የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባዖት ተፈጸመ !!!!

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዐሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እና  ብፁዓን አበው  ክብርት ፕረዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለ ስልጣናት ብዙ የአሃት አብያተክርስቲያናት ሊቃ ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያን መምህራን እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ስለቅዱስነታቸው የረጅም ጊዜ ወዳጅነት እና ስለቤተክርስቲያን አንድነት በጋራ ብዙ ይጥሩ እንደነበር አውስተው ጥረታቸው ሰምሮ ይሄው በክብር ሀገራቸው ገብተው የተመኙት ሆኖላቸዋል ብለዋል።

የቅዱስነታቸው አጭር የህይወት ታሪክ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በጽሑፍ ተነቧል።

በቅዱስነታቸው ሥርዐተ ቀብር ላይ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዘስውር እምኔነ ይዜሰ ክሱተ ኮነ በሚል መነሻ ስለቅዱስነታቸው ምስክርነት እና ትምህርት የሰጡ ሲሆን የሕይወት ዘመን ሥራቸውን ቅዱስ ገድል ሲሉ ገልፀው መንገዳቸውም ፍኖተ መስቀል ነበር ሲሉ  መስክረዋል።

የቅዱስነታቸው ጸሎትና ምኞት ለሀገራቸው ምድር እንዲበቁ ስለነበር በሚወዷቸው ልጃቸው በጠ/ሚ ዶር አብይ አህመድ አማክኝነት ለሀገራቸው እና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ስለበቁ  ይሄንም በማየቴ እድለኛ ነኝ ብለዋል።

ክብርት ፕረዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠው በተዘጋቸው የክብር መዝገብ ላይ ኃዘናቸውን ገልፀዋል።

ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ኀዘናቸውን በመግለጽ ክብራቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እና  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ  የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኢኦተቤ መጋናኛ ብዙሃን ሥራ አስኪያጅ በሊቀ ማዕምራን ፋንታሁን ሙጬ እየተመራ እጅግ ብዙ ምዕመናን በተገኙበት በክብር ተፈጽሟል።

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ ክፍል በቅዱስነታቸው ኅልፈተ ሕይወት ማዘኑን ይገልጻል።

በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ