የቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ልማትና የአብነት ትምህርት ቤት!!
የቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በ1996 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ ተመሠረተ፡፡ በወቅቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ በነበሩት በክቡር አቶ አርከበ እቁባይ ፈቃድ፣ ልዩ ትዕዛዝ፣ መመሪያ ሰጪነትና በአካባቢው ምዕመናን ርብርብ ተመሥርቷል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ አጠቃላይ የይዞታ ቦታ 54,444 ካሬ ሜትር ስፋት አለው፡፡
በዚህ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ የሥራ ቦታ ተመድበው የሚሠሩ አገልጋዮች ብዛት 87 ናቸው፡፡
የደብሩ ዓመታዊ የገንዘብ ገቢ 4 ሚሊዮን 560 ሺህ የሚገመት ሲሆን በዚሁ መጠን ለሕንፃ ግንባታ የሚውል ገቢም ይገኝበታል፡፡
በደብሩ ውስጥ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች
በ2520 ካሬ ሜትር ስፋት ቦታ ላይ ያረፈ ዘመናዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ፣ ይህ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ዲዛይንን የተከተለ ሲሆን በሕንጻው ግራና ቀኝ አቅጣጫ ደግሞ የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ፅዮንን ሕንጻ ዲዛይንን የተከተለ ነው፡፡
ቀደም ሲል የሕንጻው ግንባታ በተጀመረበት ወቅት በደብሩ ውስጥ የርዕስ በርዕስ አለመግባባት ችግር የነበረ እና የሕንጻ ግንባታ ሥራውም ጥራት የጎደለው በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ ታሪክን የተከተሉ የሕንጻ አርክና ጌጣጌጥ ተጨምሮና ኮለኖቹ ወፍራም መጠን እንዲኖራቸው ተደርጎ ሕንጻው በጥንቃቄና በጥራት እየተገነባ ይገኛል፡፡
ከላይ የገለፅነው የሕንጻ ግንባታ ሒደትን ሲሆን በዚህ ደብር በዋናነት እየተገነባ የሚገኘው ሁለተኛው መሠረተ ልማት ዘለዓለማዊ የሆነው ሕንጻ የሊቃውንት አእምሮ ነው፡፡ መሬት በዕፀዋት፣ በአዝርዕትና በልዩ ልዩ ሐመልማላት እንደምትለመልም፣ እንደምታብብና እንደምታፈራ ሁሉ መምህራንም በቃለ እግዚአብሔር የሰውን አእምሮ ያለማሉ፡፡ የአብነት መምህራን ሥር የሰደዱ የዛፍ ግንዶች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ግንድ ከሌለ ቅርንጫፍ የለም፡፡ ግንድ ከሌለ አበባ የለም፡፡ ግንድ ከሌለ ፍሬ የለም፡፡ መምህራንም ከሌሉ ቤተ ክርስቲያን አትኖርም፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋስትናዎቿ የአብነት መምህራን ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከአብነት መምህራን ነጥለን መጥራት አንችልም፡፡
የኢትዮጵያ ትምህርት ምንስቴር መሥራቾች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ናቸው፡፡ የሊቃውንት አእምሮ ግንባታ ሥራ በእጅጉ የተጠናከረ በመሆኑ በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢሩ ዘለቀ እየተከናወነ ያለው የአብነት ትምህርት የማስተማር ሥራ በአሁኑ ጊዜ ብዛታቸው 111 የሚርሱ የልዩ ልዩ ጉባኤ መምህራን ካላቸው የመምህርነት ሙያ በተጨማሪ የሐድሳት ትርጓሜ ትምህርታቸውን በመማር የሁለተኛ ዙር ተመራቂ ዕጩዎች ለመሆን በቅተዋል፡፡
እነዚህ መምህራን ከቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል፣ ከሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል፣ ከሲኤምሲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከደብረ ፅጌ ቅዱስ ኡራኤልና ከየረር ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን የመጡ ሲሆን ከአገልግሎታቸው በተጓዳኝ የሐድሳት ትርጓሜ ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡
ባሳለፍነው የካቲት ወር 2008 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የደብሩን መሠረተ ልማትና የመማር ማስተማሩን ሂደቱን በመጎበኙበት ወቅት በሐድሳት ጉባኤ ቤቱ ተገኝተው በሰጡት መግለጫ አዚህ ደብር መተው የሐድሳት ትርጓሜ ትምህርት እየተማሩ የምናያቸው መምህራን በሊቅነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ሁሉንም ሊቃውንት በአገልግሎት ላይ አውቃቸዋለሁ፡፡ ትምህርት የሚፈልግ የተማረ ሰው ነው፡፡ የተማረ ሰው የትምህርት ጥቅምን ያውቃል፡፡ ትምህርት የማይማሩ ሰዎች ሁል ጊዜ ባለ ጉዳይ በመሆን ሲአስቸግሩና በየአድባራቱ ሰላምን ሲአደፈርሱ ይታያሉ፡፡
እነዚህ ሊቃውንት ግን ሥራቸውንም ትምህርታቸውንም አክባሪ ናቸው በማለት የማጠናከሪያና የማበረታቻ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በደብሩ ያለውንም የፍቅርና የሰላም ባህል አድንቀዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱም ከደብሩ ጎን በመሰለፍ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላችን የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ማስቀጠል ይቻል ዘንድ ነባር የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማለትም ማስመስከሪያ ሆነው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትን ማጠናከርና ወደ ትምህርት ቤቱ የሚገቡትንም ደቀ መዛሙርት የመቀበያ የብቃትና ጥራት ማረጋገጫ ፈተና በመስጠት፣ ለአብነት መምህራን ለዕውቀታቸው ደረጃ እንዲወጣ በማድረግ፣ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ያሉት መምህራን የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ሁሉም አካል የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል እንላለን፡፡