የቅዱስ መስቀል ደመራ በዓል አከባበርን አስመልክቶ የማጠቃለያ የምክክር ጉባኤ ተካሔደ።
የቅዱስ መስቀል ደመራ በዓል አከባበርን አስመልክቶ የማጠቃለያ የውይይት ጉባኤ ተከናወነ።
በየዓመቱ የሚከበረው የቅዱስ መስቀል ደመራ በዓል ቤተ ክርስቲያናችን በዐደባባይ ከምታከብራቸው ከጌታ ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ ነው።
የ፳፻፲፯ ዓ/ም የሚከበረው የቅዱስ መስቀል ደመራ በዓል አስመልክቶ በዚህ ወር በተለያዩ ቦታዎችና ደረጃዎች የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በዛሬው ዕለት የእነዚህ ውይይቶች ማጠቃለያ መርሐ ግብር ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መጋቢ ታምራት
የከተማው ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ፣ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሐላፊ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ የገዳማትና የአድባራት ዋና አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች በተገኙበት ተከናውናል።
የምክክር መድረኩ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጋር በመሆን የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ በዓሉን አስመልክቶ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች በባለሙያዎች የቀረበ ሲሆን ይህን መሠረት በማድረግ ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበውበታል።
መጋቢ ተአምራት የአዲስ አበባ ከተማ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ እንደገለጹት ተደጋጋሚ የምክክር መድረኮች ማከናወን ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩ በዓሉ ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኑ እንዳለ ሆኖ ቅርስነቱ ከሀገር አልፎ የዓለም ሀብት በመሆ፣ በዓሉ የሰላም በዓል ስለሆነ በሰላም መከበር ስላለበት እንዲሁም ሀገራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ የሀገርን መልካም ገጽታ የሚናገር ድንቅ በዓል በመሆኑ ነው ብለዋል።
አክለውም ከሌሎች አብያተ እምነት አባላት ጋርም በዓሉ የሁሉም በመሆኑ በሰላም እንዲከበር የድርሻቸውን ሚና እንዲወጡ መወያየታቸውንም ገልጸዋል።
ክብር ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የከተማው የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሐላፊ በበኩላቸው በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ተደጋጋሚ ውይይቶችና ምክክሮቾ መደረጋቸውን ገልጸው።
አክለውም በሀገሪቱና እና በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዐት ያልተፈቀዱ ድርጊቶችን ከማድረግ መቆጠብ እንደሚያስፈልግ አስተውሰው የበዓሉ ተሳታፊ ሁሉ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር መሥራት በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።
በዓሉን በሰላም እንዲከበር ሁሉን አቀፍ የጸጥታ አካላት ዝግጅታውን ማጠናቀቃቸውን የገለጹት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ የሁሉም ትብብብር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
ኮምሽነሩ አክለውም ከፍተሻ ጋር በተያያዘ የአገልጋዮችንና የምእምናን ክብር በጠበቀ መልክ እንደሚከናውን ገልጸዋል በዚህም ሁሉም ሊያግዝ ይገባልም ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው በዓሉ በሰላም እንዲከበር የጋራ ውይይት በማድረግ መልካም ሥራ ለሠሩትን የከተማው ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሐላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማን እንዲሁም የከተማውን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመስግነዋል።
ቀጥለውም በዓሉን አስመልክቶ ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ ድርስ ይሠሩ የነበሩ መልካም ተግባራትን በማድነቅ ለሚመለከታቸው አገልጋዮች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ብፁዕነቻው በዓሉ በሰላም ማክበሩ እንዳለ ሆኖ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ሰዓትን በአግባቡ የመጠቀሙ ሁኔታ በእጅጉ ሊታሰብበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
Source:- አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ