የተቀጸል ጽጌ አጼጌ በዓል በድምቀት ተከበረ

00511

በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን ሲከበር የቆየው  የተቀጸል ጽጌ አጼጌ በዓል በዘንድሮም ዓመት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፣ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ  ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ ብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት፣ መምህር ጎይቶም ያይኑየአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች  በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡፤
በዓሉ በቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ የተከፈተ ሲሆን በተረኛው ደብር በመንበረ ንግሥት ፉሪሐና ደብር አገላጋይ ካህናት ጸሎተ ወንጌል ተደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሃ ኃበ እግዚአብሔር ነገሥተ ምድር ሰብህዎ ለእግዚአብሔር ወዘምሩ ለአምላክነ  የሚለው የዳዊት መዝሙር በዲያቆኑ ተዚሟል፡፡ የዮሐንስ ወንጌል ምራፍ 19 ቁጥር25 ላይ የተጻፈው ቃል ማለትም በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፣ የእናቱም እህት ፣ የቀለዮጳ ሚስት  ማርያም ፣መግደላዊት ማርያም ቁመው ነበር የሚለው ቃል  በቅዱስነታቸው በንባብ ተነቧል፡፡ የኪዳን ጸሎትም ተደርሷል፡፡
አይ ይእቲ ዛቲ ኢትዮጵያ መድኃኒት እንተ ሀሰስዋ ወኦድዋ ሊቃነ ጳጳሳት ወይቤሎ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ግበር በዓለ በጽርሀ ንግሥት  የሚል ያሬዳዊ ዝማሬ በሊቃውንቱ ቀርቧል፡፡
በከመይቤ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ንኡ ንትፈጋእ ወኢይህልፈነ ጽጌ ደመና አብርሐ በጽርሀ ንግሥት የሚል ወረብ  በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ተዘምሯል፡፡
አፄጌ ወእጨጌ  ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አባ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ  ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት  የሚል ወረብ በአጫብር ሊቃውንት ተዘምሯል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ  ፓትርያርኩ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ይህ የምናከብረው በዓል  ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ በመሰቀል ላይ ያደረገውን ውለታ እያሰብን ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ያደረገልንን ቸርነት ለሕዝበ ክርስቲያን ስናስተምር እንኖራለን፡፡ ዘመነ ማቴዎስን አሳልፈን ወደ ዘመነ ማርቆስ ተሸጋግረናል፡፡ ባለፈው ዘመን ያጠፋነውን ጥፋት ንሰሐ ገብተን ማረም አለብን እግዚአብሔር የሰጥንን ጸጋ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባናል በማለት ሰፋ ያለ አበታዊ ትምህርት አስተምረው  እንዳጠናቀቁ በዓሉን ለማብሰር  የተዘጋጀውን አደይ አበባ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በዓሉን ለማክበር ለተሰበሰበው አድለዋል፡፡

{flike}{plusone}