የቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያስተማራቸውን የሐዲሳት ትርጓሜ ደቀ መዛሙርት አስመረቀ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅ/ማርያም ቤ/ክ የተመደቡት የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ዘለቀ ለአምስት ዓመታት ያህል በሐዲሳት ትርጓሜ ያስተማሩአቸው ደቀ መዛሙርት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳ፣ ክቡር ቀሲስ በላይ መኮንን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል በጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ዋና ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና በርካታ ማህበረ ምዕመናን በተገኙበት ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም ለትምህርቱ በተሰጠው ደረጃ መሰረት ለሰላሳ አንድ ደቀ መዛሙርት የምሥክር ወረቀት ተሰጥቶአቸዋል፡፡
የሐዲስ ትርጓሜ ደቀ መዛሙርት በተመረቁበት በዚሁ ዕለት ልብሰ ተክህኖ በለበሱ ዲያቆናት “ወስተ ኩሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ” የሚለው የዳዊት መዝሙር በንባብ ቀርቧል፡፡
ጥንግ ድርብ የለበሱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ባረክና ክሙ መምህራን እምቤተ እግዚአብሔር ከመትስብኩ ወንጌለ ለሕዝበ ዓለም” የሚል ግሥ በለዘብ ቀርቧል፡፡ ከዚያም በማያያዝ በደብሩ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተለያዩ መንፈሳውያት መዝሙሮች ቀርበዋል፡፡
በመቀጠልም በሊቃውንቱ ቅኔያት ቀርበዋል፡፡ ከቀረቡት ቅኔያት መካከል በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢሩ ዘለቀ ከቀረቡት ቅኔያት መካከል ዘአምላኪየ የተባለውን ቅኔ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ግፍአ ሊቃውንት ተዘከረ እግዚአ ሊቃውንት እከመክኑ፣
በመቅበርት እስከ ሕይወቶሙ ተቀብሩአኮኑ፣
እንበለ ይሙቱ ቅድመ በሥጋ ወሥጋሆሙ ኮነኑ፣
የቅኔው መርሐ ግብር እንደተጠናቀቀ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት የምሥክር ወረቀት ሰጥተው እንደተጠናቀቀ ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ጥንት የነበረው የአብነት ትምህርት ቤት በዚህ ዘመን እየቀጨጨ መምጣቱ ይታያል፡፡ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል ጉባኤ ቤቶች እየተበተኑ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲህ አይነቱን ጉባኤ ስናይ ኪሣራ የለብንም ለማለት እንችላለን፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ በሚገኙት ሊቃውንት የገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያናትን ልትገለገል ይገባታል፡፡
የአብነት ጉባኤው ሊመረቁ የሚገባቸው ደቀ መዛሙርት አስቀድሞ የዕውቀት ብቃታቸው ሊፈተሽ ይገባል ማለትም ከሙያው የተመደበውን ትምህርት በሚገባ አጠናቀው መገኘት አለባቸው፡፡ የትምህርቱም ጥራት ሊጠበቅ ይገባዋል፡፡ በዛሬው ዕለት በቀረበው የቅኔ አሠጣጥ የመማር ውጤትን ተመልክተናል፡፡ ለወደፊቱም ትምህርቱን የሚቀጥሉ ደቀ መዛሙርት ይህንን ሥርዓት ሊከተሉ ይገባቸዋል፡፡ ትክክለኛው የመማር ማስተማር አካሄድ እየተማሩ ማገልገል፣ እያገለገሉ መማር፣ እየተማሩ ማስተማር፣ እያስተማሩ መማር ነው፡፡ እድገት ሊመጣ የሚገባው በማመልከቻ ወረቀት ሳይሆን በትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡ ሀገረ ስብከታችን እንዲህ አይነቱን የመማር ማስተማር ሂደት ይደግፋል በማለት ሰፋ ያለ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሚከተለውን አባታዊ መልእክትና መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ “ወኩሎሙ ደቂቅኪ ምሑራን በኃበ እግዚአብሔር” ልጆችሽ ከእግዚአብሔር የተማሩ ናቸው፡፡ የልጆችሽ መሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ የልጆችሽ መሠረታዊ አጀንዳ የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፍ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠበቆች፣ አቃብያነ ሕጎች፣ ጸሐፍያን ሊቃውንት ናቸው፡፡ ምሑራን ካሉ ዓለም ይስተካከላል፡፡ ዓለሙ የተበላሸው የመምህራን አቅም ስለደከመ ነው፡፡ የመምህራን አቅም ተገድቧል፡፡ ሌሎች አፍኖዋቸው ሂደዋል ነባር ትምህርቱ እየተበረዘ ነው፡፡ ለዛውና መዓዛውም እየተለወጠ ነው፡፡ ዜማው ዜማውን በማያውቁ ሰዎች እጅ ወድቋል፡፡ መምህራን ሲኖሩ ታሪክ ይጠበቃል፣ የተባረከ ልጅ ይወለዳል፤ ያድጋልም፡፡
የዚህ ደብር ሰዎች ዕድለኞች ናችሁ እላለሁ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ ሕንፃ ኮሚቴ ካህናትና ምዕመናን እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉ ያላት ሀገር ናት፡፡ በትንቢተ አሞፅ እንደተፃፈው የኢትጵያን ሕዝብ እግዚአብሔር ይወደዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰዎች ቀርቶ የኢትዮጵያ ድንጋይ ስምአኒ እግዚኦ ጸሎትየ እያለ ነው ያለው በማለት ብፁዕነታቸው ሰፋ ያለ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን “አስግረ ለነ ቆናጽለ እለ ያማስኑ አፀደ ወይንነ” የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመጥቀስ የሙስናን፣ የብልሹ አሠራርንና የዘረኝነት አስከፊነትን ገልፀው መርሐ ግብሩን አጠናቀዋል፡፡
{flike}{plusone}