የቤቶችና ሕንጻዎች ድርጅት ከፍተኛ የልማት ዕድገት አስመዘገበ
ድርጅቱ ተጨማሪ ሕንጻዎችን ለመገንባት ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር የ3 ቢሊዮን ብር ስምምነት ሊፈራረም ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ የቤቶችና ሕንጻዎች ድርጅት ሊቀ ጳጳስ፣ የቤቶችና ህንጻዎች ድርጅት፣ አመራሮች እና የቻይና ጂኦሲሲ ኩባንያ ወኪሎች በተገኙበት ግንቦት 28 ቀን 2006 ዓ.ም በልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ የጋራ ውይይት ተደርጓል፡፡ በስምምነቱም መሠረት ይገነባሉ የተባሉትን ሕንጻዎች የሳይት ፕላን አቀማመጥ አስመልክቶ በሳይት ፕላን ባለሙያው አርክቴክት ፍቅረ ሥላሴ በስላይቭ የተደገፈ መግለጫ ቀርቧል:: የኩባንያው ወኪሎች የሆኑት ቻይናውያንም በቀረበው ሳይት ፕላን መሠረት የቦታዎቹን የጥቅም ደረጃዎች፣ የሕንጻውን ተዋረድ፣ የተለያዩ ቦታዎች ፕላን የልማቱን መስተጋብር፣ እይታዎችን፣ አስመልክተው ላቀረቡአቸው ጥያቄዎች ባለሙያው ተገቢ ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡
እንዲህ አይነቶቹ የሁለትዮሽ የጋራ ውይይቶች በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱ ሲሆን በሁሉም ውይይቶች የተሻለ መግባባት ተፈጥሮአል፡፡ ውይይቱ ለወደፊቱም ቀጣይ እንደሚሆን እና ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ጋር የጋራ ውይይቱ እንደሚቀጥል የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አብራርተዋል፡፡ በተመሳሳይም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት የድርጅቱን ጠቅላላ እንቅስቃሴ አስመልክተው በጽ/ቤታቸው የሚከተለውን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ቤተክርስቲያናችን ቀደም ሲል ተወርሰውባት የነበሩት ቤቶች እና ሕንጻዎች ከተመለሱ ራሷን በራሷ ማስተዳደር እንድትችል ይህ የልማት ድርጅት ቤቶችን እንዲአስተዳደር ከተቋቋመበት ዕለት አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የተመለሱ ቤቶችን ብቻ በማስተዳደር ሲሢራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ይህ የልማት ድርጅት ቤቶችን እንዲያስተዳድር ከተቋቋመበት ዕለት አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የተመለሱ ቤቶችን ብቻ በማስተዳደር ሢሠራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ስለዚህ ባለፉት 20 ዓመታት የነበረን እንቅስቃሴ የተረከብናቸውን ቤቶች በማስተዳደር ላይ ያጠነጠነ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደስያሜ አጠራሩ የቤቶች እና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት ሰፋ ያለ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል የልማት ሁኔታው በማከናወን ላይ ይገኛል፤ ብዙም ያልተገፋበት ነበር፡፡ ይሁንና ባለፈው 2005 ዓ.ም የቅዱስ ዲኖዶስ ስብሰባ ወቅት የልማት አቅጣጫዎች ተነድፈው ስለነበር በጥቅምቱ ጉባኤ ላይ የቤቶች እና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት በረጅም፣ ባጭርና በመካከለኛ በሚል ጥናት በመቅረቡ ቅዱስ ሲኖዶስም በቀረበው ጥናት መሠረት አመራር የሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በጥቅምቱ 2005 ዓ.ም በሲኖዶስ ጉባኤ ባቀረብናቸው ጥናቶች መጀመሪያ የሚለሙት ልማቶች ምንድን ናቸው? እንዴት ነው የምናለማቸው? መቼ ነው የምናለማው? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ነበር ያቀረብነው፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያንዋ በያዘቻቸው ትርፍ ቦታዎች ላይ ምን መሥራት አለባት? መቼ መሥራት አለባት? በሚል ሥራዎችን የመለየት ተግባር ነበር ያከናወነው፡፡
በዚሁ መሠረት በይዞታችን ሥር የሚገኙትን ወደ አስር የሚደርሱ ቦታዎችን እና የኪስ ቦታዎችን ለይተን እነዚህን ለማልማት የሚአስችለውን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በማውጣት የሚል ነበር የተከተልነው ስልት፡፡ ከዚያም ባሉን ክፍት ቦታዎች ላይ መሥራት እንችል ዘንድ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መረከብ አለብን ብለን ተነሳን፡፡ ከቅጽ 006 ሠነድ ውጭ ቦታዎቹም ሆኑ ቤቶቹ የቤተ ክርስቲያን ንብረቶች መሆናቸውን የሚአሳይ ማስረጃ አልነበረም፡፡
ስለዚህ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታና ፕላን ለማውጣት ከፍተኛ ፈተና እና ውጣውረድ ገጥሞን ነበር፡፡
የደርግ መንግሥት ቤቶቹን ወርሶ ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለው ሁኔታ ቤተክርስቲያናችን የተሟላ ሰነድ ስላልነበራትና በመንግሥት በኩልም ይምጣ የተባለው ማስረጃ ባለመገኘቱ በወቅቱ የእኔ ነው ብለን የምናረጋግጥበት አግባብ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ካርታና ፕላን ለማውጣት በምንሄድበት ወቅት ቤቶቹ እንደ ጨረቃ ቤት በመቆጠራቸው የይዞታ ሰነድ ለማውጣት ሥራዎች ጊዜ በመውሰድ ይጓተቱብን ነበር፡፡ ሆኖም ይዞታችን እንደጨረቃ ቤት ሊታይ አይገባም በማለት ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጽ/ቤት ጋር የጋራ ውይይት አድርገን የተወሰኑ ቤቶች ባለቤቶች ሆነናል፡፡ ወደ አስራ አምስት የሚጠጉ ሕንጻዎች አሉን፡፡ ለአስራ አምስቱም ሕንጻዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ወጥቶላቸዋል፡፡ በቪላ ቤቶችም ደረጃ እንደዚሁ፡፡
ከዚህ አንጻር ባለፈው ጥቅምት ጉባኤ ላይ ስናቀርብ በነበረን እንቅስቃሴ ካሉን ቤቶች ላይ አስራ ዘጠኝ ብቻ ቪላ ቤቶች የካርታ ባለቤቶች ነበርን፡፡ በአሁኑ ሰዓት ማለትም ከጥቅምት እስከ ግንቦት ድረስ እጃችን ላይ የገባ አርባ ሁለት ሲደርስ ጉዳያቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ቤቶች 20 ይደርሳሉ፡፡ ወደ አንድ መቶ አሥራ ዘጠኝ የሚደርሱ የቀበሌ ቤቶች በማዕከል ካርታ ለመውሰድ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ማለትም ኋላ ስናለማ ለእያንዳንዱ ቤት ካርታ ስለሚአስፈልግ ለሥራው እንችገራለን፡፡ ስለዚህ አጎራባች የሆኑ ቤቶቻችንን አንድ ላይ አድርገን ለማልማት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ላይ ሕንጻ ለመገንባት ውህደትን የተከለከልንበት ሁኔታ ነው ያለው ጠቅላይ ቤተ ክህነት መዝገብ ቤት እና ከዚህ ከድርጅቱ የሚገኙት ፋይሎች ተፈልገው እና ተሰባስበው ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከሚቴዎቹ የፋይል ማጣራት ሥራዎችን ቅዳሜ እና እሁድ የዕረፍት ጊዜአቸውንም ጭምር ተጠቅመው እንዲሠሩ እያደረግን ፋይሎችን እየመረመርን መረጃዎቻችንን እያጠናከርን ነው፡፡
ስለዚህ መረጃዎቻችንን በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት እና በድርጅቱ ጽ/ቤት እንዲቀመጡ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት ፋይሎቻችን በየዘርፉ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡
መንግሥት የሚከተለው የመሬት ፖሊሲ እና በእኛም በኩል የተሟላ የይዞታ ሰነድ ባለመኖሩ የካርታ ማውጣት ሥራችን እጅግ አድካሚ ነበር፡፡
119 የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ የነበረውን ቅሬታ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ የተፈረመ ደብዳቤ ለፍትህ ሚኒስቴር ስለቀረበ አወንታዊ ምላሽ እንደሚሰጠን ተስፋ በማድረግ ጉዳዩን እየተከታተልን ነው ያለነው፡፡
አንድ አንድ የልማት ሥራዎችን በተመለከተ በመልሶ ማልማት ልትሰተናገዱ አትችሉም የሚል ሐሳብ ቢኖርም እንኳን ጉዳዩን ለክቡር ከንቲባው በማቅረብ መፍትሔ እየፈለግን ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ በመሬት ካርታ እና በባለቤትነት ሕጋዊ ማረጋገጫ ላይ ፈተናዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ፈተናዎችን በመግባባት እና በመንግሥት በኩልም ባለው ቅንነት የተሞላው አሠራር መሠረት ለችግሮቹ መፍትሔ እያስቀመጥንላቸው ነው፡፡
አሁን በቅርብ ሁለት ባለ አራት ሕንጻዎች በወረዳ አንድ (መሀል ፒያሳ ጀርባ) ባለው ቦታ ላይ የግንባታ ሥራ እንድናከናውን ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ይህንን ፕሮጀክት ያጠኑልን የቤተክርስቲያናችን ልጆች የሆኑ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ጥናቱን የሠሩልን ባለሙያዎች ከቤተክርስቲያናችን ወጪ እንዳይወጣ በማሰብ በነጻ ነው የሠሩልን፡፡ ባለሙያዎቹም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት የሚአገለግሉና ሲቢል ሰርቪስ የሚሠሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለነዚህ ውድ የቤተክርስቲያናችን ልጆች የላቀ ምስጋናየን አቀርባለሁ፡፡
እነዚህ ሕንጻዎች አሁን ባለው ወቅታዊ ዋጋ ማለትም አንዱ ሕንጻ 48 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል፡፡ አንዱ ደግሞ 20 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል፡፡ እነዚህ ሥራዎች ሢሠሩ የቤተክርስቲያናችን የቦርድ አካል ሥራውን እየገመገመና የደረሰበትን እያየ ስለ አጸደቀው ነው ወቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለመታየት የበቃው፡፡
ሌላው ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቀው ሥራችን ከቅድስተ ማርያም በታች ባለው ቁልቁለት ወደ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታጠፊያ ብርሃን እና ሰላም ድርጅት የሚይዘውን መንገድ እና በቅድስተ ማርያም ትይዩ ከማህበረ ቅዱሳን ሕንጻ አንስቶ በተለምዶ ጎንደር በር እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ድረስ ባሉት ቦታዎች ላይ የቤተክርስቲያናችንን ማንነት እና ታሪካዊ ይዘት የሚአሳይ ዲዛይን እና ገዳማዊ ገጽታ ሊኖረው የሚችል ዘመናውያን እና ታሪካውያን ሕንጻዎችን መገንባት እንዳለብን ለማመን በዚሁ ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት ስናደርግ ቆይተናል፡፡
እነዚህ የልማት ሥራዎች አንዳንዶቹ በእኛ ይዞታ ሥር ባይሆኑም እንኳን አሁን ባቡር በሚሠራበት በመሀል ፒያሳ ላይ የእኛ ይዞታ የሆኑ አሉ፡፡ ነገር ግን እነሱን ቦታዎች ወደ ፊት እኛ የማንጠቀምባቸው መሆናቸው ተገልጧል፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ካርታ ያወጣንባቸው ስለሆኑ በቦታ ምትክና በካሳ ክፍያ የምንስተናገድበት ሁኔታ እንዳለ በደብዳቤ ተገልጦልናል፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ቢኖሩም በዙሪያችን ማለትም በአራት ኪሎ አካባቢ የምናለማቸው በምትክ ቦታዎቹን እያካካስን እንሠራለን የሚል እምነት አለን፡፡
ስለዚህ እነዚህ ቦታዎች ሰፋ ያለ ካፒታል ይጠይቃሉ፡፡ የጥናት ሥራችንን የምንሠራው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሁለት ባለሙያዎችን እና ኢኮኖሚስቶችን ይዘን ነው የምንሠራው፡፡ ባለሙያዎቹም ሆኑ ኢኮኖሚስቶቹ የሚከፈላቸው ክፍያ የለም፡፡ ሥራውን የሚሠሩልን በበጎ ፈቃድ በነጻ ነው፡፡ ምክንያቱም የቤተክርስቲያን ልማት ማለት የሀገር ልማት ማለት ነውና፡፡ ከላይ የጠቆምናቸውን ጥናቶች ነው ባለፈው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ያቀረብናቸው፡፡ ለድርጅቱም መተዳደሪያ ደንብ ቀርጸን ይህንኑም ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርበን ዳብሮ እንዲቀርብ በተሰጠው መመሪያ መሠረት በቦርድ እየታየ ነው ያለው፡፡
ሌላው በአክሱዮን መጀራጀት የሚል ሲሆን ይህም ለቤተክርስቲያናችን አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አክሲዮን ሲመሠረት አክሲዮን መሥራቾቹ እነማን ናቸው? የሚለው አንዱ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ ለወደፊት በምንገነባቸው አዳዲስ እና ታሪካውያን ሕንጻዎች ዙሪያ ጂሲኦሲ ከተባለ አንድ የቻይና ኩባንያ ጋር ውይይቶችን አድርገን ነበር፡፡ የቻይና ኩባንያ ባለቤቶችም የሚለሙ ቦታዎችን ለይተው ተመልክተዋል፡፡
ስለዚህ የሀሳብ አቅጣጫችንን በምን መልክ ነው የምንሠራው የሚለውን በጽሑፍ አስደግፈንላቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያናችን ትልቁ የማይንቀሳቀስ ሀብቷ መሬት ነውና፡፡ በተጨማሪም በቴክኒክ ብቃት ያላቸው ልጆችም አሉአት፡፡ ባለው ነገር ግን ልማቱን የምናለማበት የፋይናንስ እጥረት አለብን የሚል ሀሳብ ነው ያቀረብንላቸው፤ ከዚያ በኋላ ሊኖራቸው የሚችለውን ፍላጎት በኢሜል ስንመላለስ ቆይተናል፡፡ በዚሁም ከመግባቢያ ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ እነርሱ በሪል እስቴትም ደረጃ አብረን እንሥራ የሚል ሐሳብ አላቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ደግሞ በኮንስትራክሽን ሕግ መመዝገብ አለባት፤ ይህ ደግሞ ይህንን ለመሥራት ከተቋቋመችበት መርሕ አንጻር ሊያስኬዳት አይችልም፡፡
ስለዚህ ይህ አሠራር ሁለተኛው አሠራር ነው፡፡ እኛ ያለን መሬት ነው በሚል ተግባብተን በዚህ አካሄድ ነው እየሠራን ያለነው፡፡
በዚህም ሊኖረን የሚችለው መረጃ ምንድን ነው በሚል የመሬቱን ቅርጽ የያዘ ፕላን ተዘጋጅቶ ያሳይት ፕላኑ እንዲቀርብ ተደርጎ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንሠራቸዋለን ያልናቸው ሁሉ ቀርበው፣ በተለይም በጠቅላይ ቤተክህነት ዙሪያ ከማህበረ ቅዱሳን ሕንጻ አንስቶ እስከታች ድረስ በአራት ኪሎ ዙሪያ አንስተን እስከ ብርሃን እና ሰላም ድርጅት ድረስ ዘመናዊ ሕንጻ መገንባት አለብን በሚለው ሀሳብ ቦርዱ ጊዜውን መስዋእት አድርጎ እና ሥራውን ገምግሞ መሆን የሚገባውን በአጥኚው ቡድን ለግንቦቱ 2006 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲቀርብ በመደረጉ ቅዱስ ሲኖዶስም የቀረበውን ጥናት ተመልክቶ፤ በመልካም ጎን ተቀብሎታል፡፡
አንዳንድ ጊዜ የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ ከቻይና ጋር የምትሄዱት በምን አይነት ነው የሚል እኛ ያሰብነው ቤተክርስቲያንዋ ተጠቃሚ መሆን አለበት ከምንሠራቸው ሕንጻዎች መካከል ለንግድ ማዕከል የሚሆኑ ይኖራሉ፣ ለመኖሪያ የሚሆኑ ይኖራሉ፣ ለመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚሆኑ ይኖራሉ፣ ዙሪያውን ዘመናዊ የሆኑ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡
ዛሬ የምናያቸው አርቲፊሻል የሆኑ ማለትም ዘመን አመጣሽ የሆኑ ሕንጻዎችን ዙሪያውን ይገነባሉ የሚል እቅድ ይዘን አልተነሳንም፡፡ ይህች ቤተክርስቲያን ጥንታዊት ናት፣ ታሪካዊት ናት፣ ስለዚህ ለማንነቷ መገለጫ የሚሆን ሕንጻ ሊቀመጥበት ይገባል ከሚል ስምምነት ላይ ነው የደረስነው፡፡ ቤተክርስቲያን የታሪክ፣ የቅርስ፣ የሥነ ሕንጻ፣ የሥነ-ፊደል ባለቤት መሆንዋን የሚአሳዩ ሕንጻዎች መቀመጥ አለባቸው ብለን ነው የወሰድነው፡፡ የአካባቢው ማስተር ፕላን ምንም ይበል ምን ቅርጹን ይዞ፣ እስታንዳርዱን ጠብቆ ይሠራል፡፡ የገዳም ሠፈር መሆኑን ሊአሳይ የሚችል ይዘት ያለው ሕንጻ እንዲቀመጥ ነው ያሰብነው፡፡ መጪው ትውልድ ሕንጻውን በማየት ቤተክርስቲያንዋ ትናንት ምን ነበረች? ዛሬስ ከምን ላይ ናት? ነገስ ምን መሆን አለባት? የሚለውን አቅጣጫ ያሳያል በሚል አሳቤ ነው፤ ዲዛይኑ እንዲቀመጥ የተደረገው፡፡
ስለዚህ አሁን ለቅዱስ ዲኖዶስ ቀርቦ የሚታየው ያንን የሚገልጽ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠን አቅጣጫ ሥራውን ሀ ብለን እንሠራለን፡፡ ነገር ግን አሁን የሚታየው የቤተክርስቲያን የኢኮኖሚ አቅም አንድን ሕንጻ እንኳን ለመሥራት የተቸገርንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከቻይናዎች ጋር የምንሠራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ጥቃቅን ልማቶችን በተመለከተ ማለትም ሁለት ባለ አራት ሕንጻዎች በመሐል ፒያሳ እየሠራነው እንዳለው አይነት በኪስ ቦታዎች ላይ ሰፊ ካፒታል በማይጠይቁት ላይ በራሳችን ኃይል እንድንሠራ ነው ቻይናዎቹም ሪኮማንድ ያደረጉን፡፡
ስለዚ ደህ ይህንን ለመሥራት ከቅዱስ ፓትርያርኩ እና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር በመምከር ቀጣዮቹን ሥራዎች እንሄድባቸዋለን ብለን እንገምታለን፡፡ ካሰብነውም አንዱ ምንይልክ ሆስፒታል ፊት ለፊት ሁለት ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የፕላን ስምምንት ወስደናል፡፡ ቢዝነስ ፕሮፖዛላችሁንም አቅርቡ ተብለናል፤ ይህንንም እያጠናቀቅን እንገኛለን፡፡ በፒያሳ አካባቢ ካርታ ወስደን ቢዝነስ ፕላኑን ደቨሎፕ አድርገን ለአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ካቀረብን በኋላ ሁለቱ ቦታዎች ተዋሕደው መሥራት እንደማይፈቀድ እና ከዚያም በሻገር በዚህ አካባቢ መንግሥት ሊያለማቸው የሚገቡ ቦታዎች ናቸው በሚል በካሣ ነው የምትሰተናገዱት ተብሎ ሀሳብ ቀርቦልናል፡፡
ይሁንና ይህ አግባብ አይደለም ቤተክርስቲያን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ስላላት ባለቤት ናት፤ መሥራት እስከቻለች ድረስ ሊፈቀድልን ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርበን እየታየ ነው ያለው፡፡
ጠቅለል ባለመልኩ ስናይ ከበፊቱ 20 ዓመት ከነበረው አሠራር በተሻለ ወደፊት ለመግፋት እየሄድን ነው ያለነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም እያሳሰበን ያለው ቦታዎቹ ካለሙ ቁጭ ብለው የሚጠብቁን ስላልሆነ መንግሥት ከተማዋን ለማልማት ካለው ፈጣን ፍላጎት ጋር በካሣ እየተስተናገድን መሥራት አለብን የሚል ነው፡፡ እኛም ፈርሰው የሚለሙ ቦታዎችን በመለየት እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው፡፡ ወደ ልማት ለመግባት ትልቁ ችግር ባለቤት ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ህንጻዎችን ከተረከብን ጀምሮ የቆየው አሠራር የባለቤትነትን መብት ለማረጋገጥ የተሄደበት ርቀት ባለመኖሩ ፈጥነን ወደ ልማት ለመግባት ይዞታዎችን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሰፊ ክፍተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ አንድ አንድ ቦታ ላይ ፎቁ የእኛ፣ ምድሩ የሌላ፤ ሆኖ የተቸገርንበት ሁኔታ አለ፡፡ ካርታ የጠየቅንላቸውን በፎቁ ብቻ ነው የተባልንበት ሁኔታ አለ፡፡
ስለዚህ ካርታ ማውጣት ቀላል ፈተና አልነበረም፡፡ አሁንም ቢሆን በካርታ ማውጣት ሂደት እየገጠመን ያለው ሌላው ችግር ሳሎኑ የእኛ፣ መኝታ ቤቱ የሌላ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን እያጣጣምን የምንሄድበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በክፍለ ከተማ የተቀመጡት የመንግሥት ኃይሎች ያቀረብነውን ጥያቄ በሥርዓት በመመልከት ሕጋዊ ድጋፍ እየሰጡን ይገኛሉ፡፡
በመጨረሻም ማስታላለፍ የምፈልገው ማንኛውም የቤተክርስቲያን አካል በግለሰብም ይሁን በተቋም ደረጃ መንግሥት በቀየሰው የልማት አቅጣጫ እና እኛም እያለማን ካለነው የቤቶች ግንባታ አንጻር ችግሩ ጊዜ የማይሰጥ ስለሆነ ሁሉም አካል እኛንም ጨምሮ አሁን ለተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ በቅንነት መደገፍ ይገባል፡፡ የጥንቶቹ አባቶች ድንጋይ ተሸክመው፣ ውሃ ቀድተው፣ የሠሩልንን ሕንጻ እኛ ደግሞ ደንጋይ ባንሸከም፣ ውሃ ባንቀዳ፣ እነሱ የሰበሰቡልንን ሀብትና ንብረት በአግባቡ ጠብቀን እና ተጨማሪ ልማት ሠርተን ቤተክርስቲያን በማህበራዊ፣ በመንፈሳዊ እና በኢኮኖሚአዊ እንቅስቃሴ የመሪነቷን ደረጃ ይዛ እንድትንቀሳቀስ ማድረግ አለብን ቀደም ሲል በዝች ሀገር ላይ የጎላ ሚና ስለነበራት ያንን የጎላ ሚና ለማስቀጠል በምናደርገው ጥሪ በሀሳብ፤ በገንዘብ፣ በሞራል፣ ሁላችንም የቤተክርስቲያን ልጆች በተቋምም ሆነ በግል አብረን እንሥራ በማለት አቶ ተስፋዬ ውብሸት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
{flike}{plusone}