የቦሌ አየር ማረፊያ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የነዳጅ ማደያ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

👉የነዳጅ ማደያና የኤሌክትርክ ቻርጀር
👉የትምህርት ቤትና የክኒሊክ ሕንጻ መሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ
👉ከፍተኛ ወጭ የተደረገበት መልክአ ምድር ጉብኝት
👉የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጉልላት መስቀል የማኖር
👉የምስጋናና የእውቅና መርሐ ግብር
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ጥር ፳፫/፳፻፲፰ ዓ/ም
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ አየር ማረፊያ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በቡልቡላ መንገድ ያሠራው ለቤተክርስታያናችን ቀዳሚ የሆነው የነዳጅ ማደያ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የደቡብ ምሥራቅ ትግራይና የራያ አህጉረ ስብከት፣ ሊቀ ጳጳስ፣ በመንበረ ፓትርያርክ የቅርሳ ቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሙዚየም መምሪያ የበላይ ኃላፊ እና የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀገረ ሀዲያ እና ሥልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ተከናውኗል::
በቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ልማት የመጀመሪያ የሆነው ይህ የነዳጅ ማደያ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ station እንዳለው ተነግሯል።
የአየር ማረፊያ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት የሠራው ይህ ልማት ቤተ ክርስቲያናችን በማኅበራዊ ሥራዎች ያላትን ከፍተኛ አገልግሎት ተጨማሪ ማሳየ እንደሆነም ተገልጿል።
በተያያዘ ዜና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ደብሩ ለሚያስገነባው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ክኒሊክ ሕንጻ መሠረት ድንጋይ ባርከው አስቀምጠዋል።
የልማት ሥራዎቹ ትውልድን በሥነ ምግባርና በሥርዓት ተከታትሎ ለሚፈለገው ሁነኛ ዓላማ ለማብቃና ማኅበረሰባዊ አገልግሎትን ለማጠናከር አዎንታዊ ድርሻ ይኖራቸው ተብሏል።
የቦሌ አየር ማረፊያ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ቦታውን በአግባቡ በመጠቀምና ለቤተ ክርስቲያን አገልግቶት በማዋል ረግድ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ የተገለጹት የደብሩ አስተዳዳሪ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ ባለሀብቶችን በማስተባበር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን መልክአ ምድር የማስተካከልና ለልማት ምቹ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን በጎብኝቱ ተናግረዋል።
በቀጠልም በብፁዓን አባቶችን ቡራኬ በመገንባት ላይ ለሚገኘው የግዙፍ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን የጉልላት መስቀል የማኖር ሥነ ሥርዐት ተከናውናል።
የደብሩ ምክትል ሊቀ መንበር በአስተዳዳሪው በመልአከ ሰላም ይትባረክ አሰፌ መሪነት ደብሩ እየሠራቸው የሚገኙ ቤተ ክርስቲያን ተኮር ትውልድ ጠቀም ሥራዎችን የዘረዘሩ ሲሆን በተለይም የይዞታን ከማስከበርና ቦታዎን በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ አርአያ ያለው ሥራዎችን መሥራታቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ደብሩ የአብነት ጉባኤ ቤትን በተለይም የአቋቋም ጉባኤን ከማጠናከር አኳያ 25 ለሚሆኑ ደቀ መዛሙርት ሠርከ ኅብስተና ማደሪያ ቦታን በማዘጋጀት ምቹ ሁኔታ ለተማሪዎች ተፈጥሮላቸው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ ብለዋል ምክትል ሊቀ መንበሩ።
በቀጣይም ለወጣቶችና የሥራ ዕድል የሚፈጥርና ለቤተ ክርስቲያንም በራስ አገዝ ልማቱ ላይ ተጨማሪ ድጋፍ የሚሆኑ ልማት ሥራዎችን ሊሠሩ እንደታሰቡበም ገልጸዋል።
በዚህ ሁሉ ሥራ ከፍተኛውን ደርሻ ከተወጡት ከደብሩ አስተዳዳሪ ጀምሮ ሰበካከ ጉባኤው ማኅበረ ካህናቱ በደብሩ ቦታ ላይ ተከራይተው ለቤተ ክርስቲያን ከፍቸኛ ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ ባለሀብቶች ምስጋና አቅርበዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ይትባረክ አሰፌ በበኩላቸው ከ5 ዓመት በፊት ወደዚህ ደብር በአስተዳዳሪነት ተመድበው ለተልእኮ ሲመጡ ብዙ አመች ያልነበረበትና ከጊዜ በኋላ ግን በደብሩ ከፍተኛ ጥረት በክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በመልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን ድጋፍና ክትትል በሀገረ ስብከቱ መመሪያ ሰጪነት የሚታይና የሚጨበት ለውጥ ለማምጣት ተችሏል ብለዋል።
በዚህም ሀገረ ስብከቱን ለመሩት ብፁዓን አባቶችን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ብፁዕ አቡነ ሄኖክና በአሁኑ ሰዓት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለሆኑት ለብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤና ለክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን የደብሩ ሰበካ ጉባኤና ማኅበረ ካህናት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው በዛሬዕ ዕለት በብዙ ድካምና ጥረት የተከናወኑ በርካታ ሥራዎችን መመልከታቸውን አስተውሰው ለዚህም ከደብረ አስተዳዳሪ ጀምሮ የሚመለከታቸውን አካላት አመስግነዋል።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው የተሠሩ ሥራዎችን አድንቀው በመተጋገዝና በመተባበር አንዱ ለአንዱ መልካም በመሆን ቤተ ክርስቲያናችን የጣለችብንን አደራ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ቤተ ክርስቲያን ከቋንቋ፣ ከነገድና ከአካባቢዊነት በላይ እንዲሁም ለወገኔ ይጠቅማል ከሚል ብሂል ውጭ ስለሆነች ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን ክብር በማስቀደም ሀገራዊ፣ ትውልዳዊና ታሪካዊ ሥራዎችን መሥራት ይገባል በማለት አሳስብዋል።
ደብሩ በዚህ አገልግሎት ድርሻ ለነበራቸው ሁሉ ምስጋና በማቅረብ ሥጦታ አብርክቶላቸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት በመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ምሕረት ቆሞሰ አባ ገብረመድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ መልአከ ሰላም ይትባረክ አሰፌ የቦሌ አየር ማረፊያ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ፣የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎችና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።