የቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሁለገብ ሕንጻ ግመንባታ በመጠናቀቁ በይፋ ተመረቀ!!

2022

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሁለገብ ሕንጻ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ጽ/ቤት ኃላፊ ፣ ሊቀማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የክፍለ ከተማ መስተዳድር ተወካዮች ፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ ካህናት ፣ የሰንበት ት/ቤቱ ወጣቶችና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ቅዳሜ ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም ተባርኮ ተመርቋል፡፡
ከዘጠኝ ዓመት በፊት የመሠረት ደንጊያው የተቀመጠላት የቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሁለገብ ሕንጻ  ባለአራት ፎቅ የንግድ ሕንጻ ፣ ባለአራት ፎቅ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ ባለአራት ፎቅ የክሊኒክ ሕንጻ ያካተተ ሲሆን አጠቃላይ የወጪ ግምት ሰባ አምስት ሚሊዮን ብር ያህል እንደሚደርስ ከደብሩ ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ለምረቃ የበቃው ሁለገብ ሕንጻ በየወሩ ብር ስምንት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ሺህ የኪራይ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ በአንድ ዓመት ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ገቢ እንዲአገኝ ሆኖአል፡፡
በተመሣሣይ በዚሁ ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አዲስ ለሚገነባው ሕንጻ የመሠረት ደንጊያ አስቀምጠዋል፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሁለገቡን ሕንጻ ባርከው ከመረቁ በኋላ ለተሰበሰበው በርካታ ምዕመናን የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ “የሰው ልጅ የተፈጠረው ለምስጋና ነው፡፡ 
ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ እንደሚያመሰግኑት ሁሉ እኛም አምላካችን እግዚአብሔር እየመገበን ስለሆነ ልናመሰግነው ይገባናል፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ፈቅዶ ሀገራችን ኢትዮጵያ የልማት ፣ የዕድገትና የብልፅግና ሀገር ለመሆን በሩጫ ላይ ትገኛለች፡፡
ወጣቶች በሀገራቸው ሠርተው እንዲኖሩ ይህ ልማት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን በልማት ራሷን መቻል አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱን ልማት ሁሉም ማልማት አለበት፡፡ ሌሎቹም አድባራትና ገዳማት እነዚህን አብነት ፣ መሪና ፊትአውራሪ በማድረግና በእነሱ መንገድ በመጓዝ ጠንክረው ሊሠሩ ይገባል፡፡

ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማርና ስብከተ ወንጌልን ማፋጠን ትልቁ ሥራዋ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ደግሞ ለማልማት መትጋት አለበት፡፡
በዛሬው ዕለት ባርከን የከፈትነው ሁለገብ ሕንጻ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቅርስ ነው፡፡ ህንጻው ራሱ ብዙ ልጆችን ይወልዳል፡፡ እንደምናየው ቦታው ለልማት የተመቻቸ በመሆኑ ለቀጣዩ ልማት የዛሬው ልማት በር ከፋች ነው፡፡ አሠሪዎቹም ሠሪዎቹም በጉልበት ፣ በዕውቀት ፣ በገንዘብና በሀሳብ የተባበሩ ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡
ይህን ሁለገብ ሕንጻ ለፍጻሜ ያደረሱ ሁሉ የተባረኩ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ሀብትን ለሰው የሚሰጠው ሰው ብቻውን እንዲጠቀምበት አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርን ድርሻ ለእግዚአብሔር መስጠት አለበት፡፡ ሀብቱ የሚገኘው በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ሀይል አይደለም፡፡
በረከት ለማግኘት የእግዚአብሔርን ድርሻ ማስቀረት አይገባም፡፡ እምነት ካለ ሁሉን ማድረግ ይቻላል፡፡
የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ገንዘቦች ምዕመናን ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ሥራም የተሠራው በመግባባት ነው፡፡ አለመስማማት ግን ሥራን ያበላሻል፡፡ በስምምነት ከተሠራ ሁሉ ነገር ይባረካል፡፡
ስለዚህ ይህንን ሁለገብ ሕንጻ ሠርታችሁ ለውጤት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ቅዱስነታቸው ጥልቅ የሆነ አባታዊ ምክርና ቡራኬ በመስጠት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖአል፡፡

{flike}{plusone}