የቅዱስ ፓትርያርኩን “ሐዋርያዊ አገልግሎት ፤ አባታዊ ትምህርት ፤ ወቅታዊ መረጃዎችና ታሪካዊ ሰነዶችን” የሚያቀርብ ድረ-ገጽ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ይፋ ተደረገ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ፤ የቅዱስነታቸውን የዕለት ከዕለት ሐዋርያዊ ተግባራት አባታዊ መመሪያዎች፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን እና የቤተክርስቲያኒቱን ዘመናዊና ታሪካዊ ክንውኖች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ የሚያደርግ አዲስ ድረ-ገጽ በይፋ ሥራ ማስጀመሩን አስታወቀ።የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት eotcp.org በሚል አድራሻ ይፋ ያደረገው ይህ ዲጂታል መድረክ፤ ከመደበኛ የዜና ማሰራጫነት ባለፈ የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊና መንፈሳዊ መረጃዎች በአንድ ማዕከል አደራጅቶ የያዘ “ዲጂታል መረጃ ማዕከል” ሆኖ ያገለግላል፡፡
ይህ አዲስ ድረ-ገጽ ከመንበረ ፓትርያርክ የሚወጡ ይፋዊ መግለጫዎችና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ለምዕመናን የሚደርሱበት አማራጭም ይሆናል ተብሏል፡፡
በድረ-ገጹ የቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ጉባኤያት ውጤቶችና መመሪያዎች ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ የሚቀመጡ በመሆናቸው መረጃዎችን ከወሬና ከግምት ባለፈ በቀጥታ ከምንጩ ለማግኘት እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስፓትርያርኩን ዕለታዊ ክንውኖችና አባታዊ ትምህርቶችንም ድረ-ገጹ ሠፊ ሽፋን ሰጥቷቸዋል።
በዚህም በድረ-ገጹ “ቃለ በረከት” በሚለው ክፍል ሥር የቅዱስነታቸው መንፈሳዊ መመሪያዎች በጽሑፍ ተቀምጠው የሚገኙ ሲሆን፣ “ዜና መዋዕል” በሚሰኘው ገጽ ደግሞ የፓትርያርኩን ታሪካዊ ጉዞዎችና ዓበይት ኩነቶች በዝርዝር ማግኘት የሚያስችል ነው፡፡
ይህም ምዕመናን ስለ ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶቻቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት ወቅታዊና ተአማኒ መረጃ እንዲኖራቸው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተመልክቷል።
የቅዱስ ፓትርያርኩ ሐዋርያዊ አገልግሎት የቤተክርስቲያናችን ታሪክ አካል እንደመሆኑ በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች ተከፍሎም በዚሁ ድረ-ገጽ ቀርቧል።
የሀገር ውስጥ አገልግሎቶችን በተመለከተም በአህጉረ ስብከት የሚደረጉ ጉብኝቶችና በዓላት አከባበር በስፋት የሚዘገብበት ሲሆን ፣ የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጉዞዎች ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተጽዕኖና የወንጌል ሥርጭት በሚወክል መልኩ የሚሰፍርበት ይሆናል ተብሏል፡፡
ከመረጃ ሥርጭት ባለፈ ድረ-ገጹ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ራሱን ለዘመናዊ የመረጃ ፍሰት ክፍት ማድረጉን የሚያሳዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችንም አካቷል።
በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀው ይህ ድረ-ገጽ ፣ ከተለያዩ ማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለው በመሆኑ ምእመናን መረጃዎችን ዘመኑን በዋጀ መልኩ እንዲያገኙ ያግዛል።
በተጨማሪም በስልክ፣ በኢሜይልና በፖስታ ሣጥን ቁጥር አማካኝነት ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሚደረግበት “ያግኙን” የሚሰኝ የግንኙነት መስመርም በድረ-ገጹ በግልጽ ተቀምጧል።
በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት በኩል ይፋ የሆነው ይህ ዲጂታል መድረክ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያሏትን ሠፊ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለዓለም ለማስተዋወቅና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ውስጥ እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር ነው፡፡
ድረ-ገጹ ይፋ መሆኑን አስመልክተው መረጃ የሰጡን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ፀሐፊ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ ድረ-ገጹ እውን እንዲሆን በሃገር ውስጥና በባህር ማዶ የሚገኙ የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች በብር እስከ 400 ሺህ የሚገመት በሙያቸው እና በሌሎችም መልኮች አስተዋጾ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የቅድስት ቤተክርስቲያን ምዕመናንና መረጃ ፈላጊዎች eotcp.org በመግባት ትክክለኛውንና ይፋዊውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መረጃዎች እንዲከታተሉም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ፀሐፊ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
©ኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነትመምሪያ
