የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይን በተመለከተ በብፁዓን አባቶች የሚመራ አጥኝ ኮሚቴ መሠየሙ ተገለጸ።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይን በተመለከተ በብፁዓን አባቶች የሚመራ አጥኝ ኮሚቴ መሠየሙ ተገለጸ
የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ለውይይት ከያዛቸው 28 አጀንዳዎች መካከል በተራ ቁጥር 5 እና 6 የሚገኙት ሀገረ ስብከቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች ነበር።
በዚህ መነሻነት ጉባኤው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አማካኝነት የተሰይመው አጥኝ ኮሚቴ በሀገረ ስብከቱ ያሉ ችግሮችና መፍትሔዎች በሚል የምርመራና የውሳኔ ሐሳብ ሪፖርት አቅርቧል።
በተጨማሪም ቅዱስ ሲኖዶስ በተራ ቁጥር 6 በተያዘው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጥያቄ አጀንዳ በዋና ሥራ አስኪያጁ የተመራ ልኡክ በምልዐተ ጉባኤው በአካል ቀርቦ ዝርዝር ጉዳዮችን አስረድቷል።
በዚህም ቅዱስ ሲኖዶሱ በሁሉቱም በኩል የቀረቡት ጉዳዮች በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ሀገረ ስብከቱን በተመለከተ እንዲጠና በብፁዓን አባቶች የሚመራ ልኡክ ሠይሟል።
ስለሆነም በብፁዓን አባቶች የሚመራ ኮሚቴም ጥናቱን ለግንቦት ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ እንዲቀርብ ወስኗል።
በዚህም
1.ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
2.ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ
የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና
የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት
3.ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ
የጀርመንና አካባቢው እንዲሁም የምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተጨማሪም ከሊቃውንት 4 እንደሚካተቱበት ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በተመለከተ ከዚህ በፊት ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አጣሪ ልኮ ውጤቱን ለሀገረ ስብከቱ ሳያሳውቅ ተጨማሪ አጣሪ በመላኩና በሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ምክንያት ሀገረ ስብከቱ ኮሚቴውን ሳይቀበለው ቀርቷል። ይህንንም ጉዳይ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ለሚመለከታቸው አካላት ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወቃል።

Source:-አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ