“የቤተ ክርስቲያንን እድገት በተግባር አረጋግጠን የቤተክርስቲያንን ልዕልና ለማስጠበቅ በጋራ መሥራት ይኖርብናል” ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በተገኙበት የመጀመሪያውን ቀን ጉባኤና የትውውቅ መርሐ ግብር አካሔደ።
አስተዳደር ጉባኤው ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሔደው ጉባኤና የትውውቅ መድረክ ላይ በቀጣዮቹ የሥራ ጊዜያት የቤተክርስቲያንን ልዕልናና ዕድገት ሊያረጋግጥ የሚችል ሥራ በመሥራት ቤተ ክርስቲያንን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዳደር ጉባኤው ፍፁም የሆነ ተቋማዊ አሠራርን ተከትሎ እንዲሁም የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን መመሪያ ጠብቆ በመሥራት ውጤት እንደሚያስመዘግብ አረጋግጧል።
ከልማት ሥራዎች አንጻር በከተማችን ውስጥ የሚታየውን የልማት ሥራ ታሳቢ ባደረገ አግባብ በቤተ ክርስቲያናችን ሥር የሚገኙ ቦታዎች በአስቸኳይ ወደ ልማት ገብተው ከልማቱ በሚገኘው ውጤት ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት ሥራችንን አጠናክረን የምንቀጥልበትን ሁኔታ መፍጠር ይኖብናል ያለው አስተዳደር ጉባኤው የቤተክርስቲያንን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል አግባብ ሥራችንን መሥራት እንችል ዘንድ የብፁዕነትዎ ቆራጥ አመራርና የአስተዳደር ጉባኤው ጥንካሬ ወሳኝ በመሆኑ ወቅቱን ታሳቢ ያደረገ ሥራን በመዘርጋት የቤተክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ከብፁዕነትዎ ጎን በመሆን ጠንክረን እንደምንሠራ ለማረጋገጥ እንወዳለን ብሏል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ቤተ ክርስቲያን አንድነቷ ተጠብቆ፣ ስብከተ ወንጌል ተስፋፍቶ፣ ልማቷ ተፋጥኖ፣ እድገቷ ተረጋግጦ፣ልዩነቶች ጠበው፣ አንድነታችን ጸንቶ፣ በተግባር የሚገለጥ ተቋማዊ ሥራ ሠርተን የቤተ ክርስቲያንን እድገት በተግባር አረጋግጠን የቤተክርስቲያንን ልዕልና ለማስጠበቅ በጋራ መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
እግዚአብሔር አምላክ ወደዚህ ኃላፊነት ያመጣኝ ማንነቴን ለመግለጽ ስለፈለገ ነው። ያሉት ብፁዕነታቸው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የተጀመሩ ሕንጻዎች መቋጫ አጥተው ዛሬ ድረስ እናያቸዋለን። በዚህ ዘመን በዘጠና ቀናት ሕንጻዎች በሚገነቡበት ጊዜ የኛ ሕንጻዎች እስከ ዛሬ አለማለቃቸው ያሳዝናል ካሉ በኋላ እነዚህንና ሌሎች የልማት ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፈጸም እንሠራለን ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያን በብዙ ፈተና ውስጥ እንደምትገኝ የገለጹት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በመላ አገራችን የሚስተዋለውን መለያየት ወደ አንድ በማምጣት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናት ሉዐላዊትና ኩላዊት ቤተ ክርስቲያንን ዕውን ለማድረግ በርትተን እንሠራለን ብለዋል።
አንድነት፣ ፍቅር፣ ስምምነትና ተቋማዊ እሳቤን ማዳበር ከቻልንና በአንድነት ከቆምን የቤተ ክርስቲያንን ፈተናዎች፣የሚገጥሟትን
ተግዳሮቶች ሁሉ ተሻግረን መሥራት ከቻልን የቤተ ክርስቲያናችንን ዕድገት ለማረጋገጥ ጊዜ አይወስድብንም ብለዋል።
ከመንግስሥት አካላት ጋር ተግባብተን እንሥራ ስንል በጋራ በሚያሠሩንና የቤተክርስቲያንን መብት በምናስጠብቅበት ሁኔታ ላይ በጋራ እንሥራ ማለት ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ጉባኤው የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ተቋም ተኮር ሥራዎችን መሰረት አድርገን እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ትኩረት በመሥራት የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁዎች ነን በማለትና ቃል ገብቶ የዕለቱን ስብሰባ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጸሎት አጠናቋል።
©️ የ/ኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ