የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ሐዋርያዊ ጉዞና የልደት በዓል በደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ

0126

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ  ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመንበረ ፕትርክናቸው ላይ ከተቀመጡበት ጊዜ ጀምሮ ከሐገር ውጪና በሐገር ውስጥ በርካታ ሐዋርያዊ አገልግሎት የሰጡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ቅዱስነታቸው ከሰጡአቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት መካከል ታህሳስ 29 ቀን 2006 ዓ.ም የሚከበረው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስና የንጉሥ ላሊበላ የልደት በዓል በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ቅዱስነታቸው ሰኞ  ታህሳስ 28 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 6፡00 ሰዓት በላሊበላ አየር ማረፊያ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመገኘታቸው ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የደብብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ ፀሐይ አባ ወ/ተንሣኤ አባተ የላሊበላ ደብረ ሮሐ ውቅር አድባራት አስተዳዳሪ፣ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በመቀጠልም በቤተ ማርያም ውቅር ደብር አውደ ምህረት ላይ በርካታ ማህበረ ምዕመናን በተገኙበት በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የተለያዩ መዝሙሮችና መወድስ ቅኔያት ቀርበውላቸዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንኳን ደህና መጡ ንግግር አድርገውላቸዋል፡፡
በማያያዝም ቅዱስነታቸው በዚህ ታሪካዊ ቦታ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ጉብኝት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው ነገር ግን ለረጅም ጊዜ  በውጩው ዓለም በመቆየታቸው በተደጋጋሚ የመጎብኘት ዕድሉ ያላጋጠማቸው በመሆኑ ቦታውን ሲናፍቁት እንደቆዩና አሁን ግን ፈቃደ እግዚአብሔር በመሆኑ ቦታውን ስላዩ የተሰማቸውን ደስታ ደስ ብሎኛል፣ ደስ ብሎኛል ፣ደስ ብሎኛል በማለት ሦስት ጊዜ ደስታቸውን ገልጸው ቃለ ቡራኬ  በመስጠት ወደ ተዘጋጀላቸው የክበር ቦታ አምርተው ከዚያም ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት በቤተ ምርያም ውቅር ቤተ መቅደስ በመገኘት ጸሎተ ኪዳን አድርሰው ሥርዓተ ቅዳሴውን መርተዋል፡፡
ከሥርዓተ ቅዳሴው ፍጻሜ በኋላ ቤዛኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ እያሉ ሊቃውንቱ ከጋራው ስር እና ከጋራው ጫፍ ሆኖ የመላእክትን እና የእረኞችን የደስታ መታሰቢያ  መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ቅዱስነታቸው ለተሰበሰበው ማህበረ ምዕመናን የሚከተለውን ትምህርታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት ተወልዷል በማለት አስቀድመው ቅዱሳን መላእክት እንደተናገሩት የዛሬው በዓላችን የዓለም መድኃኒት የተወለደበት፣ ሰላም የተገኘበት፣ መረጋጋት የተገኘበት ዕለት ነው፡፡ ከሩቅ ምሥራቅ የመጡ የጥበብ ሰዎች በኮከብ ተመርተው ቤተልሔም ደርሰው ለተወለደው መሲህ እጅ መንሻ  ሰጥተዋል፡፡

0243

በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ ግን ሕጻኑን ለማጥፋት ወይም ለመግደል በማሰብ በኮከብ ተመርተው የመጡትን ሰዎች ስትመለሱ በእኔ አካባቢ ተመለሱ ብሎ መመሪያ ቢሰጥም የክፋት ሥራው ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ወቅት መንጉቻቸውን ሲጠብቁ ያደሩ እረኞች በዙሪያቸው ታላቅ ብርሃን ስለመራላቸው እጅግ በጣም ተገርመዋል፡፡ ያዩትንም ድንቅ ነገር ወደ ከተማ ሄደው መስክረዋል፡፡ እረኞቹ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ ያደሩበት ቦታ በአሁኑ ጊዜ ኖሎት እየተባለ ይጠራል በማለት እጅግ በአማረ አገላለጽ ቅድስነታቸው ትምህርታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በዚያ ታሪካዊ ቦታ የተገኙትንም ሁሉ ዕድለኞች ናችሁ ብለዋቸዋል፡፡ በማያያዝም ቅዱስነታቸው ቡራኬና ቃለ መሀዳን አድርገው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖአል፡፡ ከበዓሉ ፈጻሜም በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን በቅዱስ ላሊበላ የታነፁትን 10 ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጉብኝተዋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላችን  ከቦታው ድረስ በመሄድ በአጠናቀረው መረጃ መሠረት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት ለማክበር  ከመላው ሀገራችን የመጡ ምዕመናን ቁጥር ከአምስት መቶ ሺህ በላይ እንደሚገመትና ከሀገር ውጪ ከተለያዩ ዓለማት የመጡት ጎብኚዎች ደግሞ ቁጥራቸው ከአስር ሺህ ያላነሰ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡
ይህም ደግሞ የቤተክርስቲያናችን ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ያመላክታል፡፡  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮችም ቁጥራቸው ሊጨምር እንደሚችል ተስፋ ሰጪ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

{flike}{plusone}