የቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት በሥሩ ካሉት አድባራትና ገዳማት ጋር በመሆን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን እያካሄደ ይገኛል!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት በሥሩ ካሉት አድባራትና ገዳማት ጋር በመሆን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን አካሄደ።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የሰሜንና የደቡብ ወሎ እንዲሁም የከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ጉባኤውን በጸሎት ከፍተዋል።
ጉባኤው የተካሄደው በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ነው።በካቴድራሉ ሊቃውንት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል።
መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን የክፍለ ከተማው ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ በጉባኤው ላይ የተገኙትን በሙሉ “የእንኳን ደህና መጣችሁ” መልእክት አስተላልፈዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቅለል ባለ መልኩ “የ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን” በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
የጉባኤው ዋና ዓላማ በክፍላተ ከተማው ሥር ባሉት አድባራትና ገዳማት ስለተሠሩ ሥራዎች እና ላደረጉት አስተዋጽኦ የሚገባቸውን ሽልማት እና ምሥጋና ለማቅረብ፤ ሲቀጥልም ከዚህ የበለጠ እንዲሠሩ ለማበረታት እንደ ሆነ አብራርተዋል።
ክፍላተ ከተማው በልማት በኩል እድገት እያሳየ መሆኑን፣ የተቸገሩትን አብያተክርስትያናትንና በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ምእመናንን በመርዳት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የክፍለ ከተማውን የአሠራር ሂደት በተለያያ ጊዜ በመጎብኘትና አመራር በመስጠት ያደረጉት አስተዋጽኦ ለክፍለ ከተማው ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ የሰሜንና የደቡብ ወሎ እንዲሁም የከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በጦርነቱ ወቅት ለምእመናን ያሳዩትን በጎነት አውስተው በጉባኤው ስም አመስግነዋቸዋል።
በበጀት ዓመቱ 91 ሚሊዮን ብር በክፍለ ከተማው ካሉት አድባራትና ገዳማት መሰብሰቡን የክፍለ ከተማው ፋይናንስ እና በጀት ክፍል ኃላፊ መ/ር ወንድወሰን ስለሺ ጠቅሰዋል።
ክፍለ ከተማው በመንፈሳዊ አገልግሎት እና በልማት ሥራ በኩል ውጤት ላስመዘገቡት አድባራትና ገዳማት ከአንደኛ አስከ አራተኛ ደረጃ በማውጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ እና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።
ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅና ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ መጽሐፍ ቅዱስና ምእመናንን የሚባርኩበት የመስቀል ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በተያያዘም በሁለቱ ክፍላተ ከተማ ከሰላምና ፀጥታ ጋር በተያያዘ በተጨማሪም የቤተክርስቲያንን ይዞታን በማስከበር በኩል አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።
የመጽሐፍ ቅዱሱን ስጦታ ያበረከቱት የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሊ/ኅ ይልማ ጌታሁን እንደሆኑ ተገልጿል።
አጠቃላይ መርሐ ግብሩን መ/ጥ ሰሎሞን ንጉሤ የክፍለ ከተማው የስብከተ ወንጌልእና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ክፍል ኃላፊ መርተዋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ መርሐ ግብሩ ባማረ መልኩ እንዲዘጋጅ ትብብር ያደረጉትን የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል እና የደብረ ጽጌ ዑራኤል የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሁሉንም አመስግነዋል።
በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እና ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሚያደርጉትን ንግግር ከቆይታ በኋላ የምንዘግብ መሆኑን እናሳውቃለን።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት/Addis Ababa Diocese
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese