የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ አባቶችን በማፍራት የሚታወቀው የፈለገ ቅዱሳን ሰ/ት/ቤት 43ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አከበረ!
የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ጨምሮ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ያፈራው የወልቂጤ ደ/ፅ/ቅ/ማርያም ፈለገ ቅዱሳን ሰ/ት/ቤት 43ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ከታኅሣሥ 15 እስከ 17 ባሉት ቀናት ውስጥ በደማቅ ሁኔታ አክብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የሦስት ቀን የዐውደ ምኅረት ጉባኤ እና በከተማው ለሚገኙ የሰ/ ት/ቤቶች የአገልግሎት ሥልጠና ተሰጥቷል።
በተያያዘም የምክክር መድረክ እና ከቀድሞ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት ጋር የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል።
ብፁዕነታቸው በጉባኤው ላይ ተገኝተው በሰጡት አባታዊ ትምህርት በዓሉ የሰ/ ት/ቤቱን ልደት ለማክበር ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ሰንበት ተማሪዎቹ በምን ዓይነት የአገልግሎት ሕይወት እንዳሉ ለማሳየት እና አገልግሎቱ እንዴት ማደግ እንዳለበትም ለመምከር እና ስልት ለመንደፍ እንደሆነ ገልጸዋል።
ስለ ሰ/ት/ቤት ምንነት፣ የሰ/ት/ቤት አስፈላጊነትንና እና ዓላማ በሰፊው ያብራሩ ሲሆን አገልግሎቱም ከእነ ቅዱስ እስጢፋኖስ መመረጥ አንስቶ እንደ ተጀመረ ጠቅሰዋል።
አገልግሎቱ በአራቱም የዓለም አቅጣጫ በመሰራጨቱ የምዕመናን ቁጥር ሲጨምር እና በየጊዜው መሰባሰብ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር በሰንበት ቀን እንዲሰጥ የተደረገ መሆኑን እና ስያሜውንም ከዚሁ ያገኘ መሆኑን ብፁዕነታቸው አውስተዋል።
በሀገራችንም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በራሷ ፓትርያርክ መመራት ከጀመረችበት ከ1951 ዓ.ም ወዲህ ትምህርቱ መጀመሩን ታሪክን ጠቅሰው በሰፊው አስተምረዋል።
ልጆች የአካዳሚክ ትምህርታቸውን ከሰኞ እስከ አርብ እየተማሩ በሰንበት ደግሞ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲበረቱ ፣ በሥነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ መማራቸው ተገቢ እና አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው ሕጻናቱ በጉባኤው ያቀረቡትን የአብነት ትምህርት ጥናት በማንሳት በፊት ወደ ጎጃም ፣ ጎንደር ወዘተ… የቆሎ ት/ቤት በመሔድ ይገኝ የነበረውን ትምህርት ሰ/ት/ቤቱ እዚሁ ማከናወን መቻሉ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ከቤተ ክርስቲያን ስለወጡትም ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት በንሰሐ እንዲመለሱ፣ የሃይማኖት ችግራቸውን ቀርፈው መመለስ ለሚሹት ቤ/ክ በሯ ክፍት እንደሆነ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በምሽት የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር ከቀድሞ የሰ/ ት /ቤቱ ተማሪዎች መካከል ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን ሰ/ት/ቤቱ ታላላቅ አባቶችን፣ በተለያዩ ገዳማት የዘጉ መናኒያንን፣ መነኮሳትን፣ በተለያዩ የቤ/ክ ኃላፊነት ደረጃ ያሉ አገልጋዮችን፣ በትላልቅ የመንግሥት እና የግል ተቋማት የሚሠሩ ሰዎችን ያፈራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በየኔታ ገ/ጊዮርጊስ አማካኝነት ከኳስ ሜዳ መጠራት ታሪክ ሁሉንም ያስገረመ እና የቅዱስ አትናቴዎስን ከጨዋታ ሜዳ መጠራት ታሪክ እንዲያስታውሱ ያደረገ መሆኑም ተነግሯል።
በጉባኤው ላይ ዶ/ር ዲ/ን ቴዎድሮስ ከአዲስ አበባ እና ዲ/ን ስንታየሁ ከሲዳማ ሀገረ ስብከት በመምጣት አስተምረዋል።
የሰንበት ተማሪዎች በአገልግሎት እንዲበረቱ የሚያደርግ ሥልጠናም በዶ/ር ዲ/ን ቴዎድሮስ ተሰጥቷል።
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
ዘገባ፦ በሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል
መረጃ እና ፎቶ፦ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት