የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አምስተኛ ዓመት በዓለ ሢመት በታላቅ ድምቀት ተከበረ!!
በዝግጅት ክፍሉ
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ5ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና የሥራ ኃላፊዎች ፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሰንበት ት/ቤ ወጣቶች በተገኙበት ቅዳሜ የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
የየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ደብር ሊቃውንት “ዝንቱሰ ፓትርያርክ አባ ማትያስ ዘተፈነወ ውስተ ምድርነ ስዩም በኃበ እግዚአብሔር፡፡ ረሰዮ እግዚኡ ለውእቱ ማትያስ ይትለዓል መንበሩ፤ ስዩም በኃበ እግዚአብሔር፤ ይስአል ለክሙ በእንተ ምሕረት ነዋ ማትያስ ፓትርያርክ የሚል ያሬዳዊ መዝሙር በዝማሜ ተዘምሯል፡፡
ዝንቱስ ብእሲ ዘእምንእሱ ሕይወቱ ውስተ ቤተ እግዚአብሔር ከመ አብ ዘኮነ ለእጓለ ማውታ ፈጻሜ ተጽናሶን ለእቤራት እስመ ውስተ ልብሱ ክህነት ኩሉ ዓለም፡፡ ሀራሲ በእርፈ መስቀል ሰባኬ ወንጌል አባ ቅዱስ ማትያስ ክቡር ብእሴ እግዚአብሔር ለአሕዛብ መምህር ትክበር ነፍስየ በቅድሜከ ዮም ባርከኒ አባ እንሳዕ በረከተከ የሚለው ያሬዳዊ ዜማ በቁም ዜማና በወረብ በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተዘምሯል፡፡ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መወደስ ቅኔ ተበርክቷል፡፡
በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የደቡብ ማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓሉን አስምልክተው ባስተላለፉት መልእክት ኖላዊነት ትልቁ የቤተ ክርስቲያን ሥራ ነው፡፡ ሊቀ ኖሎት ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ዋጋ ለማግኘት ተግዳሮትን ማለፍ ግድ ይላል፡፡
“ከእናንተ ሃይማኖት የጎደለው እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ሕዝባችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ተግተን ልንጠብቅ ይገባናል፤ የምዕመናንን መንፈሳዊ ሕይወት ለመጠበቅ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት፣ ሰንበት ት/ቤቶችን ማቋቋም፣ ሰላምን ማስፈን፤ ዘረኝነትንና ሙስናን መቃወም፣ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት መጠበቅ፤ የገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን በቂ አገልግሎት እንድታገኝ ማድረግ ይኖርብናል ፡፡ አቤቱ አምላካችን ሰላምን ስጠን እያልን ተግተን ማስተማርና መጸለይም አለብን በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚከተለውን አባታዊ መልእክት ሲያስላልፉ እግዚአብሔር አምላካችን ሁሉን የፈጠረና ያስገኘ በመሆኑ እንድንከተለው ይፈልጋል፡፡ ፈቃዱን የሚያስፈጽሙ አካላትን ሲያስቀምጥ ኑሯል፤ ወደፊትም እንደሚያስቀምጥ ገልጿል፡፡ ካህናት በመንፈሳዊ እውቀት መገንባት አለባቸው፡፡ ቅድስናን፣ ሐላፊነትን፣ ጥንቃቄን በተሞላ የሚሠራ ሥራ ዋጋ የሚያሰጥ ሲሆን ከዚህ ውጭ ከሆነ ቅጣቱ የከፋ ይሆናል፡፡ካህን ሕዝበ እግዚአብሔርን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ባለ አንድ፤ ባለ ሁለትና ባለ ሦስት መክሊት በተሰጣቸው መጠን ሊያተርፉ ይገባቸዋል፡፡ ምዕመናንን የሚጠብቅ ካህን ቤተ ክርስቲያን መድባ እያለች ምእመናንን ተኩላ ሲነጥቃቸው ካህናት የት አሉ? የሚያወዛውዝ ነፋስ ከየት መጣ?እግዚአብሔር ሁሉን የሰጠ ለካህኑ ነው፤ ለሕዝባችን እንዴት ሰላም መስጠት አቃተን? ቤተ ክርስቲያን ከሌለች ደግሞ እኛ መቀጠል አንችልም፡፡ ያለመታከት ማስተማርና መምከር ይጠበቅብናል፤የማይገሰስ ነፃነት፣ የማይበጠስ አንድነት አለን፤ ሕዝባችን ይህንን ሊረዳው ይገባል፤የሕዝባችን ማኅበራዊ ትስስር ጠንካራ ነው፤የራሳችንን ትተን የሌሎችን የአኗኗር ዘዴ ልንከተል አይገባንም፤ነባሩንና ተወዳጁን እሴታችንን እንዳናጣ መጠንቀቅ አለብን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚገዛው የእግዚአብሔር ስም ነው፤ነገሮች ሁሉ ወደነበሩበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ አለባቸው፤አንዱ የሌላውን ክብር ሳይነካ ጥያቄውን ለመንግሥት ያቅርብ፤ መንግሥትም ጥያቄዎችን እየተቀበለ ይመልስ በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ መልእክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡