአንጻሩ የእግዚአብሔርን ታቦት ሳያከብሩ ቀርተው የተጎዱ አሉ ለምሳሌ ዖዛ፡- ሳይገባው ሥልጣነ ክህነት ሳይኖረው የእግዚአብሔርን ታቦት በመንካቱ ተቀስፎአል፡፡
“ የእግዚአብሔርም ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ እጁንም ወደታቦቱ ስለዘረጋ ቀሠፈው በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ “ 1ኛ ዜና መዋ 3÷10 ዛሬም በዘመናችን የተነሡ የታቦትን ክብር የማያምኑ ዖዛዎች መናፍቃን ናቸው እንደዖዛ ከመቀሠፍ ውጭ የሚጠብቃቸው የለም ስለታቦት ይህ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ እያለ መናፍቃን እንዲሁ ዓይናቸውን ጨፍነው ደረቅ ክህደትን ማስተላለፋቸው እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡እንኳን በምድርና በሰማይም ታቦት እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ተናግሯል “ በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ “/ ራእ 11÷19 /ይህን ሁሉ ለማወቅና ለመረዳት መማር ያስፈልጋል፡፡ በሃይማኖት ጸንተን ለመኖር ትምህርት ወሳኝ ነው “ ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ በእነዚህም ጽና ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና “ /1ኛ ጢሞ 4÷16/ ጥንታውያን አባቶቻችንም “ ካልተማሩ አያውቁ ካላወቁ አይጸድቁ “ በማለት ስለትምህርት አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለዓለም ያስተዋቀችው በትምህርት ነው፡፡
በዚህ መሠረት በሃይማኖታችን ጸንተን ለመኖርና የሥነ ምግባር ሰዎች ለመሆን ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል መማርና በሥራ መተርጐም ያስፈልጋል፡፡
“ ወስብሐት ለእግዚአብሔር “

                        (በላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአ/አ/ሀ/ስ/የስብከተ ወንጌል ትምህርት ሥርጭት ኃላፊ)

{flike}{plusone}